1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

የ12ኛ ክፍል የጎንደር ተማሪዎች ጉዳይ ከምን ደረሰ?

ዓርብ፣ ነሐሴ 19 2015

ዘንድሮ የ12ኛ ክፍልን መልቀቂያ ፈተና በጎንደር ከተማ ይወስዱ የነበሩ 16ሺ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን ሙሉ በሙሉ እንዳልወሰዱ ይታወቃል። ታድያ የፈተናው ጉዳይ ከምን ደረሰ?

የጎንደር ከተማ
የጎንደር ከተማምስል Alemnew Mekonnen/DW

የ12ኛ ክፍል የጎንደር ተማሪዎች ጉዳይ ከምን ደረሰ?

This browser does not support the audio element.

ባለፈው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ካነጋገርናቸው የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች መካከል አንዱ የጎንደር ተማሪ ነው። ወጣቱ እንደገለፀለን የኬሚስትሪ ፈተና የወሰደው ተኩስ እየተተኮሰ ባለበት ሁኔታ ነበር። አበበ ብላችሁ ጥሩኝ ያለን ተማሪ « አራት ፈተና ተፈትነን የኬሚስትሪ ፈተና የምንፈተን ቀን ጠዋት ላይ ይተኮስ ነበር። ፈተና ልንፈተን ወረቀታችንን ተቀብለን እንደተቀመጥን መስኮቱ በጥይት እየተመታ ነው የተፈተነው።  80ያውንም ጥያቄ የመለስንም አይመስለኝ» ነበር ያለን። በአሁኑ ሰዓት አበበ ገጠር ወደሚገኙት ወላጆቹ ተመልሷል። ለአበበ ኃላፊነት ወስዶ እና ወደ ጎንደር ከተማ ወስዶ የሚያስተምረው ታላቅ ወንድሙ እንደገለፀልን የአበበ ስነ ልቦና በነበረው ሁኔታ እጅጉን ተጎድቷል። « በቃ ሳይሳካለት እንደተመለሰ ነው የነገረኝ። ቢያንስ እንኳን ፈተና እስክንጨርስ ጦርነቱ ቢዘገይልን ኖሮ ይል ነበር። »
የአበበ ወንድም ጎንደር ሆኖ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ እየተከታተለ ይገኛል። አሁን ባለው መረጃ መሠረት ተማሪዎቹ የፊዚክስ እና የባዮሎጂ ፈተናዎች እንደሚወስዱ ነው የሚያውቀው። ነገር ግን በጦርነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው የወሰዱት የኬሚስትሪ ፈተና እንደ አዲስ ቢሰጥ ጥሩ ነው ይላል የአበበ ወንድም « እኛ ኬሚስትሪን ጨምሮ እንደሚፈተኑ ነበር ግምቴ። አሁን ግን እንደሰማሁት ፊዚክስ እና ባዮሎጂን ነው የሚፈተኑት። 
አቶ መንግሥት ታከለ አበበ የሚማርበት  የአዞዞ ድማዛ 2ኛ ደረጃ የመንግሥት  ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው። እሳቸው ለዶይቸ ቬለ እንተናገሩት ፈተናውን ያልወሰዱ ተማሪዎች የስነ ልቦና ጉዳት እንዳይገጥማቸው ርዕሰ መምህራን ከትምህርት መምሪያ ጋር ተወያይተው ተማሪዎች ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። « በሁሉም የጎንደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከጎንደር ዩንቨርስቲ የመጡ የሳይኮሎጆ ምሁራን በነበረው ሁኔታ ላይ አጭር የስነ ልቦና ስልጠና አድርገዋል። » ከስነ ልቦናው ስልጠና በተጨማሪ ለተማሪዎች የተደረገ ሌላም ድጋፍ እንዳለ ርዕሰ መምህር መንግሥት ገልፀውልናል።  «የጋራ መግባባት ተደርጎ ፈተናው ቀን በውል ባይታወቅም እስከዚያው ድረስ ሌሎች የተፈተኑት እና እነሱ ያልተፈተኑት የፈተና ወረቀቶች ተሰጥቷቸዋል። ከሰኞ ጀምሮ ደግሞ መምህራን ተመድቦላቸው ያስጠኗቸዋል። » 

ተማሪዎች ፈተና በሚፈተኑበት ወቅት ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ይሰማ ነበርምስል Alemenew Mekonnen/DW

የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው ዘንድሮ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሦስት ካምፓሶች ይፈተኑ የነበሩ 16 ሺ የሚሆኑ ተማሪዎች በከተማዋ በነበረ ውጊያ ምክንያት ፈተናውን ሳይወስዱ ቀርተዋል። የአዞዞ ድማዛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መንግሥት  ፈተናዎቻቸውን ሳያጠናቀቁ ከተመለሱት ተማሪዎቻቸው በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ጠይቀው የተረዱት ምን ይሆን? « ፋሲል ካምፓስ ላይ ችግር አልደረሰም። ችግር የነበረው ማራኪ ካምፓስ ላይ ነው። የተኩስ ድምፅ ስለነበር ያለ መረጋጋት ሁኔታ ነበር እንጂ የተፈጠረ ነገር አልነበረም። ድምፁ ግን አይደለም ለእነሱ ለከተማው ሰው ይሰማ ስለነበር የመደንገጥ ባህሪ ነበራቸው እንጂ እነሱ አካባቢ የተፈጠረ ችግር አልነበረም።»

በወቅቱ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል በነበረው ውጊያ በማራኪ ካምፓስ ላይ በትክክል ስለደረሰው ችግር  ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለማጣራት እና ፈተናው መቼ እንደሚሰጥ ለመጠየቅ ከበላይ አመራሩ ጋር ያደረግነው ሙከራ  ከቀጠሩን ሰዓት ጀምሮ በተደጋጋሚ ስልካቸው ላይ ብንደውልም ጥሪው ስለማይነሳ አልተሳካም። በእዛው ዩንቨርሲቲ የሚሰሩ አንድ ሰራተኛ እንደገለፁን ግን በካምፓሱ ላይ ያስተዋሉት የጎላ ጉዳት እንደሌለ እና ፈተናውም በቅርብ  ቀን ይሰጣል ብቻ ነው የተባለው ብለውናል። 
የ12 ክፍል ፈተና ከሚያስፈትኑ መምህራን መካከል አንድ መምህር ጎንደር ላይ « በታጣቂዎች» መገደላቸው ትምህርት ሚኒስቴር በወቅቱ ማስታወቁ ይታወቃል። 

 

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW