1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

የ2023 ወጣት የሕዋ መሪዎች ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 2016

ዓለም አቀፉ የጠፈር ተመራማሪዎች ፌደሬሽን /IAF/ ኢትዮጵያዊውን ወጣት ትንሳኤ አለማየሁን በ2023 ዓ/ም ከተመረጡ 5 ወጣት የሕዋ አመራሮች መካከል አንዱ አድርጎ መርጦታል።ወጣቱ በአሁኑ ጊዜ በበጎ ፈቃደኝነት ቬና አውስትሪያ ለሚገኘው የስፔስ ጀነሬሽን አማካሪ ምክር ቤት በርቀት የአፍሪካ አስተባባሪ ሆኖ እየሰራ ይገኛል።

ትንሳኤ አለማየሁ አሊ
ትንሳኤ አለማየሁ አሊ ፤የ2023 ወጣት የህዋሳይንስ አመራሮች ሽልማት አሸናፊ ምስል፦ privat

ወጣቱ ከዚህ ቀደምም በዘርፉ በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል

This browser does not support the audio element.


የዓለም አቀፉ የጠፈር ተመራማሪዎች ፌደሬሽን /IAF/የሚያዘጋጀው ወጣት የጠፈር  መሪዎች /young space leaders/ሽልማት፤ በስራ ዘመናቸው ለጠፈር ምርምሮች አስተዋፅዖ ላደረጉ ወጣት የሕዋ ሳይንስ ባለሙያዎች እውቅና የሚሰጥ መርሃ ግብር ነው። የዘንድሮው/የ2023/ መርሀ ግብር የ25 ዓመቱን ትዮጵያዊ ወጣት ትንሳኤ አለማየሁን፤ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ5 ወጣት የሕዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ሽልማት ሰጥቷል። በደቡብ አፍሪቃ ሆኖ በርቀት ቬና አውስትሪያ ለሚገኘው የህዋ ሳይንስ ትውልድ  አማካሪ ካውንስል /SGAC  /በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገለ የሚገኘው ትንሳኤ፤ እንዲመረጥ ያደረገው  ዘርፉን መቀላቀል ለሚሹ ተማሪዎች እና ወጣት ባለሙያዎች ተነሳሽነትን የሚፈጠር እና በአርአያነት የሚጠቀስ ስራ በመስራቱ ነው።

የዓለም አቀፉ የጠፈር ተመራማሪዎች ፌደሬሽን /IAF/የሚያዘጋጀው ወጣት የጠፈር  መሪዎች ሽልማት፤ በስራ ዘመናቸው ለጠፈር ምርምሮች አስተዋፅዖ ላደረጉ ወጣት የሕዋ ሳይንስ ባለሙያዎች እውቅና የሚሰጥ ነውምስል፦ privat

ከዚህ በተጨማሪ ትንሳኤ እንደሚለው ለፌደሩሽኑ ያበረከተው ስራ ለመመረጡ ሌላው  ምክንያት ነው።ወጣቱ ከ 2019 ዓ/ም ጀምሮ በበጎ ፈቃደኝነት የህዋ ሳይንስ ትውልድ  አማካሪ ካውንስል የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆኖ  ለሁለት ዓመታት ያገለገለ ሲሆን፤በአሁኑ ጊዜም በበጎ ፈቃደኝነት በስፔስ ጀነሬሽን አማካሪ ምክር ቤት የአፍሪካ ክልላዊ አስተባባሪ (SGAC) ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል።
እንደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ተመራማሪዎች ፌደሬሽን በህዋ ሳይንስ እና በምህንድስና ዘርፍ  ትንሳኤ ያሰያቸው አስደናቂ ትጋት እና ውጤታማነት   ቀጣይ የጠፈር ባለሙያዎችን በማብቃት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ወጣት አድርጎታል። ወጣቱ በአማካሪ ምክር ቤቱ /SGAC/ ካለው የሥራ ድርሻ በተጨማሪ በቅርቡ CubeSpace በተባለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ስፍራ በሚይዘው  የሳተላይት  ማምረቻ ድርጅት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሽያጭ መሐንዲስነት እየሰራ ይገኛል።በዚህም በቴክኒክ እውቀቱ እና ልዩ የተግባቦት  ክህሎቱ  የድርጅቱን የንግድ ስራ እያሳደገ እንደሚገኝ ሽልማቱን በሰጠው ዓለም አቀፍ ድርጅት ድረ-ገፅ ላይ የሰፈረው መረጃ ያሳያል።
ትንሣኤ በዘርፉ ላበረከታቸው ልዩ ልዩ አስተዋፅዖዎች ከዚህ ቀደም በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም ከዓለም አቀፉ የጠፈር ተመራማሪዎች ፌደሬሽን (አይኤኤፍ) ተስፋ የተጣለባቸው 30 ወጣት የጠፈር ምርምር መሪዎች መካከል አንዱ ሆኖ ተመርጧል። የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ሽልማት ተቋም በ2021 ከመረጣቸው እድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ከሆኑ  ምርጥ 10 የአፍሪካ የህዋ ምርምር ባለሙያዎች  ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅቷል።ከምርጥ የአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዝርዝር የተካተተው ወጣት

ትንሳኤ CubeSpace በተባለ የሳተላይት ማምረቻ ድርጅት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሽያጭ መሐንዲስነት እየሰራ ይገኛልምስል፦ privat

ለዘርፉ ተመራማሪዎች በሚሰጠው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ መርሃ ግብር  በ2021 አሸናፊ ከሆኑ አምስት የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ውስጥ ከአፍሪቃ የመጀመሪያው ነው። ወጣቱ በ2019 ዓ/ም ደግሞ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የወጣት የሕዋ ሳይንስ አምባሳደርነት እውቅና አግኝቷል።ያም ሆኖ ለአሁኑ ሽልማቱ የተለዬ ቦታ አለው።ከእርሱ ጋር  አብረው የተመረጡት አራቱ  የተለያዩ ሀገራት ተመራማሪዎች በሙያው ጥሩ ስም ያላቸው መሆናቸው ለሽልማቱ ክብደት እንደሰጥ ካደረጉት ምክንያቶች መካከልም አንዱ ነው።

የዘንድሮው/የ2023/ መርሀ ግብር የ25 ዓመቱን ትዮጵያዊ ወጣት ትንሳኤ አለማየሁን፤ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ5 ወጣት የሕዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ሽልማት ሰጥቷልምስል፦ Privat

ትንሣኤ ዓለማየሁ አሊ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ምህንድስና በላቀ ውጤት የተመረቀ ሲሆን የመቀሌ እና   የቤልጄሙ ቶማስ ሞር ዩንቨርሲቲዎች  በጋራ ባያዘጋጁት «ሙን ሹት ኢትዮጵያ» የተባለ ልዩ የትምህርት መርሃ ግብር ተከታትሎም የድርብ ክብር ዲግሪ አግኝቷል።
በቱርክ አንካራ የአቬሽን ቴክኖሎጅ ስልጠናን ጨምሮ ፤በተለያዩ ሀገራት በርካታ ስልጠናዎችንም በመውሰድ፤በአፍሪካ ስፔስ ሳይንስ እና ምህንድስና ዘርፍ ብዙ እውቀትን አካብቷል።በአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተቋም ሰለመገንባት የመከረው አውደ ጥናት
ይህንን እውቀቱን ለሌሎች እኩዮቹ ለማካፈል እና በህዋ ሳይንስ  ዘርፍ ግንዛቤን ለማሳደግ በአዲስ አበባ እና በመቀሌ በርካታ  ስራዎችን መስራቱ የIAF መረጃ ያሳያል። በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ (ESSS) የመቀሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚ በመሆን ወጣቶችን በማሳተፍ ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር የሚያደርግ ስራ ሰርቷል።
ስለሆነም፤ከዓለም አቀፉ የጠፈር ተመራማሪዎች ፌደሬሽን በቅርቡ ያገኘው  እዉቅና ከዚህ ቀደም ለተሰሩ ስራዎቹ ዋጋ ከመስጠቱ ባሻገር ፤እሱን ላፈሩ የትምህርት ተቋማት፣ለወላጆቹ ፣ለሚሰራበት ድርጅት እና ለሀገሩም ትልቅ ውጤት መሆኑን ይገልጻል። ትንሳኤ እንደሚለው ለወደፊቱም በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ተጨማሪ እውቀት እና ልምድ በመሰብሰብ  የሀገሩን  ህዝብ  ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የዕለት ተዕለት ህይወትን የሚያሻሽሉ ተጨባጭ ስራዎችን የመስራት ዓላማ አለው።የዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ፌደሬሽን የ2023 ወጣት የጠፈር መሪዎች  ተሸላሚዎች ምርጫ ባለፈው መጋቢት  በአስመራጭ ኮሚቴው የተከናወነ ሲሆን፤ ከጎርጎሪያኑ ያለፈው ከጥቅምት 2 እስከ 6  በአዘርባጃን ባኩ በተካሄደው 74ኛው ዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጉባኤ  የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ወጣቶቹ ሽልማታቸውን ወስደዋል።

 


ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW