የ2015 ዓ.ም. የኢሬቻ ሆራ ሀርሰዲ በቢሾፍቱ ዛሬ ተከበረ
እሑድ፣ መስከረም 22 2015የ2015 ዓ.ም. የኢሬቻ ሆራ ሀርሰዲ ዛሬ በቢሾፍቱ በደማቅ ስነስርዓት ተከብሮ ዋለ፡፡
የኦሮሞ ዓመታዊ የምስጋና አሰጣጥ ክብረ በዓል የሆነው ኢሬቻ በርካታ ተሳታፊዎችን ባሳተፈ መልኩ ነው የተከበረው፡፡
አባገዳዎች ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በሆራ ስፍራ ተገኝተው ወንዙን ባርከው ባደረጉት የምርቃት ስነስርዓትም በዓመቱ ህዝቡን መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል፡፡
ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ የተከበረው ኢሬቻ ሆራ ሀርሰዲ ትናንት በአዲስ አበባ እንደተከበረው የኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ ሁሉ በጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር የታጀበ ነበር፡፡
ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ ከተፈቀደላቸው ውስን ተሽከርካሪዎች ውጪ ወደ ቢሾፍቱ ከተማ እንዳይገቡ ጭምር በማድረግ ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር የተደረገበት የዘንድሮው የኢሬቻ ሆራ-ሀርሰዲ ዓመታዊ ክብረ በዓል፤ ዛሬ ከማለዳው ከ12 ሰዓት ጀምሮ አባገዳዎች በተገኙበት ነው በሆራ ሀርሰዲ ሀይቅ ላይ በደማቅ ስነስርዓት መከበር የጀመረው፡፡
አባገዳዎች በማለዳው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በተሰበሰበበት በሆራ ስፍራ ተገኝተው የምርቃትና የኢሬፈና ስነስርዓቱንም አስጀምረውታል፡፡
ከለገጣፎ ለገዳዲ መጥተው ኢሬቻ ሆራ-ሀርሰዲ ላይ የተገኙት አቶ ኃይሉ በቀለ የዘንድሮውን ጨምሮ ከዚህ ስርዓት ቀርተው አያውቁም፡፡ እንደ እሳቸው አስተያየት የዘንድሮው የኢሬቻ አከባበሩ ደግሞ የተለየና መልካም ድባብ ያለው ነው፡፡
“እኔ እንደምታየኝ አዛውንት ነኝ፡፡ ነፍስ ካወኩበት ጊዜ ጀምሮ ግን ከዚህ ኢሬቻ ቀሪቼ አላውቅም፡፡ ዘንድሮ የተሳተፍኩት ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ የማላስታውሰው ለዚያ ነው” ይላሉ አቶ ኃይሉ፡፡ ሰላማዊ ያሉት የዘንድሮ የቢሾፍቱው ኢሬቻ መልካም ድባብ እንዳስተዋሉበትም በአስተያየታቸው ጠቅሰዋል፡፡
እኚህ የእድሜ ባለጸጋ የኢሬቻን ሰላም ሰባኪነትም ገልጸው፤ በተለይም በኦሮሚያ ያለውን ልዩነቶች በመፍታት ለሰላምም ለመስራት በኢሬቻ የሚስተዋለውን አንድነት መጠቀም ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ወጣት ደበሌ ነጋ ደግሞ 5ኛውን የኢሬቻ ተሳትፎ በማድረግ በዛሬው ክብረ በዓሉ ላይ የተሳተፈው ከአቃቂ አከባቢ በመምጣት ነው፡፡ ወጣት ደበሌ በዘንድሮው የኢሬቻ ተሳትፎ ያስደመመው የተሳታፊዎቹ በደመቀ ባህላዊ የኦሮሞ አልባሳት በጎላ መልኩ ደምቀው መታየት ነው፡፡
ወጣቱ በኢሬቻ አከባበሩ ተመለከትኩ ያለውን ትዝብትም ለዶይቼ ቬሌ ሲያጋራ፤ “እንደ ምልከታዬ የዘንድሮ ኢሬቻ ላይ ቅር ያለን የተወሰነ ነገር አለ፡፡ ሰው እንደ በፊቱ በተለይም ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም. የኢሬቻ አከባበር ሁሉ በነጻነትና በሰፊው ቢሳተፍ ምንኛ ደስ ባለኝ፡፡ አሁን ያ ነጻነትና ደማቅ ተሳትፎ በመጠኑም ቢሆን ተገድቧል ብዬ አምናለሁ፡፡ የጠበቀ የፀጥታ ሁኔታ ለሰላሙ አስፈላጊ ቢሆንም ሲበዛ ግን ተሳትፎን ይገድባል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት በዚህ ላይ የሚያደርገው የበዛ ቁጥጥር የኢሬቻን መልክ እንዳይቀይረው ስጋት አለኝ” ሲል ተናግሯል፡፡
ቢዲቅቱ ደበሌ ደግሞ ዘንድሮ በሆራ ሀርሰዲ የሁለተኛ ጊዜ የኢሬቻ አከባበር ስነስርዓት ተሳትፎን ነው ያደረገችው፡፡ እንደ እሷ አስተያየት ደግሞ የዘንድሮ ኢሬቻ በእጅጉ ደማቅና ከሌላውም ጊዜ የተሻለ ነው፡፡
“የዘንድሮ ኢሬቻ የሰው ተሳትፎ እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ሰላማዊና ደስ የሚል ድባብም አለው” ስትል አስተያየቷንም አጋራችን፡፡ ወጣቷ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በኢሬቻ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየሰፋ መምጣትንም በጎላ በጎነቱ ነው የምትመለከተው፡፡
ይሁንና በፀጥታ ችግር በሚታመሱ የኦሮሚያ አከባቢዎች ከዚህ ቀደም መጥተው በኢሬቻ ላይ ይሳፉ የነበሩት ዘንድሮ የመታደም እድላቸው አነስተኛ መሆኑ እነሱንም ማሰብ እንደሚገባ ሃሳቧን አጋርታለች፡፡ “በቀጣይም አገሩ ሁሉ ሰላም ሆኖ አብሮ ለማብክበር ያብቃን” ስትልም መልካም ምኞቷን አጋራችን፡፡
የዘንድሮ ኢሬቻ ሆራ ሀርሰዲ በደማቅና በርካታ ተሳታፊዎች በታደሙበት ነው የተከበረው፡፡ በከተማዋ ተሽከርካሪዎች ዝር እንዳይሉ ተደርጎ የጠበቀው የፀጥታ ጥበቃ ግን ተሳታፊዎቹ በኪሎሜትሮች የሚቆጠሩ ረጃጅም ርቀት ያላቸው መንገዶችንም በእግር እንዲጓዙ አስገድዷል፡፡
በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ትናንታና እና ዛሬ የተከበረው የኢሬቻ በዓል መጠናቀቅን ተከትሎ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የኢሬቻ አከባበሩን ሰላማዊ ብለውታል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫቸው፤ በኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ እና ዛሬ በተከበረው የሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓል 10 ሚሊየን ህዝብ ወጥቶ ስደናቂ ባሉት አኳኃን ማክበራቸውንም ገልጸዋል።
ለዚህም የፀጥታ ኃይሉ እና የተለያዩ አካላትን አመስግነው፤ “በዓሉን ምክንያት በማድረግ የጠላት ተልዕኮዎች ቢኖሩም ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር በሰላም ተጠናቋል” ብለዋል።
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ