1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ቅሬታ

ሰኞ፣ የካቲት 27 2015

የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከሱ ኢትዮጵያ አገራዊ ውይይት ለማከናወን ከተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ተገናኝተው እንደማያውቁና ከዚህ በፊት ከኮሚሽኑ ጋር የነበራቸው ልዩነቶች መቀጠላቸውን አሳውቋል። የኮከሱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ የገለልተኝነትና አካታችነት ጥያቄዎችን ሲያነሱ ቆይተዋል።

Political parties caucus
ምስል Seyoum Getu/DW

የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ቅሬታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ላይ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ አያያዝ ቅሬታ አለን ያሉ አስር የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ መሥርተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ሂደቱን ተቃውመው ኮከሱን የተቀላቀሉ የፖለቲካ ድርጅቶች 16 መድረሳቸው ተገልጿል፡፡ ኮከሱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችን ሰብስቦ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረም፣ ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር እስካሁን የመተማመን ደረጃ ላይ አለመደረሱን ገልጿል። 
የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከሱ ቅዳሜ አከናወንኩ ባለው ስብሳባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አዲስ ለተቀላቀሉት የፖለቲካ ድርጅቶች አቀባበል ሲያደርግ እስካሁን በኢትዮጵያ አገራዊ ውይይት ለማከናወን ከተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር ተገናኝተው እንደማያውቁና ከዚህ በፊት ከኮሚሽኑ ጋር የነበራቸው ልዩነቶች መቀጠላቸውን አሳውቋል። አገራዊ ምክክሩ መርህን የተከተለ እንዲሆን ተሰባሰብን የሚሉት የኮከሱ አባላት የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ላይ የገለልተኝነትና አካታችነት ጥያቄዎችን ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከ16ቱ የኮከሱ አባል የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና በተለይም ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት፤ ኮከሱ ባሁኑ ውይይቱ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አካታችነትና ገለልተኝነት ላይ ግፊት ለመፍጠር ተነጋግሯል፡፡ “በዋናነት የተመካከርነው ብሔራዊ መግባባት የሚባለው መንግስት በገፋበት  መንገድ ሊሳካ እንደማይችልና እስካሁንም ተቋቋመው ኮሚሽን የትም እንዳልደረሰ ነው፡፡ በመሆኑም ጊዜ ከማጥፋትና ተጨማሪ ችግሮች እንዲፈጠሩ ዕድል ከመስጠት ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት በገለልተኛነት ሊዳኝ፣ ሊያስተባብርና ሊያገናኝ የሚችል ኮሚሽን እንዲፈጠር ግፊታችንን ለመቀጠል ነው፡፡”
በኮሚሽኑ አስፈላጊነት ላይ ባናመነታም አመሰራረቱ ላይ ጥያቄ አለን የሚሉ የኮከሱ አባላት እስካሁን ምንም አይነት ግንኙነት ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር እንዳልፈጠሩና ውይይትም ለማድረግ ዕድሉ እንዳልገጠማቸው ያስረዳሉ፡፡ ፕሮፈሰር መረራም እንደሚሉት “የኮሚሽኑን አባላት የመለመላቸው የአንድ ፓርቲ የፓርላማ አባላት በመሆኑ ገለልተኝነቱ ላይ ጥያቄ አለ፡፡” የፓርቲዎቹ ስብስብ ኮከስም የሚጠይቀው በሁሉም ወገኖች የሚታመን ኮሚሽን ይመስረት የሚል አስተያየት እንደሆነ የኦፌኮው ሊቀመንበር በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡ ፕሮፌሰር መረራ አክለውም “የኮሚሽኑ ገለልተኝነትን ጥያቄ ውስጥ ያስገባነው በጫካ ውስጥ ጠመንጃ ይዘው ከሚንቀሳቀሱት ጋር ብቻ ሳይሆን በህጋዊነት ከምንንቀሳቀሰው ከተማ ካለነው ጋርም  ለመወያየት ተነሳሽነት አልተመለከትንም” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው አለመረጋጋትና ግጭት ዘላቂ እልባትም ለመስጠት ገለልተኛ አካል ወክሎ ለምክክር መቀመጥ ብቸኛ መፍትሄው ነው ሲሉ መክረዋል፡፡ 
የኮከሱ አባላት የአካታችነትና ገለልተኝነት ጥያቄ ያነሱበት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ስለቅሬታው እና እልባቱ የሚሰጠውን ምላሽ ለመጠየቅ በተለይም የኮሚሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ተወካይ ጋር በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አስተያየት አልሰጥም በማለት ለሌላ ጊዜ ቀጠሮ በመያዛቸው ለዛሬ አስተያየቱን ማካተት አልተቻለም፡፡ ኮሚሽኑ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ዕቅዱ ግን በመጪው ግንቦት ወር በሙሉ አቅሙ ወደ ዋና ስራው ለመግባት በመጨረሻው ምእራፍ ዝግጅት ላይ መሆኑን አሳውቆ ነበር፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መረራ አስተያየት ግን በኮሚሽኑ የሚስተካከል ተግባር ከሌለ ለአገራዊ ምክክሩ አማራጭ ለማቅረብ ተሰባሰብን የሚሉ የኮከሱ አባል ፓርቲዎች በውይይቱ አይሳተፉም፡፡ “ይስተካከል ብለን ጥያቄ አቅርበናል፡፡ እየተሳተተፍንም አይደለም፡፡ ኮሚሽኑን ከአፈጣጠሩ በገለለልተኝነቱና አካታችነቱ ላይ ስጋት አድሮብናል፡፡ ሀቀኛ ገለልተኛ መሆን አለበት፡፡ ተጠሪነታቸው ለፓርላማ ቢሆንም ፓርላማውን የአንድ ፓርቲ ፍላጎት የበዛበት ነው ብለን ስለምናምን ለውጥ የሚያመጣ ኮሚሽን ሆኗል ብለን አላመንም” ለቅሬታቸው ምክንያት ያሉትን ሃሳብ አኑረዋል፡፡ 
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እና ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር) ከብሔራዊ እንዲሁም ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲያዊ ሉዓላዊነት (ዓረና)፣ የአፋር ህዝብ ፍትሓዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ከክልላዊ ፓርቲዎች በኮከሱ አባልነት የተካተቱት ናቸው፡፡
የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕደግ)፣ አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ (ገዳ ቢሊሱማ) እና ሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ (ሲፌታ) ደግሞ ኮከሱን በአዲስ መልክ የተቀላቀሉ ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ 
ስዩም ጌቱ 
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ 
 

ምስል Seyoum Getu/DW
ምስል Seyoum Getu/DW
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW