1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ36ኛው የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ትኩረት

ሰኞ፣ የካቲት 13 2015

36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ቅዳሜ እና እሑድ ተካሂዶ ተጠናናቀቀ። ጉባኤው ሲያበቃ በተሰጠው መግለጫም የተነጋገረባቸው አበይት ነጥቦች ይፋ ሆነዋል። ጉባኤው ከሁሉም የዓለም ዳርቻ አዲስ አበባ በመጡ 800 ጋዜጠኞች የዘገባ ሽፋን ማግኘቱ ተገልጿል።

Äthiopien | AU Gipfel in Addis Ababa
ምስል Solomon Muchie/DW

ቅዳሜ እና እሑድ ጉባኤው ተካሂዷል

This browser does not support the audio element.


ከ 600 ሚሊዮን በላይ አፍሪቃውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማያገኙባት አፍሪቃ «ነፃ የንግድ ቀጣናን» እንዴት በፍጥነት መተግበር ይቻላል የሚለው የዚህኛው ዓመት የመሪዎቹ ዋነኛ መወያያ ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘም እየተባባሰ ነው የተባለው የክፍለ ዓለሙ የሰላም እና ፀጥታ መናጋት ፣ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጦች እና ሽብርተኘትን አስመልክተው ተወያይተዋል።
የሕብረቱን የመሪነት ኃላፊነት የደሴት ሀገሯ ኮሞሮስ ከሴኔጋል ተረክባለች። አዲሱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሶማኒ የነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራው «የተለጠጠ እቅድ ቢሆንም" እናሳካዋለን» ብለዋል፤ ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ትናንት ሌሊት በሰጡት መግለጫ። ክፍለ ዓለም አፍሪቃ በሀብት የተሞላ መሆኑ ደግሞ የተስፋቸው ምንጭ ሆኗል። ያም ሆኖ ግን ቀላል ሥራ እንደማይጠብቃቸው የሚገነዘቡት ሊቀ መንበሩ «ያለ ሰላምና መረጋጋት ልማትን ማስፈፀም ስለማይቻል በእኔ የአመራር ጊዜ ለሕብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ይደረጋል» ነው ያሉት።
የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለውን አደጋ፣ በምግብ ራስን ያለመቻ ችግሮች ትኩረት የሚያስፈልጋቸው አንገብጋቢ የሕብረቱ የሥራ መስኮች እንደሚሆኑና የባሕር በር እና የመርከብ አገልግሎት ደህንነትን ማስጠበቅ መሠረታዊ የሥራ አቅጣጫ ሆነው እንደሚቀጥሉም ይፋ አድርገዋል።የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ተጀመረ
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማትም እንዲሁ ንግድንና ግብይትን ማሳለጥ የግድ ስለመሆኑ ፣ ለዚህ ደግሞ ነፃ የዜጎች እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ የሚያስችሉ መሠሰረተ ልማቶችን መገንባት እንደሚያሻ ፣በአህጉሩ በሚታየው ያመረጋጋትን በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት መረባረብ እንደሚገባና መሪዎቹ በዚህ ላይ በስፋት መምከራቸውንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል እስራኤል በሕብረቱ የታዛቢነት ሚና እንዲኖራት ጥያቄ መቅረቡን አስታውሰው ባለፈው ዓመት መሪዎቹ እንደተወያዩበት፣ ይህንኑ ጉዳይ የሚመረምር ኮሚቴም መቋቋሙን እና ጉዳዩ በተዋቀረው ኮሚቴው እስኪታይ ድረስ ለጊዜው ስለመታገዱ አስታውቀዋል።
«በመሆኑም በዚህ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፍ የጋበዝነው የእስራኤል ባለሥልጣን የለም። ሆኖም አዲስ አበባ ላይ ተቀማጭ ያልሆኑ ሰው ወደ አዳራሽ በመግባታቸው እንዲወጡ አድርገናል። ግለሰቧ እንዴት ያንን የመግቢያ ፈቃድ እንዳገኙ ምርመራ እያደረግን እንገኛለን።» በማለት ወደፊት መሪዎቹ ተቀምጠው ሲወስኑ ግን እስራኤል በሕብረቱ የታዛቢነት ሚና ሊኖራት እንደሚችል ገልፀዋል። አሁን ግን ጉዳዩን አስመልክቶ በሕብረቱ የተወሰነ ምንም ነገር አለመኖሩን አብራርተዋል።
አዲሱ የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር አዛሊ ኮሞሮስ ለዚህ ኃላፊነት መብቃቷን የሕብረቱ ፍትሐዊነት ማሳያ አድርገው ጠቅሰዋል። አባል ሃገራቱ ለሰላም እና ፀጥታ ሥራዎች የሚያደርጉት መዋጮ በቂ አለመሆኑን፣ በአፍሪቃ የሚታየው የፀጥታ ችግር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጋራ ሥጋት ጭምር መሆኑን በማመን ድጋፍ እንዲያደርግም ይጠበቃል ብለዋል።

36ኛው የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ በአዲስ አበባምስል Solomon Muchie/DW

«የአፍሪቃ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ለብዙ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል ። ያንን ማድረግ ካለብን ግን ፀጥታ እንፈልጋለን ። ውጤታማ በሆነ መንገድ ከመጣን በኋላ ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድል መፍጠር እንችላለን። ሙሳ እንደተናገሩት ሽብርተኝነት እንዲሁ ሀገር በቀል ችግር ብቻ አይደለም። ታዲያ ይህን ስጋት እንዴት እንፈታዋለን? ወጣቶች በእነዚህ አሸባሪዎች እንዳይቀጠሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለብን። ግን ይህንን ሁሉ እንዴት መቆጣጠር እንደምንችል ማየት አለብን። ሆኖም ይህ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ነው።»
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዓለም በበርካታ ውስብስብ ችግር ውስጥ መሆኗን፣ በርካታ  አፍሪቃውያን የዚህ ችግር ቀዳሚ ሰለባ መሆናቸውን በማመን ከአህጉር እና ህዝቡ ጋር ያላቸውን ትብብር እና ግንኙነት ለማጠናከር አዲስ አበባ መምጣታቸውን ገልፀዋል።
አፍሪቃ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት የገለፁት ጉቴሬዝ ተቋማቸው የ250 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉንም አብስረዋል። አፍሪቃ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውክልና ይኑራት የሚለውን ሀሳብም ደግፈው ታይተዋል። የአፍሪቃ ሕብረት ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤትን ለማጠናከር ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል። አፍሪቃ የፀጥታው ምክር ቤት አባል እንድትሆን በሕብረቱ የቆየ አቋም ስለመያዙ እና የተቋሙን ምላሽ ተጠይቀው ሲመልሱም፤

በ36ኛው የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ላይ የተገኙት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ምስል Solomon Muchie/DW

«ይህ በአባል ሀሃራቱ የሚወሰን ጉዳይ ነው። ከዋና ጸሐፊው ሥልጣን በላይ ነው። ሆኖም እኔ እንደማምነው በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አለ የሚባል ኢ-ፍትሐዊነት ካለ አፍሪቃ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ የቋሚ አባል ሃገራት ውስጥ ያለመካተቷ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ የፀጥታው ምክር ቤት በሚቋቋምበት ወቅት ከቅኝ ተገዢነት ነፃ የነበሩ የአፍሪቃ ሃገራት ጥቂት ስለነበሩ ነው። ስለዚህ አፍሪቃ ሁለት ጊዜ ተጎጂ ሆናለች። አንደኛ በቅኝ ግዛት መገዛቷ ፣ሁለተኛ ደግሞ በፀጥታው ምክር ቤት ተወካይ ባለመሆኗ። ሆኖም ግን ብዙ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሃገራት የናይትድ ስቴትስ፣ ራሺያ እና ቻይናን ጨምሮ እንዲሁም እንደማምነው እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በፀጥታው ምክር ቤት ቢያንስ አንድ የአፍሪቃ ቋሚ ተወካይ እንዲኖር ስምምነት እንዳላቸው መግለፃቸውን ነው። ይህም ማለት ይህ ጉዳይ ይተገበራል የሚል ተስፋ አለ ማለት ነው።»
በጉባኤው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት የገቡበትን ጦርነት በሰላም መፍታታቸው «ለአፍሪቃዊ ችግሮች አፍሪቃዊ መፍትሔ» የሚለው መርህ ማሳያ ነው በሚል ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ጉባኤው ከሁሉም የዓለም ዳርቻ አዲስ አበባ በመጡ 800 ጋዜጠኞች የዘገባ ሽፋን አግኝቷል ተብሏል።
ለጉባኤው የመጡ እንግዶችም ከትናንት ምሽት ጀምሮ ወደየሀገራቸው እየተመለሱ ሲሆን ጉባኤው «ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን» የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል ።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW