1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

የ2023 የኖቬል ሽልማት አሸናፊ የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ግኝቶች

ረቡዕ፣ መስከረም 30 2016

በዘንድርው የኖቬል ሽልማት በህክምና እና በፊዚዮሎጅ ዘርፍ ለኮቪድ-19 ክትባት የዋለው ኤም አር ኤንኤ ቴክኖሎጅ፤በኬሚስትሪ ዘርፍ በቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ የምንመለከታቸውን ስዕሎች የተሻለ ለማድረግ በሚረዳው ኳንተም ዶት ቴክኖሎጅ ፤በፊዚክስ ዘርፍ ደግሞ አቶሰከንድ የተባለው የኤለክትሮንን በቅፅበት ለማሰስ የሚረዳው ቴክኖሎጅ አሸናፊዎች ሆነዋል።

የኖቬል ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች የላቀ ስራ ለሰሩ ግለሰቦች በየ ዓመቱ የሚሰጥ ሽልማት ነው።
የኖቬል ሽልማት በየ ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጥ ሽልማት ነውምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

የዘንድሮው የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ቴክኖሎጅዎች

This browser does not support the audio element.


የስዊድን ሮያል የሳይንስ አካዳሚ ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ዘርፎች የኖቬል ሽልማት አሸናፊዎችን ይፋ አድርጓል። የዚህ ሳምንት የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ባለፈው ሳምንት በተካደው የኖቬል ሽልማት አሸናፊ የሆኑ የሳይንስ እና የቴክኖሎጅ ግኝቶች ላይ ያተኩራል።
 በየዓመቱ የሚካሄደው እና በተለያዩ ዘርፎች ላቅ ያለ የምርምር ስራ ላበረከቱ ግለሰቦች ሽልማት የሚሰጠው የኖቬል ሽልማት ኮሚቴ በተለያዩ ዘርፎች አሸናፊዎችን  ያለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።በዘንድርው የኖቬል ሽልማት  በህክምና እና በፊዚዮሎጅ ዘርፍ  በኮቪድ-19 ክትባት ኤም አር ኤንኤ የተባለ -/messenger RibioNucliec Acid/  የተባለ የተለዬ ቴክኖሎጅ ላበረከቱ ሁለት ሳይንቲስቶች ሰጥቷል።
ኤም አር ኤንኤ ፕሮቲኖችን ለመስራት መመሪያዎችን የያዘ ነጠላ ሞሎኪዩል ሲሆን፤የኮቪድ-19  በሽታን ለመከላከል  የሚያገለግሉ  ክትባቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማበልፀግ ጥቅም ላይ የዋለ ቴክኖሎጅ ነው። የዚህ ክትባት  ምርምር መሠረት የተጣለው በአሁኑ ጊዜ በሃንጋሪ ዩኒቨርስቲ  ፕሮፌሰር በሆኑት ዶ/ር ካታሊን ካሪኮ እና በአሜሪካ ፔንሲልቬኒያ ዩኒቨርስቲ  ፕሮፌሰር ሆነው እያገለገሉ በሚገኙት ዶ/ር ድሪው ዋይዝማን ነው።

ካትሪን ካርኮ እና ድሪው ዋይዝማን፤ በህክምና እና በፊዚዮሎጅ ዘርፍ የ2023 የኖቬል ሽልማት አሸናፊዎችምስል፦ JONATHAN NACKSTRAND/AFP

ይህ ምርምራቸውም ሁለቱን ሳይንቲስት በህክምና እና የፊዜዮሎጅ ዘርፍ የዘንድሮው ዓመት የኖቬል ተሸላሚ አድርጓቸዋል። የኖቬል ሽልማት ኮሚቴው ሁለቱን ሳይንቲስቶች ይፋ ሲያደርግ በሰጠው መግለጫ «በሰው ልጅ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ላጋጠመው ከፍተኛ የጤና ስጋት ሁለቱ ተሸላሚዎች ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ክትባት በማዳበር  አስተዋጽኦ አበርክተዋል» ብሏል።
ያም ሆኖ የኖቬል ተሸላሚዋ ፕሮፌሰር ካትሊን ካሪኮ ውጤታማነቱ በቀላሉ ተቀባይነት እንዳለገኘ ያስታውሳሉ።
ካትሊን ካሪኮ የኖቤል ተሸላሚ «እኔ የተረዳሁት እውቀት ስለሌላቸው በቃ ዝም ብለው ያምኑ ነበር። ስለዚህ ክትባቱ በጣም አስተማማኝ እና በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ብቻ እመኑኝ እያልኩ እነግራቸው ነበር። እናም ሌሎች ተጨማሪ ክትባቶች ይኖራሉ  ሁሉም ለሰዎች በጣም ጠቃሚ ይሆናሉ አላቸው ነበር።»
ሁለቱ ሳይንቲስቶች ከጎርጎሪያኑ 1990ዎቹ ጀምሮ በአሜሪካው ፔንሲልቬኒያ ዩንቨርሲቲ በኤምአርኤን ላይ ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። የበሽታን መከላከያ ክትባቶች በተለምዶ የሚዘጋጁት ከሞቱ ወይም ከተዳከሙ  ተዋህሲያን ወይም ባክቴሪያዎች  ነው።ተሸላሚዎቹ ሳይንቲስቶች ካሪኮ እና ዌይስማን  ግን ኤምአርኤንኤ የተባለውውን ቴክኖሎጂ የፈጠሩት  ከተለመደውየክትባት አሰራር ፈጽሞ በየተለየ መንገድ ነው።

የኤምአርኤንኤ ክትባቶች በሰውነት ውስጥ በሽታውን ለሚመስሉ ለተወሰኑ ፕሮቲኖች መመሪያ በመስጠት የሰውነት የበሽታ መከላከያ ስርዓት ከትክክለኛው ተዋህሲ ጋር. እንዲዋጋ የሚያሰለጥኑ ናቸው።ይህ ቴክኖሎጂ በሰው ልጆች ዘረ መል ላይ ያሉ መረጃዎችን ተንትኖ ለመረዳት የሚያስችልም ነው። የሚገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግም የሰው ልጅን የሚያጋጥሙ የጤና ጠንቆችን በዝርዝር በመረዳት፣ ተፈጥሯዊው በሽታን የመከላከያ ሥርዓት የበሽታ አምጭ ተዋህሲያንን ለመዋጋት እና ለማጥፋት የሚያስችለውን አቅም  እንዲያዳብር ያደርጋል።
የፕሮፌሰር ካሪኮ እና ዊስማን  የምርምር ውጤት የተገኘው በጎርጎሪያኑ 2005 ዓ/ም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ ከ15 ዓመታት ቀደም ብሎ ነው። ቴክኖሎጂው  ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት በሙከራ ደረጃ ላይ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ኮቪድ-19ን ለመከላከል እንዲከተቡ ተደርጓል።ስለሆነም ጥቅም ላይ የዋሉት ሞደርና ፣ ፋይዘር እና ባዮንቴክ ክትባቶች የዚሁ ቴክኖሎጂ  ውጤቶች ናቸው።

የኖቬል ተሸላሚው ፕሮፌሰር ድሪው ዋይዝ ማን እንደሚሉት ይህ  ቴክኖሎጂን ከኮቪድ ባሻገር ፤ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከልም ትልቅ አቅም አለው።  
«የ ኤም አርኤን ኤ  ክትባቶች በአጠቃላይ  በበርካታ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክሊኒካዊ ሙከራዎች ተደርጓል ።  ለምሳሌ በሳይስቲክ ፋይብሮሲስ፣ በተለያዩ የጉበት በሽታዎች፣በሲክል ህዋስ በሚባለው የደም ማነስ በሽታ ላይ ክሊኒካዊ ሙከራዎች አሉ። ስለዚህ ታውቃላችሁ፣ ያለው አቅም በጣም ትልቅ ነው።»
ከዚህ በተጨማሪ የኤም አር ኤን ኤ ቴክኖሎጂ በአሁኑ ጊዜ ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎች በሽታዎች ጥቅም ላይ ለማዋል ምርምር እየተካሄደበት ሲሆን፤እንደ ሜላኖማ በመሳሰሉ አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶችም ጥሩ የሚባል የመጀመሪያ ደረጃ  ውጤቶችን አሳይቷል።
የኳንተም ዶት ፤በኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቬል አሸናፊው ቴክኖሎጂ  

ሌላው የዚህ ዓመት የኖቬል ተሸላሚ ዘርፍ የኬሚስትሪ ዘርፍ ሲሆን፤የዘንድሮው የኬሚስትሪ የኖቤል ሽልማት በቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ የምንመለከታቸውን ስዕሎች የተሻለ ለማድረግ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ምርምር ላደረጉ  ሳይንቲስቶች ተሰጥቷል።ተሸላሚ ሊቃውንቱ ማውንጊ ባውንዲ ፣ ሉዊስ ብሩስ እና አሌክሲ ኤኪሞቭ  ይባላሉ። ሶስቱ ሊቃውንት በኬሚስትሪ ዘርፍ የዘንድሮ /የ2023/የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት «ኳንተም ዶት» በተባለ ቴክኖሎጅ ላደረጉት ምርምር እና ግኝት ነው።
የኳንተም  ነጠብጣቦች/የኳንተም ዶት/፣ በከፊል ኤሌክትሪክን የሚያስተላልፉ ትንንሽ ሰው ሠራሽ ክሪስታሎች ናቸው። ክሪስታሎች በቴሌቪዥን መስኮቶች እና በ LED መብራቶች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላሉ።ጀርመናዊው የስነ ፈለክ ተመራማሪ ራየንሃርት ጌንዝልና ግኝቶቻቸው

የ2023 በኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቬል ሽልማት አሸናፊዎችምስል፦ Jonathan Nackstrand/AFP

የስዊድን የኖቬል ኮሚቴ ሦስቱን ሳይንቲስቶች ደማቅ ብርሃን እና የተለያዩ ቀለሞችን ለመልቀቅ በሚያስችሉ ቅንጣቶች ላይ ላደረጉት ስራ እውቅና ሰጥቷል። የ2023 የኬሚስትሪ የኖቬል ኮሚቴ ሀይነር ሊንከ ተሸላሚውን ቴክኖሎጅ እንዲህ ነበር የገለፁት።«ስለ ኳንተም ነጠብጣቦች ዋናው ነገር መጠናቸውን በመቀየር ጥቂት መቶ አተሞችን ወይም በአንድ አቶም ንብርብር ላይ እንደገና የበለጠ የአተም ንብርብር በመጨመር ባህሪያቸውን ለምሳሌ ቀለማቸውን መለወጥ ነው።»

የኬሚስትሪ ኖቤል ኮሚቴ ሊቀመንበር  ጆሃን አክቪስት እንዳሉት የኳንተም ነጠብጣቦች ብዙ አስደናቂ እና ያልተለመዱ ባህሪያት ያሏቸው እና እንደ መጠናቸው የተለያየ ቀለም ያላቸው ናቸው።
የኳንተም ነጠብጣቦች መጠናቸው ከ2-10 ናኖሜትሮች አካባቢ የሚሆኑ እና ከፊል ኤለክትሪክ አስተላላፊ በጣም ጥቃቅን ክሪስታሎች ናቸው።
እነዚህ ነጠብጣቦች  ተመሳሳይ መዋቅር ያላቸው እና መጠናቸውን በመቀየር ብቻ ባህሪያቸውን ሙሉ በሙሉ ሊለውጡ የሚችሉ ናቸው። ትንንሽ ነጠብጣቦች ሰማያዊ ብርሃን ሲያመነጩ፤ ትልልቆቹ ነጠብጣቦች ደግሞ ቀይ እና ቢጫ ቀለሞችን እንዲያመነጩ ተደርገው የተሰሩ ናቸው። በዚህ መልኩ  የኳንተም ነጠብጣብ ቴክኖሎጂዎች በቴሌቪዥን እና በኮምፒውተር ስክሪኖች ላይ ይበልጥ ብሩህ  እና ትክክለኛ ቀለሞችን እንድናይ ያረዱናል።

ሊቃውንቱ ግኝቱን መስራት የተቻሉት ኳንተም መካኒክ በተባለው ዘዴ መሆኑን የኖቬል ኮሚቴው ያስረዳሉ።«ለምሳሌ ያህል ቲሸርትህን፣ ቀይ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ወይም ሰማያዊ አድርገህ ማቅለም ትፈልጋለህ ብለን እናስብ። የተለያዩ ቀለሞች እንዲሰጡህ ለእያንዳንዳቸው የተለያዩ ሞለኪውሎችን እና የተለያዩ አተሞችን ለእነዚህ ቀለሞች መጠቀም ያስፈልጋል።በኬሚስትሪ የሚሆነው ነገር ይህ ነው። ነገር ግን በኳንተም ነጠብጣቦች  ውስጥ ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ  ተመሳሳይ አተሞችን በመጠቀም መጠኑን መለወጥ ይቻላል። ምንም ያህል አቶሞች ቢኖሩህም አዳዲስ ቀለሞችን እና  ሌሎች አዳዲስ ባህሪያትን ታገኛለህ።»
ከዚህ አንፃር  ዘመናዊ ኮምፒዩተሮች እና ቴሌቪዥኖች የእያንዳንዱን ፒክሰል ቀለም ለመፍጠር የኳንተም ነጠብጣቦች አስተዋፅኦ አላቸው።ጥቅሙ ግን ያ ብቻ አይደለም።ለወደፊቱም ተጣጣፊ የኤለክትሪክ ዕቃዎችን፣ አነስተኛ ሴንሰሮችን እንዲሁም የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ለማሻሻል ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። ለተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች ፀረ-ካንሰር መድኃኒቶችን ማድረስ ያስችላል። .ቴክኖሎጂ በባዮሜዲካል ምርምር ውስጥ ሞለኪውሎችን በምስል ለማሳየት እንደሚያገለግልም የ2023 የኬሚስትሪ የኖቤል ኮሚቴ ፐርኒላ ዊቱንግ-ስታፍሼዴ  ይገልፃሉ።
«በህክምና የካንሰር ዕጢዎችን ለመለየት የኳንተም ነጠብጣቦችን እንጠቀማለን። ለምሳሌ እብጠቱ ላይ ማነጣጠር እና ከሆነ ነገር ጋር ማገናኘት ትችላለህ። ከዚያም  እዚያው ቦታ ላይ ብርሃን በማብራት ዕጢው የት እንዳለ ማየት ትችላለህ።»ሁለቱ የ2021 የኖቤል ተሸላሚ ጀርመናውያን ሊቃውንት

አቶሰከንድ ፤በፊዚክስ ዘርፍ አሸናፊው ግኝት

ሌላው የኖቬል ሽልማት ዘርፍ የፊዚክስ ዘርፍ ነው። ፒየር አጎስቲኒ፣ ፌሬንክ ክራውዝ እና  አን ኤል ሁሊየር የዘንድሮ የፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ናቸው።ሶስቱ የሳይንስ ሊቃውንት ሽልማቱን በጋራ የወሰዱት በአተም ውስጥ ያለውን የኤሌክትሮን ዓለም  በትንሽ ሴኮንዶች በቅፅበት ለማሰስ የሚረዱ  መሳሪያዎችን በማበለፀጋቸው ነው።
የሮያል ስዊድን የሳይንስ አካዳሚ ዋና ፀሃፊ ሃንስ ኤሌግሬን እንዳሉት የሊቃውንቱ ስራ በቁስ አካል ላይ የኤሌክትሮን ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ለማጥናት በ«አቶሰከንድ»በሚባሉት ሽርፍራፊ ሰከንዶች የብርሃን ፍንጣቂዎችን የሚያመነጩ የሙከራ ዘዴዎችን አስገኝቷል.።
ይህ ምርምር እጅግ በጣም አጭር በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ምን እንደሚፈጠር እንድንገነዘብ ከመርዳቱ በተጨማሪ ኤሌክትሮኒክስን በጣም ፈጣን እና ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም የበሽታዎችን ምርመራ ለማሻሻል እንደሚረዳ የኖቬል ኮሚቴው ገልጿል።

የ2023 በፊዚክስ ዘርፍ የኖቬል አሸናፊ ሊቃውንት ፤ፔሬ አውጉስቲን፣ፍሬንክ ክራውዝ እና አነ ሊ ሁለር ምስል፦ Anders Wiklund/TT News Agency/REUTERS

«በደም ሴል ውስጥ በጣም ትንሽ እና  ጥንቃቄ የሚያሻው ለውጥ ካለ እና ያ ለውጥ  በበሽታ ምክንያት መሆኑን  መገንዘብ ከቻልን ትልቅ ጥቅም አለው።ያ ማለት በሽታውን በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ስር ሳይሰድ ማወቅ የምንችልበት ዘዴ አለን ማለት ነው።ለምሳሌ የሳንባ ካንሰር።የአክቶ ሰከንድ ቴክኖሎጅ አለን ማለት ይህንን ለጥንቃቄ  ለማድረግ ይረዳናል ማለት ነው።»
«አቶሰከንድ»በጣም አጭር  የጊዜ መለኪያ ሲሆን፤ «አንድ አክቶ ሰከንድ /Attosecond /አንድ ሰከንድ ነው። እንደ አንድ ሰከንድም የአጽናፈ ዓለም ዕድሜ ነው።አንድ ሰከንድ የልብ ምት የሚቆይበት ጊዜ ያህል ነው።»በማለት ነበር ኮሚቴው ያለፈው ማክሰኞ የኖቤል ሽልማቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ውስብስቡን ፅንሰ ሀሳብ ለማስረዳት ሞከረው።
ሦስቱ የኖቤል ተሸላሚዎች በምርምራቸው ለሰከንዶች ብቻ/Attoseconds/ የሚቆዩ የብርሃን ፍንጣቂዎችን ማምረት ችለዋል። እነዚህ ፍንጣቂዎች በአተሞች እና በሞለኪውሎች ውስጥ ምን እንደሚከናወን ምስሎችን ለማቅረብ ሊያገለግሉ ይችላሉ ተብሏል።

ሙኒክ ጀርመን በሉድቪግ-ማክስሚሊያንስ-ዩንቨርስቲ  ፕሮፌሰር የሆኑት ዮርግ ሽራይበር እንደሚሉት ይህ ምርምር ከዚህ በፊት  ተደራሽ ያልሆነ ዓለምን ክፍት እንዲሆን አድርጓል። 
የ2023 የፊዚክስ የኖቤል ተሸላሚዎች ጥናታቸውን የሰሩት በተናጠል ሲሆን፤ ኤል ሁሊየር በጎርጎሪያኑ 1980ዎቹ ፣አጎስቲኒ እና ክራውዝ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ  ምርምራቸውን ሰርተዋል።
አጎስቲኒ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር፣ ክራውስዝ ጀርመን በሚገኘው የማክስ ፕላንክ የኳንተም ኦፕቲክስ ተቋም ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ ኤል ሁሊየር ደግሞ በስዊድን የሉንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ናቸው።
ኤል ሁሊየር በዘርፉ ሽልማት ያገኙ አምስተኛዋ ሴት የፊዚክስ ሊቅ ናቸው።

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW