1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ «90´s ልጆች» የፌስ ቡክ ትዝታዎች

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 3 2012

የ «90´s ልጆች» ከቅርብ ወራት አንስቶ በኢትዮጵያዉያን የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ ዝና ያተረፈ የፌስቡክ ቡድን ነው። ከተከፈተ ገና ሶስት ወር ሳይሆነው ከ 300ሺ በላይ ተከታዮች አሉት።

Äthiopien Facebook Gruppe "Kinder der 90er"
ምስል Leyou Amare

የ «90´s ልጆች»

This browser does not support the audio element.

የ90ዎቹ ልጆች የተሰኘው የፌስ ቡክ ገፅ ላይ በብዛት የትምህርት ቤት ገጠመኞች፣ የድሮውን ጊዜ የሚያስታውሱ ፎቶዎች እና ትዝታዎች በሰፊው ይንሸራሸራሉ። ልዩ አማረ የዚሁ ቡድን መስራች እና የአስተዳደሩ አካል ናት። « ጨዋታዎቻችን፣ ሙዚቃዎቻችን ፣ ንግግሮቻችን የተጠቀሱት ነገሮች እኛን የ90ዎቹን ልጆች ይገልፁናል» ትላለች። ልዩ የ «90´s ልጆች» የምትላቸው በጎርጎሮሲያኑ የዘመን አቆጣጠር የ90ኛቹ የሚባሉትን እና በኢትዮጵያ አቆጣጠርም የ90ዎቹ የሚባሉትን በጠቅላላው 20 ዓመታትን ያቀፈ ነው። 

የቡድኑ መስራች ልዩ አማረምስል Leyou Amare

የዚሁ የፌስቡክ ቡድን አባላት ከለጠፏቸው እና ከ10ሺ በላይ ሰዎች ከወደዱላቸው ወይም ብዙዎች ከሚጋሯቸው ትዝታዎች መካከል፣ በኢትዮጵያ ቴሌቬዥን ታላቅ ፊልም ሲጀምር ወላጆቻቸውን ቀስቅሱን ያሉ፣ በዳማ ከሴ የታከሙ፣ ጢንዝዛ እግሩን በክር አስረው የተጫወቱ፣ ፀጉራቸውን ፍሪዝ ለማድረግ ተልባ ቀቅለው የተቀቡ፣ ጥቅስ እና የታዋቂ ሰዎች ምስሎች የለጠፉበት አውቶግራፍ የነበራቸው በርካታ እንደነበሩ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ሌሎች አሳታፊ ውድድሮችም በዚህ የ90ዎቹ የፌስ ቡክ ቡድን ላይ ተለጥፈዋል። « ድሮ እና ዘንድሮ የሚሉ ፎቶዋችንን እንለጥፍ ነበር።» ትላለች ልዩ።  ወታደሩ በጥይት፣ የቤት ሰራተኛዋ በፅዳት እቃዎች፣ የብረታ ብረት ሰሪው ከቁርጥራጭ ብረቶች እና ሌሎችም ቁሳ ቁሶችን በመጠቀም የ90ዎቹ ልጆች እንደሆነ በጥበብ የገለፁበት ምስሎችም እዚሁ ገፅ ላይ ይገኛሉ። ልዩን በጣም ያሳቃት በገንፎ የተሰራው ነው። 

የዚህ ቡድን አባል የሆነው ቴድሮስ ሙሴ የለጠፈው ደግሞ ከ 29ሺ በላይ አድናቆት አግኝቷል። ይህም እህቱን ለማመስገን በለጠፈው መልዕክት ነው።« ብዙዎቻችንን ያሳደጉን በሁለት እና በሶስት አመት የሚበልጡን እህቶቻችን ናቸው። እሷን ለማመስገን ስል «እነሱ ሳያድጉ እኛኝ ላሳደጉን እህቶቻችን አንዴ ጭብጨባ ብዬ የለጠፍኩት ነበር» ይላል።  

ምስል Leyou Amare

በአሳ እና የውኃ ሳይንስ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪዋን ያጠናቀቀችው የቡድኑ መስራች ልዩ ይህንን የፌስቡክ ገፅ  ብቻዋን አይደለም የምትቆጣጠረው። ከእሷ ጋር ኃላፊነት የወሰዱ 33 ወጣቶች እንደሚሰሩ ገልፃልናለች። ከነዚህ አንዱ ግዕዝ ዘውዱ ይባላል። « ከልዩ እና ከኤሊያስ ጋር የግሩፑ አድሚን ነኝ »ይላል ግዕዝ ። በህብረት ከህዝቡ የሚመጣውን መልዕክት ማለፍ የሌለባቸውን እየለየን ለህዝብ እንለቃለን የሚለው ግዕዝ የዘንድሮ ዓመት የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ምሩቅ እና ሰራተኛ ነው። እሱም በትርፍ ጊዜው ነው ለ90ዎቹ ቡድን የሚያገለግለው። « ገቢ አናገንበትም ግን የሰው ደስታ ፣ ሀገሪቱ ላይ ያለው ሁኔታ መቀየሩ ያስደስተኛል። ሀገሪቱ ላይ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጥቅም ሆን ተብሎ  ወደ መጥፎ ግራ ጎን እየወሰደው ነበር። ስለ ፖለቲካ ስለ ዘረኝነት ነበር የሚነገረው። ሁሉም ሰው የፖለቲካ ተንታኝ ሆኖ ነበር። መፍትሄ ጠፋ። እና ይህንን በትንሹም ቢሆን ወደ በጎው ቀይረንዋል ብዬ አስባለሁ።» ይላል ግዕዝ። 

የቡድኑ አባላትምስል Leyou Amare

ሙሉውን ዝግጅት በድምፅ ማግኘት ይቻላል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW