1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

ለምን 5,4 % ብቻ ተፈታኞች የ12ኛ ክፍል ፈተናን አለፉ?

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መስከረም 3 2017

የ2016ዓም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 684,205 ተማሪዎች መካከል ያለፉት 36,409 ተማሪዎች ብቻ ናቸው። ቁጥሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ አሁንም አነስተኛ የሚባል ነው። ችግሩ የቱ ጋር ነው ያለው? ለዚህስ ምክንያት እና መፍትሔው ምን ይሆን?

Äthiopien Vorbereitungen Studenten auf Prüfungen
ምስል privat

ለምን 5,4 % ብቻ ተፈታኞች የ12ኛ ክፍል ፈተናን አለፉ?

This browser does not support the audio element.

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ መሻሻል አሳይቷል። ይሁንና አሁንም ፈተናውን ያለፉት 36,409 ተማሪዎች ብቻ ናቸው።   ለንጽር ያህል በዚህ በጀርመን የዶይቸ ቬለ ስቱዲዮ የሚገኝበት የኖርድ ራይንቬስትፋለን ግዛት የበለጠ ተማሪ ያልፋል።  ባለፈውን ዓመት ፈተና ከወሰዱ 80,500 ገደማ ተማሪዎች 76,500 ያህሉ ፈተናውን አልፈዋል።  ጀርመንን ከኢትዮጵያ ጋር ማነፃጸሩ ከባድ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አነስተኛ ነጥቦች መመዝገብ የጀመሩት ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ ነው። በ 2014 ዓም ፣ 3,3 በመቶ  በ2015 ዓም 3,2 በመቶ በ2016 ዓም ደግሞ  5,4 በመቶ የማለፊያ ውጤቱን አግኝተዋል ተብሏል።   ለውጤቱ ማሽቆልቆል ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶችን ይሰጣሉ።  

ዲንሰፋ ሱሩር ይህ ውጤት እንደሚመጣ ጠብቄው ነበር ይላል። በትምህርቱ ጎበዝ ፣ ወረዳ እና ዞን ወክሎ ይወዳደር የነበረ ተማሪ እንደነበር የገለፀልን ዲንሰፋ እንደሚለው ከሆነ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት 12ኛ ክፍል ሲደርሱ « አስጨንቆ በማስፈተን ሳይሆን» ከታች ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በማሟላት መሆን ነበረበት።«መጨረሻ ላይ ለፈተና መምህር ምደባ የሚወጣው ወጪን እታች ላለው ተማሪ መሠረታዊ ነገር ቢሟላለት ምርጥ ተማሪ ነበር የሚወጣው።  ከ9ኛ ክፍል በኋላ እርስ በእርሱ ይፎካከራል። ማንም አያስኮርጅም። እኛ እታች ሳለን ለሰነፍ ተማሪ ነበር የምናስኮርጀው ምክንያቱም ጎበዝ ተማሪ ይቀድመኛል፣ይመልጠኛል ስለምንል »  

«ተማሪዎች ዓርአያ የሚሉት ሰው ያስፈልጋቸዋል»

በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆነው ዲንሰፋ ሌላም ወሳኝ ነው የሚለው ነገር አለ። ተማሪዎች ዓርአያ የሚሉት ሰው ያስፈልጋቸዋል።« የታነፀ ተማሪ እንዲወጣ ተምረው በጥሩ ውጤት ያለፉ ልጆች ፣ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስ አለባቸው። በአሁን ሰዓት በማዕረግ ከዩንቨርስቲ ተመርቀው የወጡ ልጆች በየአካባቢው አብደው ነው የምናያቸው። ሰፈር ላይ እኔን አይተው ትምህርት ያቋረጡ አሉ። ሰፈር ላይ አርዓያ የሆንኩ ልጅ ነበርኩ። ስራ አጥቼ ለብዙ ጊዜ እቤት ስቀመጥ እነ እንትናስ የት ደረሱ ይሉ ጀመር»

የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መምህራንንም ጠይቀናል። «የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት  እንዲህ አነስተኛ እንዲሆን ሚና የሚጫወቱ በርካታ ነገሮች አሉ »ይላሉ ስማቸውን መግለፅ የማይፈልጉ አንድ መምህር ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን ። እሳቸው ከሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ያለፈ አንድም ተማሪ የለም።« በመምህራን በኩልም ክፍተት አለ። በተማሪዎችም በኩል ክፍተት አለ። ገጠር ስለሆነ ፣ ተፎካካሪም የለም። ተማሪዎች እንዴት እንደሚፎካከሩ ስለማያውቁ አያጠኑም። ለመምህራንም ከመንግሥት የሚከፈለው ጥቅማ ጥቅሞች ባለመከፈሉ ችግሮች አሉ። በመንግሥት በኩልም አስፈላጊ ነገሮች በቂ መፅሀፍ ለተማሪዎች አልተሟሉም።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋምስል Education Ministry of Ethiopia

«የግድ ታሳልፋላችሁ የሚል ጫና እኛ መምህራን ላይ አለ»

በተለይ በገጠራማ አካባቢ ማስተማር እና ተማሪዎችን ብቁ ማድረግ ትልቅ ፈተና እንደሆነ ሌሎች መምህራንም ገልፀውልናል።  « የገጠር መምህራን ተማሪዎችን እቤት ድረስ እየሄድን ቀስቅሰን አምጥተን ነው የምናስተምራቸው» የሚሉት ተከታዩ ስማቸውን ለዶይቸ ቬለ ብቻ የገለፁ መምህር የገጠማቸውን ገልፀውልናል።« ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በምናስተምርበት ጊዜ ገጠር አካባቢ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የሚመጡት አንድ ወር ፣ሁለት ወር ቀርተው ነው። እንደፈለጋቸው ይቀራሉ።  የበላይ አካላት ደግሞ ተማሪ መውደቅ የለበትም የግድ ታሳልፋላችሁ የሚል ጫና እኛ መምህራን ላይ  አለ። እኛም ለመኖር ስንል እናሳልፋለን። እንደዚህ እየተገፉ 12ኛ ክፍል ይደርሳሉ። 12ኛ ክፍል ላይ ደግሞ የሚታየው ውጤት ይመዘገባል»  

በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን የ2ኛ ደረጃ አስተማሪ እንደሆኑ የገለፁልን መምህር አለባቸው እንደነገሩንም መምህራን ከበላይ አካላቶች ብዙ ጫና ይገጥማቸዋል። ስለሆነም ተማሪዎች በብዛት ኮርጀው 12ኛ ክፍል እንደሚደርሱ የሚያውቁት ነገር ነው።  « መምህሩ ቁጥጥር ላድርግ ካለ ይጠቆራል። ወይም የደረጃ እድገት አያገኝም። ዝም  ብለህ ለምን አታሳልፍም የሚል ተፅዕኖ ስለሚመጣ ተማሪዎች በጋራ ነው የሚሰሩት። የቡድን ስራ ነው። ፈተና የይስሙላ ነው። ከሶስት አመት በፊትም (12ኛ ክፍል) በጋራ ነበር የሚፈተኑት በዛን ዘመን ያን ያህል የሚወድቅ አልነበረም። »

ተማሪዎች በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ሆነው መፈተናቸው

ስለሆነም ያለፉት የሶስት አመታት ውጤቶች ብዙም የማይገርማቸው መምህር አለባቸው አክለው እንደገለፁልን  አሁን ላይ ትምህርት ቤቶች የፖለቲካ ስራ የሚሰራባቸው ቦታዎች መሆናቸው የትምህርት ማስተማር ፈተናውን የባሰ አድርገውታል።« ዝምብሎ ምን ያህል መምህር የድርጅት አባል ነው፣ ምን ያህል ተማሪ የድርጅት አባል ነው የሚል ሁኔታ ነው ያለው ባለፉት አምስት እና ስድስት አመታት። ለትምህርት ትኩረት የሚሰጥ የለም። »

ተማሪዎች ፈተና ለመፈተን ተፈትሸው ሲገቡ ምስል Shewangizaw Wegayoh/DW

የ7ኛ ክፍል የሳይንስ መምህር እንደሆኑ የገለፁልን መምህር ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንደውም ዘንድሮ ያለፈው ተማሪ ቁጥር  ብዙ ነው ባይ ናቸው። « 8ኛ ክፍል ስሙን በእንግሊዘኛ መፃፍ የሚችል የለም (ገጠር)። እኔ እንደ መምህር የመጣው ውጤት ይበዛል ባይ ነኝ። የ12ኛ ክፍል አይነት ምዘና እታች ድረስ ቢመጣ ከክፍል ሁለት ልጆች አያልፉም»

ለአጭር ጊዜም ቢሆን በመምህርነት ያገለገሉት ሀብታሙ  ካሳዬ ግን « ይሄ ሁሉ ተማሪን አላዋቂ አድርጌ አልቆጥርም፣ቢያንስ ከአንድ ትምህርት ቤት ጥቂት ጎበዝ ተማሪዎች አይጠፉም። » ይላሉ።  ስለሆነም በ 1363 ትምህርት ቤቶች ዉስጥ አንድም ተማሪ ዘንድሮ አለማለፉ  አስገርሟቸዋል።« እጎአ በ 2018 ዓ ም 12ኛ ክፍል ኢኮኖሚክስ እና ቢዝነስ አስተምር ነበር። በወቅቱ ጦርነት ባይኖርም ቢያንስ 10 የሚሞክር ወይም ጎበዝ ተማሪ አይጠፋም።  አሁን ላይም ቢሆን የድሮውን ጥያቄዎች ስሰጣቸው በደንብ ነው የሚሰሩት። ስለዚህ ያ ሁሉ ተማሪ ሰነፍ ነው ብሎ መደምደብ አግባብ አይመስለኝም።»

ወጣት ናሆም ባለፈው ዓመት ነው ከዩንቨርስቲ ተመርቀዉ። እሱስ ለተማሪዎቹ ብቁ አለመሆን ችግሩ ምኑ ጋር ነው ያለው ይላል?« በግልፅ የሚታዩ ችግሮች አሉ። በዋንኘት የሰላም መደፍረስ እና የፀጥታ ችግር ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ተማሪዎች መማር አይችሉም። ከዚህ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የመጣው የኢኮኖሚ ችግር እነዚህ ነገሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል።»

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ባጀት እና ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ይችላሉ?

በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ምግብ ሲቀበሉምስል Shewangizaw Wegayoh/DW

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ባጀት አነስተኛ መሆኑን እና ተማሪዎችን ለመመገብ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ባለፈው ዓመት የሰሙ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ስላልቻሉ « ሆን ተብሎ ወደ ከፍተኛ ተቋም የሚገቡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል የተወሰደ ርምጃ ነው ሲሉ ትምህርት ሚኒስትቴር እና መንግሥትን ይተቻሉ።  ባለፈው ዓመት ትምህርቱን አጠናቆ ከዩንቨርሲቲ የወጣው ናሆም ይህን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ባይጋራም ከፍተኛ ችግሮች ማስተዋሉን ገልፆልናል።« በካምፓስ ውስጥ፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ብዙ የማይገኙ ነገሮች አሉ። በዛ  ሁኔታ ተማሪዎች ለችግር እየተጋለጡ ነው ያሉት። ከመሠረታዊ  የሚበላ የሚጠጣ ነገር ጀምሮ  የተለያዩ ፋሲሊቲዎች የሉም። አንዱ የኢኮኖሚ ችግር ሲሆን ሌላው ደግሞ ሙስና ነው።ያለውን ሀብት በአግባቡ ያለመጠቀም እና ለተማሪዎች ተደራሽ አለማድረግ»

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW