የ11 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጥምረት ምስረታ ጉባኤ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 14 2017
ፓርቲዎቹ ይህንንጥምረት ለመመስረት መነሻ የሆናቸው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ከፓርቲዎች ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች በክልላዊ ፓርቲዎች ላይ "አግላይ አካሄድ" በመከተሉ እና ለጥያቄያቸውም "የተሟላ ምላሽ ባለመስጠቱ" መሆኑ ተጠቅሷል። የጥምረቱ ስያሜ እና አርማ ዛሬ እና ነገ በሚደረገው የመስራች ጉባኤው ይወሰናል የተባለ ሲሆን ጥምረቱ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በአንድ ምልክት ለመወዳደር እና "ሥልጣንን ለመጋራት የሚችል ተገዳዳሪ ኃይል ለመሆን" በጋራ እንደሚንቀሳቀስ ተገልጿል። ጥምረቱ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት የሚጠበቅበት ሲሆን ቦርዱ ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ መሰባሰባቸውንም በበጎ እንደሚመለከተው አስታውቋል።//
የጥምረቱ ገፊ ምክንያት ምንድን ነው?
በሰሜን በአማራ እና በትግራይ፣ በምዕራብ በጋምቤላ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በድምሩ በሰባት ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱት 11ዱ ክልላዊ የፖለቲካ ድርጅቶች በ2016 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ19 ክልላዊ ፓርቲዎች ለቀረበለት የውይይት አጀንዳ "አግላይ እና ስኹት" ያሉትን አካሄድ መከተሉ ብሎም ለጥያቄዎቻቸው "የተሟላ ምላሽ" ሳይሰጥ በመቅረቱ፤ በሂደት ግን ኮሚሽኑ ይህንን አተያዩን መቀየር በመቻሉ ግፊታቸውን አሳድገው ጥምረትየመመስረት እንቅስቃሴ ውስጥ መቆየታቸውን ዛሬ አስታውቀዋል። የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዳሮት ጉምዐ ይህንኑ ጠቅሰዋል። "ስንነሳ የክልል ፓርቲዎችን የማግለል አሠራር በኮሚሽኑ በኩል ሲካሆድ ያንን ለመከላከል ነው የተሰባሰብነው።"
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከጥምረቱ የሚጠብቀው
ፓርቲያቸው የዚህ ጥምረት አባል የሆነው እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሰለሞን አየለ የጋራ ምክር ቤቱ ጥምረቱ "በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር አስታራቂ ሆነው የአብሮነት ፖለቲካን ማራመድ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ በእኩልነት፣ በመተሳሰብ እና በመተባበር መሥራትን" ዓላማው እንዲያደርግ ይጠብቃል ብለዋል።
"ቢያንስ አሁን ያለውን የፖለቲካ አለመግባባት፣ አለመረጋጋት፣ የሰላም እጦት፣ ግጭቶችን ሊያስቀሩ በሚችሉ የፖሊሲ አማራጮችን ጭምር እስከማቅረብ የሚሄድ ጥምረት ነው።"
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥምረቱን እንደሚደግፍ ገልጿል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላተ ወርቅ ኃይሉ "ይህ ጥምረት የተመሰረተው በተለይም ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተቃረበበት በመሆኑ" የሚደገፍ ነው ብለዋል። ይሁንና የጥምረቱ ውጤትመለኪያ ፓርቲዎቹ በሂደት የሚያደርጉት በጎ ተጽዕኖ እንጂ ምስረታው ብቻውን ግብ እንደማይሆን ገልፀዋል። "በተመሳሳይ ሀሳባችሁ ተባብራችሁ በመሥራት መጪውን ምርጫ ታማኝ እና ሰላማዊ እንደምታደርጉ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓትን በሀገራችን እንደምታስፋፉ እምነቴ ነው።" ለዚህ ጥምረትም ይሁን ለሌሎች ፓርቲዎች ለቀጣዩ ምርጫ አሁን ያለው ሀገራዊ ዐውድ ምን ያህል ይፈቅዳል የሚለእን የተጠየቁት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ቅድሚያ ሰላም ሊሰፍን ይገባል ብለዋል።
ጥምረቱን የመሠረቱት ፓርቲዎች እነማን ናቸው?
እነዚህ 11 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ የምርጫ ምልክት ለመወደግር፣ ሥልጣንን በጋራ ለመጋራት የሚችሉ ተወዳዳሪ ኃይል ለመሆን ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። እውቅና ለማግኘት ገና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ ይጠብቃሉ። ቦርዱ ግን ለዚህ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አስታውቋል። የጥምረቱ ስያሜ እና አርማ ዛሬ እና ነገ በሚደረግ ጠቅላላ ጉባኤ ይወሰናል ተብሏል። ጥምረቱን መሠረትን ያሉት ፓርቲዎች አገው ለፍትሕና ዴሞክራሲ፣ አገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የዶንጋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ አፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ፣ ጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ እና የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ናቸው።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ልደት አበበ