1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2021 ዓለም አቀፍ የሮቦት ውድድር አሸናፊው ኢትዮጵያዊ

እሑድ፣ ጥቅምት 14 2014

በቻይና ቤጂንግ በቅርቡ  በተካሄደው የ2021 ዓለም አቀፍ የሮቦት ውድድር በቻይና በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ተሳትፈዋል። ከነዚሀም መካከል በቻይና የዶክትሬት ዲግሪውን በመከታተል ላይ የሚገኘው ሰላሙ ይስሃቅ የተባለ ኢትዮጵያዊ ውደደሩን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ተሽላሚ ሆኗል።

China | Selamu Yishak Gewinner des Weltroboterwettbewerbs 2021
ምስል Selamu Yishak

የ2021 ዓለም አቀፍ የሮቦት ውድድር አሸናፊው ኢትዮጵያዊ

This browser does not support the audio element.

በቻይና ቤጅንግ በቅርቡ በሰውሰራሽ አስተዉሎት እና ለኢንዱስትሪ ስራ አገልግሎት በሚሰጡ ሮቦቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ውድድር ተካሂዷል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በዚህ  ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ከሆነ ኢትዮጵያዊ የቴክኖሎጅ ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርጓል። 
በቻይና ቤጂንግ  በቅርቡ  በተካሄደው የ2021 ዓለም አቀፍ የሮቦት ውድድር  ከተለያዩ ሀገራት የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ  ተወዳዳሪዎች ተሳትፈውበታል።በዚህ ውድድር  በቻይና በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም ተሳትፈዋል። ከተሳተፉት መካከልም በቻይና ቲያንጂን የቴክኖሎጂ እና የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት  አባኩማ ጌታቸው እና ፀጋዬ አለሙ የተባሉ  ሁለት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የብር እንዲሁም ዮሐንስ ኃ/መስቀል እና ሄኖክ ሰይፉ የተባሉ ሁለት ተማሪዎች ደግሞ የነሀስ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።
በዚሁ ዩንቨርሲቲ ላለፉት ሶስት ዓመታት የዶክትሬት ዲግሪውን በመከታተል ላይ የሚገኘው ሰላሙ ይስሃቅ  ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈ ኢትዮጵያዊ ነው።ውድድሩ በተለዩ ዘርፎች የተካሄደ ሲሆን  ሰላሙ የተሳተፈው «Tri Co» በመባል በሚጠራው በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ሮቦቶች ላይ መሆኑን ገልጿል። 
ውድድሩ በአጠቃላይ ሰውሰራሽ አስተዉሎትን መሰረት አድርገው በማምረቻ ኢንዱስትሪ ፣በጤና እንክብካቤና እና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ጥቅም በሚሰጡ ሮቦቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በየደረጃው በተደረጉ ውድድሮች ማጣሪያዎችን ያለፉ 2000 /ሁለት ሺህ /የቴክኖሎጅ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነበር።ባለሙያው እንደሚለው ተሳታፊዎቹ ከትምህርት ቤቶች ፣ከዩንቨርሲቲዎች፣ ከቴክኖሎጅ ማዕከላት እና የዳበረ ልምድ ካላቸው አምራች ኩባንያዎች ጭምር የመጡ በመሆናቸው ውድድሩ ቀላል አልነበረም። ያ በመሆኑ በውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ለራሱና ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ የፈጠረበት የደስታ ስሜት ከፍተኛ ነው።
« እያንዳንዷን ነገር በተግባር ስታሳይ፤ ስለዚያ ጉዳይ አብጠርጥረሽ ሳታውቂ ወደየትም መሄድ አትችይም።በዚያ የተነሳ ውድድሩ አስጨናቂ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሌላ ሀገር ዜጋ ሆነሽ ከእነሱ ጋር ስትወዳደሪ እነሱም የሚሰጡሽ ቦታ አለ። ያን ሁሉ ተቋቁሞ ቴክኖሎጂን አውቀሽ፣ እነሱ በሚሰጡት  ሰዓት  ውስጥ አልያም በተሻሻለ ስዓት ውስጥ ለመጨረስ የምታደርጊው ሩጫ አለ። ያን ሁሉ ስታስቢው አሸናፊነሽን ስታረጋግጭ ያለው ደስታ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው። ዋናው ግን ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ሀገር ሄዶ ከማንኛውም ሰው ጋር፤  ቴክኖሎጂን በተመለከተ ወይም በቴክኖሎጂ ነክ ጉዳዮች ላይ ማወቅ እንደሚችል ፣ ማስረዳት፣ መወዳደር እንደሚችል፣ አሸናፊ መሆን እንደሚችል ማረጋገጡ ትልቅ ነገር ነው። አንድ መሳተፉ ትልቅ ነገር ነው። ከዚያ በዘለለ አሸንፈሽ ስትገኝ ያለው ደስታም ትልቅ ነው። በዚያ  ላይ ደግሞ የሀገራችን ስምና ባንዴራ ስታነሽ ያለው ነገር ደግሞ  በጣም ትልቅ ደስታ ነው።»ሲል ተናግሯል።
የኢትዮጵያውያኑ ማሸነፍ  በተለያዩ የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን እና በቻይና የአፍሪቃ ተጠሪ ባለስልጣናት ዘንድ  ጥሩ ምላሽ ማግኘቱን የገለፀው ሰላሙ፤ኢትዮጵያውያን ንድፈ ሀሳብ ደረጃ ቴክኖሎጅውን የመረዳት ችግር የለባቸውም ይላል።ነገር ግን በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ለመሞከር የቴክኖሎጅ መለማመጃ ዕቃዎች አለመኖር በቴክኖሎጅው ዘርፍ ወደ ፊት ለመራመድ ከፍተኛ ችግር መሆኑን ይገልፃል። በሶስት ዓመት የዩንቨርሲቲ ቆይታዉ ያገኘው የተግባር ዕውቀት ታዲያ ይህንን ችግር በመቅረፍ እሱ ለተወዳደረበት የኢንዱስትሪ ሮቦት ዘርፍ ብቁ እንዲሆን አድርጎታል። ውድድሩ ሶስት የተግባር ደረጃዎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው ስራ የሮቦቱን የተለያዩ ክፍሎች አንድ ላይ መገጣጠም መሆኑን በማብራራት ይጀምራል።
እንደ ባለሙያው የሮቦቱን አፅመ አካል የመገጣጠም የመጀመሪያ ስራ ካጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛውና ቀጣዩ የውድድሩ ስራ  የተገጣጠሙት የሮቦቱ ክፍሎች  ትዕዛዝ እንዲቀበሉ  የሚያደርግ የራሱን ሶፍትዌር የማበልፀግ ስራ ነበር።
የቴክኖሎጅ ባለሙያው ሰላሙ ይስሃቅ እንደገለፀው ከአሁኑ ሽልማት በተጨማሪ ቀደም ሲልም ታዋቂው የቴክኖሎጅ ኩባንያ ሲመንስ በዘንድሮው ዓመት በቻይና ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጅ ክህሎት ውድድር አሸናፊ በመሆንም ሽልማት አግኝቷል። ይህንን ክህሎቱን በመጠቀምም ለወደፊቱ «በኢትዮጵያ የተሰራ» የሚል የቴክኖሎጅ ምርት የማቅረብ  ህልም አለው።
«የእግዚአብሔር ያለው ነው ሚሆነው። እንደ ሰው የማስበው ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ቴክኖሎጂ ሊኖራት ይገባል ነው። በተለይ በሰውሰራሽ አስተውሎትና በኢንዱስትሪ ሮቦት ዘርፍ  ያለው ቴክኖሎጂ። የተጋነነ ፋብሪካ ሳይሆን እነሱን የሚያመርቱ የተወሰኑ ፋብሪካዎችን አስገብቶ ኢትዮጵያ ሰራሽ የሆነ ቴክኖሎጂዎች ማምረት ይቻላል። መፍጠር ይቻላል። ስለዚህ «ሜድ ኢን ኢትዮጵያ»  የሚል ሮቦት ይኖራል ብዬ አስባለሁ። መቶ ፐርሰንት እርግጠኛ ሆኜ ነው የማስበው።በእኔ በኩል ። የመንግስት ፍላጎትና የራሱ የመንግስት አሰራር እንዳለ ሆኖ።ከዚያ ውጭ ግን በቴክኖሎጂው ዘርፍ  አቅማቸው የተገነቡ ሰዎች መፈጠር አለባቸው። ያንን ለመፍጠር ደግሞ የበኩሌን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ።»በማለት አብራርቷል።
በደቡብ ክልል ከንባታ ጠንባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ  ተወልዶ ያደገው ሰላሙ ይስሀቅ ፤የመጀመሪያ ዲግሪውን ከመቀሌ ዩንቨርሲቲ በሂብ ሁለተኛ ዲግሪውን በአስተዳደርና በመረጃ ቴክኖሎጅ  ዘዴ  እንዲሁም ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ  በአመራር እና  አስተዳደር ከኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩንቨርሲቲ አግኝቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቻይና ቲያንጂን የቴክኖሎጂ  ዩኒቨርሲቲ  በሰውሰራሽ አስተውሎትና በአምራች ኢንዱስትሪ ሮቦቶች  ሶስተኛ ዲግሪውን በመከታተል  ላይ ይገኛል።በዚህ የቻይና ቆይታው እንዳስተዋለው ልጆች ተሰጧቸውን እንዲከተሉ ለማድረግ  በወላጆች፣ በትምህርት ቤቶች እና በዩንቨርስቲዎች የሚደረግ ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከቻይና ልትማረው የሚገባ ነው። በመንግስት በኩልም በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቅሶ ቢያንስ የሰለጠነ የሰው ሀይልን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል እና ቴክኖሎጅን የሚደግፍ አሰራር በኢትዮጵያ ሊዳብር እንደሚገባ አመልክቷል። ወጣቶችም በሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ተስፋ ሳይቆርጡ በስራቸው እንዲገፉ መክሯል።
«ወጣቱ በተለይ « ሪጀክት» መደረግን ሳይሰላች፤ ማለፍ የሚገባቸው ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ሁሉን ነገር አልጋ በአልጋ  ሆኖ አይደለም የመጣሁት።እውነቱን ለመናገር ብዙ ፈተናዎችን ታሳልፊያለሽ ። በህይወት መደራደር ሁሉ ሊመጣ ይችላል።  ለሀገር ይጠቅማል ለሰው ይጠቅማል ብለሽ የምታስቢያቸው ነገሮች ከበላይ የሚቀመጠው አካል  በቃ ደፍቆ የመያዝ ኘሮፖዛል የመቀማት ነገር ይኖራል። ነገር ግን ያንን ሁሉ ተቋቁመሽ  ማለፍ ከቻልሽ፤ ፕሮፖዛሉ ይቀማ ሌላ ፕሮፖዛል ሰርቶ መቅረብ። በተለይ ወጣቶች « ክሬቲቭ» የሆኑ ወጣቶች አሉ።  እዚህም ተመርቀው የሚሄዱ ብዙ ወጣቶች አሉ። እነዚህ ሁሉ መስሪያ ይፈልጋሉ። የሚገርመው ወደ ሀገር ቤት የሚሄዱት ሰዎች እዚህ ጥሩ ተከፋይ ናቸው። በነገራችን ላይ በየሀገራቱ ደላሎች አሉ። የቻይናን ቴክኖሎጂው የሚፈልጉ የተለያዩ ሀገራት አሉ። ያንን  ተቋቁመው እነዚህ  ልጆች ሀገር ቤት ሲገቡ እጅ ዘርግቶ የሚቀበል አካል ከሌለ በአንድ በኩል አምልጦ ይወጣና ሌላ ሀገር ተቀጥሮ ይሰራል።ጥሩ እተከፈለ። አገሩን ማገልገል ሲገባ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልጆችም ሃሳባቸውን እዛው ማስረፅ  የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻቹላቸው የቻሉትን ያህል ርቀው መሄድ መቻል አለባቸው። የሰለጠነ የሰው ኃይል ከመጠቀም አንጻርም አመራሩ ትኩረት ቢሠጥ መልካም ነው።» ብሏል።

ምስል Selamu Yishak
ምስል Selamu Yishak
ምስል Selamu Yishak
ምስል Selamu Yishak

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ


ነጋሽ መሀመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW