1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስ

የዘንድሮው የኮርበር የአውሮፓ የሳይንስ ሽልማት አሸናፊ ምርምር

ረቡዕ፣ መስከረም 4 2015

በየዓመቱ በሳይንስ ዘርፍ የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ ተመራማሪዎች ሽልማት የሚሰጠው ኮርበር የአውሮፓ የሳይንስ ሽልማት ድርጅት፤ የ2022 ሽልማትን የህዋስ ተመራማሪ ለሆኑት ፕሮፌሰር አንቶኒ ሀይማን ሰጥቷል።ፕሮፌሰሩ ምርምር የአንጎልን የማስታወስ ችሎታ የሚያስተጓጉሉ አንደ አልዛይመር ላሉ በሽታዎች መንስኤ እና ህክምና ለማግኘት የሚረዳ ነው።

Anthony Hyman
ምስል፦ Friedrun Reinhold

ምርምር የአንጎልን የማስታወስ ችሎታ የሚያስተጓጉሉ በሽታዎች ህክምና ለማግኘት የሚረዳ ነው

This browser does not support the audio element.


በጀርመናዊው ተመራማሪ ኩርት ኮርበርት  የተመሰረተው የኮርበርት የአውሮፓ የሳይንስ ሽልማት ድርጅት የ2022 ሽልማትን በህዋስ ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር ላካሄዱ አንድ የሥነ-ህይወት ተመራማሪ  መስጠቱን በቅርቡ በሀምቡርግ ከተማ ባካሄደው የሽልማት ሥነ-ስርዓት ላይ ይፋ አድርጓል።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ለሽልማት በበቃው አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰናዳ ነው።
በየዓመቱ በሳይንስ ዘርፍ የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ የሳይንስ ተመራማሪዎች ሽልማት የሚሰጠው ኮርበር የአውሮፓ የሳይንስ ሽልማት ድርጅት፤ የ2022 የሳይንስ ሽልማትን የህዋስ ተመራማሪ ለሆኑት ፕሮፌሰር  አንቶኒ ሀይማን ሰጥቷል።
ከ20  ዓመታት በላይ በጀርመን ደረስደን ከተማ የማክስ ፕላንክ የሳይንስ ተቋም በሥነ-ህይወት እና  በህዋስ ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር ሲያደርጉ የቆዩት ብሪታኒያዊው ፕሮፌሰር አንቶኒ ሃይማን ከድርጅቱ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኙት በህዋስ ውስጥ በሚገኙ ፕሮቲኖች ባህሪ ላይ ባደረጉት ምርምር እና አዲስ ግኝት ነው።
ፕሮፌሰሩ በዚህ ምርምራቸው፤ በህዋሳት ውስጥ የሚገኙ ፕሮቲኖች በጥቃቅን ጠብታዎች መልክ በከፍተኛ መጠን በመከማቸት የህዋስን እንቅስቃሴን መቀየር እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

ምስል፦ Friedrun Reinhold

የሀምቡርግ ከተማ የመጀመሪያ  ከንቲባ ዶክተር ፒተር ቸንቸር በሽልማት ሥነ-ስርዓቱ እንደገለፁት ምርምሩ የበሽታዎችን መንስኤ እና ህክምና ለመረዳት ጠቃሚ  ነው። 
«አንቶኒ ሃይማን እና ቡድኑ ህዋሳት፤ የፕሮቲን ጠብታዎችን እንዴት እንደሚፈጥሩ፣  እንዴት እንደሚሰባብሩ  እና እንዴት እንደሚቆጣጠሩ እንዲሁም በእነዚህ ሂደቶች ላይ የሚስተጓጉሉ ነገሮች እንዴት እንደሚስተካከሉ በመመራመር ላይ ናቸው። ከዚህ ጠቃሚ ውጤት የበሽታዎችን መንስኤ እና ህክምና  ምናልባትም ፈወስ ማየት ይቻላል።»
ሃይማን ለDW እንደተናሩት ምርምሩ  ከዚህ ቀደም ብዙም ልብ ባልተባሉ ነገር ግን በቅርፃቸው እና በተግባራቸው ከሰው ልጆች ዘረመል ጋር  ተመሳሳይነት ባላቸው በዓይን በማይታዩ  ክር መሳይ ትላትሎች የተካሄደ ነው።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት በሰዎች ህዋሳት ውስጥ የሚገኙ ፕሮቲኖች በተለምዶ በፈሳሽ መልክ የሚገኙ ናቸው።ነገር ግን  አንቶኒ ሀይማን ባለ አንድ ሴል ጥገኛ ትላትሎችን ተጠቅመው ባደረጉት ጥናት ፕሮቲኖች በህዋስ ውስጥ በጥቃቅን  ጠብታዎች መልክ በከፍተኛ መጠን ሊከማቹ እንደሚችሉም ተገንዝበዋል።ሂደቱንም ከደመና ጋር ያመሳስሉታል።
«ሰማይ ላይ  ደመና የሚፈጠርበትን ሁኔታ ስናስብ፤ እንደ ሙቀት ወይም የአየር ግፊት ለውጥ ያሉ  የውሃ ሞለኪውሎችን  በድንገት እንዲተኑ የሚያደርጉ እና ደመናን የሚፈጥሩ ሂደቶች አሉ። ይህ የትነት ሂደት ህዋስ ውስጥ ከምንመለከተው እሳቤ እና ሂደት ጋር ተመሳሳይ ነው።»   

ምስል፦ OKAPIA KG, Germany/picture-alliance

ነገር ግን  ምርምሩ እንደ አልዛይመር ካሉ በሽታዎች ህክምና ጋር ምን ግንኙነት አለው? ይህንን ለመረዳት ከ20 ዓመት በላይ ወደሰሩበት እና ድሬዝደን ወደ ሚገኘው የማክስ ፕላንክ  የሞለኪውላር ህዋሶች የሥነ-ህይወት  እና የዘረ-መል  ተቋም   ቤተ ሙከራ መመለስንን ይጠይቃል። 
ቡድኑ በቤተሙከራ ውስጥ በአልዛይመር በሽታ ላይ  ሚና የሚጫወተውን  ሰው ሰራሽ  ፕሮቲን ጠጣር የሚያደርግ ንጥረ-ውህድ በመጨመር ወይም የሙቀት መጠንን በመቀየር እና በህዋስ ውስጥ የተለያዩ ሁኔታዎችን በመጠቀም የትኞቹ ምክንያቶች ያልተፈለጉ የፕሮቲን እብጠቶችን ለመፍጠር መንስኤ እንደሆኑ ጥናት አድርገዋል።
በሌላ በኩል ጠጣር ፕሮቲኖችን በንጥረ ውህድ አማካኝነት ወደ ፈሳሽነት በመቀየር በሽታውን ለማከም የሚያስችሉ መድሀኒቶችን ለመስራት የመጀመሪያውን እርምጃ ተጉዘዋል። በዚህ ሁኔታ ቶኒ ሃይማን በሰውነታችን የሚገኙ ህዋሳትን የምንመለከትበትን መንገድ ለውጠዋል።አልዛይመርን የመሳሰሉ የአንጎልን የማስታወስ ችሎታ የሚያስተጓጉሉ በሽታዎች የሚከሰቱት በህዋስ ውስጥ የፕሮቲን ውህዶች በዚህ መልኩ ሲከማቹ መሆኑን ያስረዳሉ ።
« በጤናማ ህዋሳት መዋቅር ውስጥ የፕሮቲን ጠብታዎች  ይገኛሉ። ነገር ግን አልዛይመርን የመሳሰሉ  የመርሳት በሽታዎች በተጠቁ ህዋሳት ውስጥ ጠጣር የፕሮቲን ክምችት ይኖራል። ይህ  ክምችት ተለዋዋጭ ያልሆኑ ፕሮቲኖች የተሰባሰቡበት ሲሆን፤ ልክ እንደ ጠጣር ነገርም አንድ ቦታ ይቆያሉ።»
ሃይማን እንዳሉት በእነዚህ በሽታዎች ከሞቱ ሰዎች በተወሰደ  የናሙና ምርመራ አንጎል ውስጥ የማይንቀሳቀሱ የፕሮቲን ክምችት ተገኝቷል።
 የአልዛይመር በሽታ ባለባቸው ሰዎች «ታው ፕሮቲን» የሚባሉት የፕሮቲን ውህዶች በነርቭ ህዋሳት ውስጥ ይሰባሰቡና ትልቅ ክምችት ይፈጥራሉ። በዚህ ጊዜ ተለዋዋጭ ባህሪያቸውን በማጣት መርዛማ ይሆናሉ። ይህም በአንጎል ውስጥ የነርቭ ህዋሳት እንዲሞቱ በማድረግ በጊዜ ሂደት «ዴሜንሺያ» ለተባለው የመርሳት በሽታ ይዳርጋሉ። የሃይማን ምርምር በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ክምችት ለምን ተፈጠረ ለሚለው መልስ ይሰጣል። በጎርጎሪያኑ 2009  የህዋስ ተመራማሪው አንቶኒ ሃይማን እና ቡድናቸው  ባደረጉት ጥናት  ፈሳሽ ፕሮቲን ወደ ከፊል ጠጣር ንጥረ-ነገር እንደሚቀየሩ በማሳየት ሙሉ ለሙሉ አዲስ የሆነ ሥነ-ህይወታዊ ጉዳይ አግኝተዋል። ይህ የሚሆነውም ህዋሳት  ድንገተኛ የምግብ እጥረት ወይም የሙቀት መጠን መቀነስ ያሉ አካባቢያዊ ጫናዎች ሲያጋጥማቸው  ጠጣር ፕሮቲኖች በመፍጠር አጠቃላይ  እንቅስቃሴን ወደ ማቆም ሊያመሩ ይችላሉ። ይህም ህዋሳት ጠጣር ገፅታ በመፍጠር ራሳቸውን ከውጥረት የሚከላከሉበት ፈጣን ምላሽ  መሆኑን ተመራማሪው ገልፀዋል። የወደፊት ጉጉታቸውም  ሂደቱን  መገንዘብ ነው።
 «የኔ ትልቁ ምኞቴ ህዋሳት እንዴት የጠብታዎችን ባህሪ እንደሚቆጣጠሩ እና ወደ ተሳሳተ መንገድ ሄደው ለምን በሽታ እንደሚያመጡ  መገንዘብ ነው።»

ምስል፦ iLexx/Imago

ተመራማሪው ጥናቱን ያካሄዱት ሰማያዊ ሰማይ ሳይንስ/ Blue-sky science / አንዳንዴም መሰረታዊ ሳይንስ /Basic science/በሚባለው መንገድ ሲሆን ይህም ምርምሩ አንድ የተወሰነ መዳረሻ ወይም ግብ ሳይገድበው ሳይንሱን የበለጠ ለማወቅ በሚመጣ ጉጉት የሚሰራ ነው። በዚህ ሂደት የሂማን ግኝት ተፅዕኖ ህዋሳትን ከሚጎዱ በሽታዎች ምርምር ባሻገር  የህዋሳትን መሠረታዊ ባህሪያት ለመረዳት ያግዛል ። 
በጎርጎሪያኑ  2009 ዓ/ም በሳይንስ መፅሄት ላይ ለህትመት የበቃው ይህ የሃይማን  ፍንጭ ሰጪ ግኝት ምንም እንኳ  ገና በጅምር ላይ ቢሆንም  በህዋስ ሥነ-ህይወት ምርምር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው።በመሆኑም በሽልማቱ ያገኙትን 1 ሚሊዮን ዶላር   ምርምሩን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያውሉት ገልፀዋል።
የአልዛይመር እና ሌሎች ከነርብ ጉዳት ጋር የተያያዙ በሽታዎች  ከእድሜ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የአንጎል ውስጥ ለውጦች፣ ከዘረመል ፣ ከአካባቢያዊ እና ከአኗኗር ዘይቤዎች ጋር ከማገናኘት ውጭ፤ስለ በሽታው ትክክለኛ መንስኤ እስካሁን አይታወቅም። በዚህ የተነሳ የበሽታውን ተጋላጭነት ለመቀነስ  ወይም  በሽታውን ለመከላከል እንዲሁም ለማከም ምንም ዓይነት መንገድ የለም።.
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዚህ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ ቢያንስ 50 ሚሊዮን ሰዎች በአልዛይመር እና ተያያዥ የአንጎል ህዋሳት ህመም ጋር ይኖራሉ። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አዳዲስ  ግኝቶች እና ምርምሮች ካልተደረጉ በ2050 ቁጥሩ ወደ 152 ሚሊዮን ሊያሻቅብ ይችላል። ተመራማሪው ፕሮፌሰር አንቶኒ ሃይማን ግን ተስፋ ሰንቀዋል።
"ለወደፊቱ እጅግ በጣም ጥሩ ተስፋ አለኝ። ምክንያቱም ህዋሳትን  ከፕሮቲኖች ጋር አብረው የማይሰሩ ፈሳሽ ውህዶች አድርጎ ማሰብ እንደማይቻል ግልጽ ነው።ያ ማለት  ቡድን የመመስረት ሥነ-ልቦና ላይ ሳይሰሩ በግለሰብ ደረጃ መንደር ለመፍጠር እንደማሰብ ነው። ስለዚህ እነዚህን ፅንሰ-ሀሳቦች በመጠቀም ህዋሳትን ማጥናት በረዥም ጊዜ ሂደት በመድኃኒት ግኝት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።»

ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW