1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"የ10ኛዋ ክልል" ቀጣይ ፈተናዎች

ዓርብ፣ ኅዳር 12 2012

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ከትላንት በስቲያ ተካሔዷል። ከሐዋሳ እና ሌሎች ጥቂት ወረዳዎች በቀር እምብዛም ፉክክር ባለመታየቱ ብዙዎች በሕዝበ ውሳኔው "10ኛዋ ክልል" መወለዷን እርግጠኛ ሆነዋል። ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው ይህንን የተሰላ ግምት መነሻ በማድረግ በማድረግ ነው። 

180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

"የ10ኛዋ ክልል" ቀጣይ ፈተናዎች

በፍቃዱ ኃይሉ

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ከትላንት በስቲያ ተካሔዷል። ከሐዋሳ እና ሌሎች ጥቂት ወረዳዎች በቀር እምብዛም ፉክክር ባለመታየቱ ብዙዎች በሕዝበ ውሳኔው "10ኛዋ ክልል" መወለዷን እርግጠኛ ሆነዋል። ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው ይህንን የተሰላ ግምት መነሻ በማድረግ በማድረግ ነው። 

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ታዛቢዎች አባል ሆኜ በመገኘቴ ሪፈረንደሙን እና ሕዝባዊ ስሜቱን በቅርብ ርቀት ለመከታተል ዕድል አግኝቻለሁ። ብዙዎች በጣም ስሜታዊ ሆነው፣ እንደሚቸኩል ሰው ሌሊት ተነስተው ለረዥም ሰዓታት በመሰለፍ ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ ከምርጫ ጣቢያው ብዙም ሳይርቁ የድምፅ መስጠት ስርዓቱ እስኪጠናቀቅ የጠበቁበት ሒደት እንደ ነበር አውቃለሁ። ይህ የሲዳማ ተወላጆች በጉጉት የጠበቁት የክልልነት ጥያቄ ምን ይዞላቸው ይመጣ ይሆን? 

ክልልነት የራስን ሕግ የማውጣት እና መሻር፣ መሬት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን የማስተዳደር፣ ክልላዊ ፖሊሶችን የማደራጀት፣ የመምራት እና ፀጥታ የማስጠበቅ እንዲሁም የተወሰነ ታክስ የመሰብሰብ መብቶችን ያጎናፅፋል። ይህ ትንሽዬ ሉዓላዊ አገርነት ስሜት ይሰጣል። ከዚያም በላይ ሥያሜው ከዞንነት የተሻለ ማዕረግ ስላለው ያጓጓል። ዞንነት የክልል ሞግዚትነት ስለሚመስል አይወደድም። ከዚህ ባሻገርስ? 

የወሰን ማካለል ፈተና

ሲዳማ ዞን ከተለያዩ የደቡብ ዞኖች እና ኦሮሚያ ክልል ጋር የአስተዳደር ወሰን ይጋራል። የወሰን አሠማመሩ ላይ መግባባት ባለመቻሉ ሪፈረንደም የተደረገባቸው ቀበሌዎች ነበሩት። ከነዚህ ቀበሌዎች መካከል እስካሁን ከምዕራብ አርሲ ዞን ጋር የሚዋሰነው የወንዶ ገነት ወረዳ ይገኝበታል። እዚሁ ወረዳ ኤዶ ቀበሌ ውስጥ የምርጫ ጣቢያ ማቋቋም አስቸጋሪ ሆኖ እንደነበር ምርጫ ቦርድም ሳይቀር ገልጿል። ክልልነት የራሱ የሆነ የወሰን ማካለል ጫና ማስከተሉ አይቀርም። ይህ ችግር ግን ምናልባት ግምባር ቀደሙ ቢሆን እንጂ ብቸኛው እና ዋነኛው አይደለም። 

የሕዝቡን ጉጉት ማሟላት

የሲዳማ ተወላጆች "ሆ!" ብለው ሲወጡና ድምፅ ሲሰጡ ከክልልነት በኋላ ምን እንደሚጠብቁ ማንም መገመት አይችልም። ክልልነት ሥሙ ደስ ይላል ነገር ግን የሚጨምረው ብዙም ነገር የለውም። የሲዳማ ዞን ባሁኑ ሰዓት ራስ ገዝ አስተዳደር አለው። ዞኑ ከፍ ያለ የሕዝብ ብዛት ያለው በመሆኑ እና ሐዋሳ ከተማ በዞኑ ውስጥ በመሆኗ የሲዳማ ሕዝብ በኢኮኖሚም፣ በፖለቲካም የተሻለ ተጠቃሚዎች ናቸው። የሐዋሳ ከተማ ከንቲባዎች እና የደቡብ ክልል ፕሬዚደንቶች በብዛት የሲዳማ ተወላጅ እንዲሆኑ የተደረገው ለዚህ ነው። የተለያዩ ቁጥሮች እንደሚያመለክቱት ባለፉት 15 ዓመታት በሐዋሳ የሲዳማ ተወላጆች ቁጥር በጣም ጨምሯል። አሁን ሲዳማ 10ኛዋ ክልል ስትሆን የሲዳማ ተወላጆች ተጨማሪ ነገር የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ ነው። እንዲያውም በደቡብ ክልል ውስጥ ያላቸው ሚና ቀንሶ በዞኑ አስተዳደር ውስጥ ያላቸው ሚና ክልላዊ አስተዳደር ሆኖ ብቻ ይቀጥላል። 

በተለይ ደግሞ ድምፃቸው ወሳኝ ሚና የተጫወተው የገጠር ነዋሪዎች አሁን ካለው ሁኔታ ቅንጣት ታህል የተለየ ነገር የማግኘት ዕድላቸው ክልል በመሆን አይወሰንም። 

ሽግግሩን ማሳመር

ሲዳማ በሪፈንደም ክልል የመሆን ዕድል ያለው የመጀመሪያው ዞን እንደመሆኑ መጠን ሽግግሩ በጣም ውስብስብ እና አስቸጋሪ እንደሚሆን መጠበቅ አይቸግርም። ከደቡብ ክልል ተግባራዊ ፍቺው እንዴት ነው የሚፈፀመው? ደቡብ ክልልስ እንዴት እና መቼ ነው ሌላ ከተማ (የሚቀይር ከሆነ) የሚቀይረው? ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር የሚኖረው ግንኙነት እንዴት ነው የሚሆነው? እነዚህ ጥያቄዎች ቀላል ሊመስሉ ይችላሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ ከብሬግዚትም ያልተናነሱ ውስብስብ ሊሆኑ ይችላሉ።

የሥልጣን ሽኩቻ

"10ኛዋ ክልል" ከተመሠረተች በኋላ ምናልባት የሚወለደው ሌላ ፈተና ክልላዊ የሥልጣን ሽኩቻ ነው። በዚያ ላይ አገር ዐቀፉ ምርጫ በቅርቡ ይመጣል፤ የውስጣዊ ጉዳያቸውን ሳይጨርሱ ለአገር ዐቀፉ ውክልና መዘጋጀት ያስፈልጋል። በዚያ ላይ አመራሮቹን የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ከጎን ሊያሰልፏቸው መቋመጣቸው ካሁኑ እየተስተዋለ ነው። ይህ የውስጥ ፈተና ከውጭ ፈተናዎች ጋር ተባብሮ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምንድን ነው?

የሲዳማ አመራሮች እና ተቃዋሚዎች የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ከፀደቀበት ዕለት ጀምሮ እጅና ጓንት ሆነው ከርመዋል ማለት ይቻላል። ይህ ግን የመቀጠል ዕድሉ በጣም አናሳ ነው። የሲዳማ ፖለቲከኞች ለነዚህ ሁኩ ፈተናዎች መዘጋጀት እና የክልልነት ጥያቄያቸው እውነትም ፋይዳ ያለው እንደሆነ ማስመስከር አለባቸው። ይህንን ለማድረግ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሥራውን ክብደት መረዳት እና ማድረግ የሚቻለውን መረዳት ናቸው።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ« DW»ን አቋም አያንጸባርቅም!

በፍቃዱ ኃይሉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW