የ2018 በጀት "ከፍተኛ ትኩረት"የሚጠይቅ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ ይጠበቅበታል -ገንዘብ ሚኒስቴር
ማክሰኞ፣ ሰኔ 3 2017
ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት የ8.9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ታስመዘግባለች የሚል ግምት ስለመያዙ ዛሬ የበጀት መግለጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ።
ለ2018 1.93 ትሪሊዮን ብር በጀት መያዙንይፋ ያደረጉት ሚኒስትሩ፣ ከዚህም ውስጥ 1.5 ትሪሊዮን ብሩ ከሀገር ውስጥ ግብር እና ከውጭ እርዳታ የሚገኝ ገቢ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተያዘው በጀት 417 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ያለበት መሆኑም ታውቃል። የበጀት ድልድሉ ለአዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የሚውለውን የካፒታል በጀት አሳንሶ የደለደለ ነው በሚል ከምክር ቤት አባላት ተደጋግሞ ጥያቄ ቀርቦበታል።//
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ባቀረቡት የ2018 የበጀት መግለጫ መንግሥት 1.2 ትሪሊየን ብር ከሀገር ውስጥ ገቢ፣ 282 ቢሊዮን ብር ከውጭ እርዳታ እንዲሁም ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ብድር በድምሩ 1.5 ትሪሊዮን ብር ገቢን ታሳቢ ያደረገ ነው።
"አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የ2018 ጠቅላላ ወጪ በጀት ብር 1.93 ትሪሊዮን ሲሆን፣ ብር 1.2 ትሪሊዮን ለመደበኛ ወጪ፣ ብር 415.2 ቢሊየን ለካፒታል ወጪ፣ ብር 315 ቢሊዮን ለብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የበጀት ድጋፍ እና ብር 14 ቢሊዮን ለክልሎች የዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ድጋፍ የተመደበ በጀት ነው"
ይህ ገንዘብ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ማድረጓን ተከትሎ የብር የመግዛት አቅም በመዳከሙ በውጭ ምንዛሪ ሲሰላ ዝቅተኛ በጀት ነው የሚል ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት ተነስቷል።"የተመደበው በጀት እጅግ አነስተኛ መሆኑን እረዳለሁ። ዘንድሮ የተመደበው የበጀት መጠን ወደ 33.83 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ይሆናል ማለት ነው"
አቶ አሕመድ ሽዴ የኢትዮጵያ ሕጋዊ ገንዘቧ ብር በመሆኑ በጀቷን በአሜሪካ ዶላር አታሰላም ሲሉ መልሰዋል። ይልቁንም በጀቱ ከፍተኛ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
"የበጀት አወቃቀሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለማሳካትም አላማ ያደረገ እና በዚሁ መሠረት ተናቦ የተሠራ መሆኑን ምክር ቤቱ ሊገነዘበው ይገባል"።
መንግሥት 415 ቢሊዮን ብር ለካፒታል በጀት የመደበ ሲሆን ይህ ሀብት በዋናነት የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የሚውል እንጂ ለአዳዲስ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደማይሆን ተጠቅሷል። ይህ በመላ ሀገሪቱ የሚነሱ የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የማህበራዊ ተቋማት እና ሌሎችን የዘነጋ ነው በሚል የካፒታል በጀቱ አንሷል፣ አዳዲ ፕሮጀክትቶችን መገንባት የሚጀመረውስ መቼ ነው የሚል ጥያቄ አስነስቷል።
በተመሳሳይ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ግንባታ 10 ቢሊዮን ብር ብቻ መመደቡ ጥያቄ ቀርቦበታ። እንደተጠበቀው ከውጭ የልማት አጋሮች የታሰበው ሀብት ባለመገኘቱ ይህ ድልድል ዝቅ ማለቱን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
አንድ የምክር ቤት አባል ለመከላከያ ሠራዊት እና ለፌዴራል ፖሊስ አባላት ደሞዝ ሊጨመር ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል። ሆኖም ይህ "በተረጋጋ ሁኔታ ወደፊት የሚታይ ነው" የሚል ምላሽ ተሰጥቶበታል። በሌላ በከል ብዙ በጀት ለምን ለፀጥታ እና ለደህንነት ተቋማት እንዲመደብ ተደረገ የሚል ጥያቄ ቀርቧል።
ለዚህ ጥያቄ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ ምላሽ ሰጥተዋል።"የፀጥታ ሴክተር በጀት ብዙ አይደለም" በሚያስፈልገውም ልክ አይደለም የተመደበላቸው"መንግሥት ይህንን ከፍተኛ ያለውን የ2018 በጀት ለመሰብሰብ ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚገባ እና ይህም "እጅግ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ሥራ" መሆኑ በምክር ቤቱ ተገልጿል።
የክልሎች ድጋፍ 314.7 ቢሊዮን ብር ሆኖ የቀረበ ሲሆን ከፍተኛው የኦሮሚያ ክልል 108.4 ቢሊዮን ብር ነው። ለአማራ ክልል 67.9 ቢሊዮን፣ ለሱማሌ ክልል 31.4 ቢሊዮን፣ ለደቡብ ኢትዮጵያ 22 ቢሊዮን፣ ለትግራይ 18.9 እንዲሁም ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 18.5 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ