1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ33 የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማሕበራት ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 27 2015

"በበቂ ሁኔታ ምርመራዎች ተደርገዋል፣ የደረሱት የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ተደርጎ ተመዝግቦ ተቀምጧል ብለን አናምንም። ምርመራ በበቂ ሁኔታ ተደርጓል የሚሉ አካላት አሉ። የባለሙያዎቹ ቡድን ኮሚሽን ኃላፊነቱን እየተነጠቀ ሥለሆነ ፣ ስልጣኑን መነጠቁ አግባብ አይደለም።"

የሂውማን ራይትስ ወች ምልክት
ምስል John MacDougall/AFP/Getty Images

የ33 የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማሕበራት ተቃውሞ

This browser does not support the audio element.

ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በስድስት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 33  የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማሕበራት የአፍሪካ የሰብዓዊና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል በጦርነቱ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ያቋቋመው ኮሚሽን እንዲበተን መወሰኑን በመቃወም ጉዳዩ ዳግም እንዲጤን ጠየቁ።
የድርጅቶቹ ተቃውሞ በሂደት በአፍሪካ በሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ላይ በሚከናወኑ የምርመራ ሥራዎች ላይ ዐሉታዊ ውጤት ያስከትላል የሚል እና የደረሱ የመብት ገፈፋዎች በበቂ ሁኔታ ተመርምረው አላበቁም ከሚል እምነት የመነጨ መሆኑ ተገልጿል።
በአፍሪካ ሕብረት ሥር ያለው የአፍሪካ የሰብዓዊና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን በመተግበር በጦርነቱ ለደረሰው ጉዳት መፍትሔ ለመስጠት አቋም መያዙን መግልፁን እና በትግራይ ክልል ሰላም እየሰፈነ መሆኑን ለመርማሪ ኮሚሽኑ መበትን ምክንያት አድርጎ ጠቅሷል።
ተቃውሞ ያሰሙት ድርጅቶች ኮሚሽኑ ውሳኔውን ቆም ብሎ እንዲያጤነውና እንዲበተን የተወሰነበት መርማሪ አካል ሥራውን እንዲቀጥል ግልጽ ጥሪ አድርገዋል።

የአፍሪካ የሰብዓዊና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ያለውን የመብት ጥሰት ምርመራ ለምን አቋረጠ ?

የአፍሪካ የሰብዓዊና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት የተፈፀሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ያቋቋመው ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነትን በማቆም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ተጠያቂነትን፣ እውነትን ማውጣትን፣  ለተጎጂዎች መፍትሔ እና እርቅ እንዲሁም ማገገም ላይ ያትኮረ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ለማፅደቅ በሂደት ላይ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ መርማሪ ኮሚሽኑ ሥራውን እንዲያቋርጥ መወሰኑን አስታውቋል። ይሁንና በአገሪቱ ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብት ሁኔታ መከታተሉን እንደሚቀጥልም ገልጿል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በዋናነት በሂውማን ራይትስ ዎች አስተባባሪነት በስድስት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 33  የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማሕበራት ውሳኔውን ተቃውመውታል።
ውሳኔው ኮሚሽኑ ከተቋቋመለት አላም እንፃር የሚቃረን መሆኑን የገለፁት እነዚህ ድርጅቶችና ማሕበራት ለውሳኔው ምክንያት ተብሎ የቀረበው ገዳይም አሳማኝ አይደለም ብለዋል።
33ቱ የሰብዓዊ ምብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማሕበራት በትግራይ ክልል ስለተፈፀመው የመብት ጥሰት ሌሎች ገለልተኛ መርማሪ አካላት የሚያደርጉትን የምርመራ ሥራም የሚያደናቅፍ ነው በሚል በብርቱ ተችተውታል።
ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነውና በኢትዮጵያ የተመዘገበው የመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ በፍቃዱ ኃይሉ ድርጅቶቹ ውሳኔውን በመቃወም ለምን ደብዳቤ እንደፃፉ ለ ዶቼ ቬለ አብራርተዋል።

የመብት ድርጅቶች ያሰሙት ተቃውሞ ምክንያቱ ምንድን ነው?

ለተቃውሞአቸው ያስቀመጡት ምክንያት "በበቂ ሁኔታ ምርመራዎች ተደርገዋል፣ የደረሱት የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ተደርጎ ተመዝግቦ ተቀምጧል ብለን አናምንም። ምርመራ በበቂ ሁኔታ ተደርጓል የሚሉ አካላት አሉ። የባለሙያዎቹ ቡድን ኮሚሽን ኃላፊነቱን እየተነጠቀ ሥለሆነ ፣ ስልጣኑን መነጠቁ አግባብ አይደለም። በኢትዮጵያ ያለው የፍትሕ ጥያቄ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት ውስጥ የገለልተኛ ወገኖች ምርመራ ይፈልጋል የሚል እምነት ስላለን ነው" ብለዋል።
መንግስት አጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት ለማስፈን እሰራለሁ ማለቱን ከገለልተኝነት አንፃር ተቀባይነት እንደሌለው ድርጅቶቹ እና ማሕበራቱ ጠቅሰዋል። እንዲበተን የተወሰነበት ኮሚሽኑ በጦርነቱ የተሳተፈው እና በሰው ልጆች ላይ በተፈፀመ ወንጀል እና በጦር ወንጀል ክስ የሚቀርብበት ያሉት መንግሥት ፍትሕ ይሰጣል በሚል በአፍሪካ የሰብዓዊና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን የተሳሳተ ትርክት በመያዙ የመጣ ነው ብለው እንደሚያምኑም ገልፀዋል። ይህ የመርማሪ ኮሚሽኑ ለፖለቲካ ውሳኔ ሰለባ የመሆኑ ማሳያ አድርገው እንደሚወስዱትም ለኮሚሽኑ በፃፉት ደብዳቤ ገልፀዋል።

ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በስድስት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 33 የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማሕበራት የአፍሪካ የሰብዓዊና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል በጦርነቱ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ያቋቋመው ኮሚሽን እንዲበተን መወሰኑን ተቃውመውታል።ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

ሰሎሞን ሙጬ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW