1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ዩሪ ጋጋሪን - የዓለማችን የመጀመሪያው የጠፈር ተጓዥ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 6 2013

ከ60 ዓመታት በፊት የሩሲያው ጠፈርተኛ ዩሪ አሌክሲይቪች ጋጋሪን «ቫስቶክ 1»መንኮራኩረን ይዞ ወደ ህዋ በመጓዝ የመጀመሪያው ሰው በመሆን ታሪክ ሰርቷል። ይህንን ጠፈርተኛ ሩሲያውያን በሳምንቱ መጀመሪያ ዘክረውታል። ጠፈርተኛወ ንድፈ ሀሳብን ወደ ተግባር በመለወጥ ለህዋ ሳይንስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

Juri Gagarin in der Wostok 1
ምስል United Archives International/imago images

ዩሪ ጋጋሪን - የዓለማችን የመጀመሪያው የጠፈር ተጓዥ

This browser does not support the audio element.

  

በጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 12 ቀን 1961 ዓ/ም የሩሲያው ጠፈርተኛ ዩሪ አሌክሲይቪች ጋጋሪን «ቫስቶክ 1» በተባለች ሮኬት ወደ ጠፈር በመጓዝ ምድርን የዞረ የመጀመሪያው ሰው በመሆን ታሪክ ሰርቷል። ይህ የጋጋሪን ታሪካዊ ጉዞ 108 ደቂቃዎችን የፈጀ ሲሆን ያለፈው ሰኞ 60ኛ አመቱን ደፍኗል።፤ከስድስት አሥርተ ዓመታት በፊት ዩሪጋጋሪን በሞስኮ ቀዩ አደባባይ የተቀበሉት ሩሲያውያንም ለዩሪ ጋጋሪ  ክብር ከካርቶን እና ከፕላስቲክ  የተሰሩ ሮኬቶችን ወደ ሰማይ በመተኮስ በሺዎች የሚቆጠሩ  ሩሲያውያን በሳምንቱ መጀመሪያ  በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የጠፈርተኛው ቀን ዘክረዋል።በዓሉ ላይ የታደሙት ቭላድሚር ክራስኪን  ከ 60 ዓመታት በፊት በተካሄደው የጠፈር ጉዞ መሬት ላይ ሆነው በረራውን ከሚቆጣጠሩ ሰራተኞች አንዱ ነበሩ። የ90 ዓመት አዛውንቱ ከ60 ዓመት በፊት የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ያስታውሱታል።
«በዚያን ወቅት  ከሚያዚያ 12 ቀን በፊት ጥቂት እንቅልፍ አልቫ ሌሊቶች ነበሩን።ስለዚህ የዚያን ዕለት በጣም የጭንቀት ስሜት ነበረን። እውነቱን ለመናገር  መተኛት ያስፈልገኝ ነበር። ግን ደግሞ በጣም ተጨንቄ ስለነበር አይኖቼን እንኳ መጨፈን አልቻልኩም። ስራችንን  መቀጠልም ነበረብን።» 
ወቅቱ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና በቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት መካከል በነበረው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የተነሳ ከሚያደርጉት ቀዝቃዛ ጦርነት ባሻገር የህዋ ምርምር ፉክክርም በሀገራቱ መካከል  እያደገ ስለነበር፤ ይህ አስደናቂ የዩሪ ጋጋሪን የጠፈር ጉዞ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክስተት ነበር፡፡
የጋጋሪን ስኬት ሶቬት ህብረት የህዋ ምርምር  ዕውቀትን ለማሳደግ ከአሜሪካ ጋር በነበረው ውድድር ወሳኝ ምዕራፍ ቢሆንም፤ ሰርጌ ኒኪታ ኩሩሾፍ  እንደሚሉት ተልዕኮው ሙሉ በሙሉ በታቀደው መንገድ የሄደ አልነበረም፡፡ 

ምስል Vladimir Gerdo/TASS/dpa/picture alliance

በወቅቱ ጋጋሪን ከታቀደው ከፍታ በላይ ወደ ምህዋር ውስጥ በመግባቱ  ጉዞው ሊሰናከል ይችላል፤ወይም የእርሱን  ወደ መሬት መመለስ ሊያዘገይ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አሳድሮ ነበር ። የጋጋሪን በሕዋ ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ መቆየት ደግሞ  በሂደት  የምግብ ፣ የመጠጥ እና የኦክስጂን  እጥረት ሊያጋጥመው  ስለሚችል፤ ህይወቱ አደጋ ላይ ሊሆን ይችላል የሚል ሌላ ስጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ያም ሆኖ  «ቮስቶክ -1» መንኮራኩር  ጋጋሪን ይዛ በሰላም ወደ ምድር ተመለሰች።የደረሰው ግን እንዲያርፍ  ከተወሰነለት ቦታ ርቆ በሩሲያ ሳራቶቭ ክልል ውስጥ አንዲት አሮጊትና የልጅ ልጃቸው  ድንች በሚቆፍሩበት አንድ ማሳ ላይ ነበር። 
እንደ ኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጅ  ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር ሶሎሞን በላይ  የጋጋሪን ጉዞ ምንም እንኳ በቀዝቃዛው ጦርነት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ ንድፈ ሀሳብን  ወደ ተግባር በመለወጥ ለህዋ ሳይንስ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። 
የሁለቱ ሀያላን  ርዕዮተ-ዓለም በሁለት ጎራ መከፈል ጋር ተያይዞ ሀገራት ለዩሪ ጋጋሪንና  ለጉዞው የነበራቸው እይታ የተለያዬ ቢሆንም፤ ሶቪየት ህብረት ለቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመንን ፣ ሮማኒያን ፣ ቡልጋሪያና  ፖላንድን የመሳሰሉ  የሶሻሊስት ሀገሮች የራሳቸውን የጠፈር ተጓዞች ወደ ምህዋር እንዲልኩ  ጥረት ታደርግ ስለነበር ፤ለነዚህ  ሀገራት የጋጋሪን ዝና ከ60 ዓመታት በኋላ አልደበዘዘም። የዩሪጋጋሪ ንድፈ ሀሳብን  ወደ ተግባር የመለወጥ ስራም  በአሁኑ ወቅት ከነዚህ ሀገሮች አልፎ የዓለምን አመለካከት  ጭምር የለወጠ መሆኑን ዶክተር ሶሎሞን ያስረዳሉ።

ምስል Tass/picture-alliance

ሶቪዬት ህብረት  በጋጋሪን በረራ ስኬታማነት ለጊዜው አሜሪካን መብለጥ ብትችልም፤ በሶስት ሳምንት ልዩነት ውስጥ ግንቦት 5 ቀን 1961 ዓ/ም አሜሪካ አላን ሸፓርድን  ወደ ህዋ  መላክ ችላለች።ጠፈርተኛው የንዑስ ምህዋር በረራ በማድረግም ሁለተኛው ሰው ሆኗል።በየካቲት 20 ቀን 1962 ደግሞ ደግሞ  «አትላስ -6» ሮኬትን ይዞ  አሜሪካዊ ጠፈርተኛ ጆን ግሌን ወደ ህዋ ተጓዘ። ግሌን ከጋጋሪን የበለጠ ምድርን ሦስት ጊዜ በመዞር ክብረወሰንን ሰበረ። የሶቪዬት ህብረትም ከጋጋሪን ጉዞ ከሁለት ዓመት በኋላ፤ የመጀመሪያዋን ሴት ጠፈርተኛ ወደ ህዋ ላከች። ቫለንቲና ተሬሽኮቫ «ቮስቶክ -6 »በተባለች  መንኮራኩር ለሦስት ቀናት ያህል ያሳለፈች ሲሆን መሬትን 48 ጊዜ መዞር ችላለች።ሐምሌ 20 ቀን 1969 ኒል አርምስትሮንግ እና ባዝ አልድሪን ጨረቃን በመርገጣቸው፤አሜሪካ የጠፈር  ፉክክሩን የበላይነት ያዘች። በዚህ ሁኔታ የቀጠለው የሁለቱ ኀያላን ፉክክር  ለሳይንሱ እድገት አስተዋፅኦ ማበርከቱን ዶክተር ሶሎሞን ይገልፃሉ።
በ34 ዓመቱ በ1968 ዓ/ም  የሚሰለጥንበት ተዋጊ ጀት በመከስከሱ  ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የሪ ጋጋሪን፤ወደ ህዋ በመጓዝ ዛሬም ድረስ የዘለቀውን የሶቪዬት ህብረት የጠፈር ምርምር ልዕለ ኃያልነት ሚና አጠናከሯል። 

ምስል Dmitry Rogulin/TASS/dpa/picture alliance

የምስራቅና የምዕራቡ ፍጥጫ ማብቃትና የርዕዮተ-ዓለም ልዩነት መደብዘዝ ተከትሎ በዘርፉ የነበረው ፉክክር ወደ ትብብር አድጓል። ትብብሩ  በ1980 ዎቹ መገባደጃ ላይ ሶቪዬቶች ምዕራባውያን ጠፈርተኞችን  «ሚር»የተባለውን የጠፈር ጣቢያቸውን እንዲጎበኙ መጋበዛቸውን ተከትሎ የመጣ ሲሆን፤በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ የጠፈር  መርምር ጣቢያ ጥረቶች ትብብር  ላይ ያተኮሩ ናቸው። የምርምር ጣቢያው ከሩሲያ እና ከአሜሪካ በተጨማሪ የአውሮፓ ህዋ ኤጀንሲ ፣ካናዳ እና ጃፓንንም ያካትታል። ከዩሪ ጋጋሪን የመጀመሪያው ታሪካዊ የጠፈር ጉዞ በኋላ ወደ ህዋ  የሚደረጉ የጠፈር ጉዞዎችም መደበኛ ሆነዋል። ምንም እንኳን  የዓለም አቀፍ ግንኙነት  መልኮች ልክ እንደ ቴክኖሎጂው ሁሉ የተለወጡ ቢሆንም፤ የጠፈር ምርምር  የኃይልና የክብር ማሳያ መሆኑ ግን አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 

ፀሀይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW