የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና እየተሰጠ ነው
ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2018
ይህም የፈተናውን ፍጹም ፍትሃዊነትና ታማኝነት ለማረጋገጥ ነው ቢባልም ይህ ጥብቅ ቁጥጥር በተማሪዎች ላይ ጭንቀትን ፈጥሮባቸው እንደ ነበር ተናግረዋል። ፈተናው እና ቁጥጥሩ የተማሪዎችን በራስ የመተማመን ስሜት ለማጎልበት እና በሥራቸው ብቻ ተመስርተው ውጤታማ እንዲሆኑ ለመድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት እዳስታወቀው ፈተናው እስከ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል። በዚህ ፈተና ላይ በአጠቃላይ 563,501 ተፈታኞች ይቀመጣሉ። ከእነዚህም መካከል 306,456ቱ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ 257,045ቱ ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው።
ፈተናው በ 607 የፈተና ማዕከላት ውስጥ በስድስት ዙሮች የሚሰጥ ሲሆን፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ዙር ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ታውቋል። የዘንድሮውፈተና ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት የውጤት ማሽቆልቆል ማሻሻያዎችን ለማስመዝገብ ትልቅ ዝግጅት የተደረገበት መሆኑን የትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ DW በተገኘባቸው በሦስት የፈተና ማዕከላት ውስጥ፣ተማሪዎች ያለ ችግር ወደ ተመደቡባቸው የፈትና ማዕከላት ክፍሎች መግባታቸውን ተመልክተናል። በማዕከላቱ የተደረገው ጥብቅ ፍተሻና ዝግጅት በተለየ መልኩ የሚጠቀስ ነው። ተማሪዎች የተከለከሉ ዕቃዎችን እንደ ስልክ፣ታብሌት እና ስማርት ሰዓት ያሉ ሳይይዙ በመምጣት ለሕጉ ተገዢ መሆናቸውን አሳይተዋል። ወደ ማዕከላት ሲገቡም አስቀድሞ የተዘጋጀላቸውን የፈተና መግቢያ ካርድ፣ የተማሪ መታወቂያ፣የተፈቀደ እስክሪብቶ ወይም እርሳስ እና ባዶ ወረቀት ብቻ መያዛቸውን አረጋግጠናል።
መነፅር የሚያረጉ ተማሪዎች በሀኪም የታዘዘ ለመሆኑ የሀኪም ፍቃድ ወረቀት ሲጠየቁ DW በተመልክቷል። ፈተናውን ተፈትነው የወጡ ተማሪዎች የፈተና ውሎ ያለምንም የደኅንነት ስጋት በሰላም መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ካለፉት ዓመታት ዝቅተኛ የውጤት ሪከርድ በመነሳት ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተማሪዎቹ ይናገራሉ።በመላው ሀገሪቱ የተጀመረው ይሄው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በቀጣዮቹ ቀናትም በተመሳሳይ የዝግጅትና የጥንቃቄ ደረጃ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ለተፈታኝ ተማሪዎች በሙሉ መልካም ዕድል እንመኛለን።
ሃና ደምሴ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ