1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዩናይትድ ስቴትስ ለሱዳን ተፋላሚዎች መሳሪያ በሚያቀርቡ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

ሰኞ፣ ሰኔ 22 2018

በጀርመን የአለምአቀፍና የአካባቢ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የኾኑት ሃገር አሊ ለዶይቸ ቨለ እንደገለፁት፣ ማዕቀቡ የተጣለው ለኹለቱም ተፋላሚ ወገኖች ድጋፍ በሚያደርጉ ተቋማት ላይ ነው።

Sudan Khartum 2025 | Zerstörte Panzer vor der sudanesischen Zentralbank
ምስል፦ El Tayeb Siddig/REUTERS

ዩናይትድ ስቴትስ ለሱዳን ተፋላሚዎች መሳሪያ በሚያቀርቡ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

This browser does not support the audio element.

 ዩናይትድ ስቴትስ፣ የሱዳንን ጦርነት በማቀጣጠል ተጠያቂ ናቸው ባለቻቸው ስምንት ግለሰቦችና አካላት ላይ ማዕቀብ መጣሏን ሰሞኑን አስታውቃለች። ዶይቸ ቨለ ያነጋጋራቸው የፀጥታ ጉዳይ ተመራማሪ ግን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ራሷም ጦርነቱን ለመሸምገል እየሰራች ያለችው ተፋላሚዎቹን በመደገፍ ከሚከሰሱ ሃገራት ጋር መኾኑን ጠቅሰዋል።

በአጭር አገላለጽ "ኩአድ" በመባል የሚታወቁትና የሱዳንን ግጭት ለመፍታት የተሰባሰቡት ዩናይትድ ስቴትሰ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ እያተኮሩ ያሉትም በራሳቸው ጉዳይ ላይ ነው በማለት ተናግረዋል። ከተጀመረ ከሦሰት አመታት በላይ ያስቆጠረው የሱዳን የእርስበርስ ጦርነት አሁንም አሳሳቢ እንደኾነ ቀጥሏል።

ዩናይትድ ስቴትስ የጣለችው ማዕቀብ

ዩናይትድ ስቴትስም፣ ይሄንኑ ግጭት በማነሳሳት፣ የሰላም ጥረቶችን በማደናቀፍና ጦርነቱን በማቀጣጠል ተጠያቂ ናቸው ባለቻቸው ስምንት ግለሰቦችና አካላት ላይ እገዳ መጣሏን ሰሞኑን አስታውቃለች። በዋሽንግተን የወጣው መግለጫ፣ እነዚህ አካላት የጦር መሳሪያዎችንና የውጭ ሃገራት ተዋጊዎችን ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልና ለሱዳን ጦር ኃይል ያቀርባሉ ብሏል። እነሱ የሚያደርጉት ድጋፍም ጦርነቱ እንዲራዘም አድርጓል በማለት አክሏል።

በጀርመን የአለምአቀፍና የአካባቢ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የኾኑት ሃገር አሊ ለዶይቸ ቨለ እንደገለፁት፣ ማዕቀቡ የተጣለው ለኹለቱም ተፋላሚ ወገኖች ድጋፍ በሚያደርጉ ተቋማት ላይ ነው።

"በተለያዩ ሃገራት የሚሰሩ ተቋማት ናቸው። አብዛኛዎቹ መሰረታቸውን በሱዳን ያደረጉ ነገር ግን ኢራን፣ ፓናማ እና ኮሎምቢያን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት የሚሰሩ ናቸው። ማዕቀብ ከተጣለባቸው አንዱ የኃይል አምራችና አቅራቢ ኩባንያ ነው። አንደኛው ደግሞ የመሳሪያ አምራች ነው። ሌላው የኮሎምቢያ ኩባንያ ደግሞ የግል የመሳሪያ አምራች ኩባንያ ነው። እናም በመሰረቱ የተለያዩ ቀጥተኛ የመሳሪያ አቅራቢዎች የተካተቱበት ዝርዝር ነው" ብለዋል።

ማዕቀብ የተጣለበት የኀይል ኩባንያ፣ የሱዳን ጦር ኃይል የሚጠቀምባቸውን ፈንጂዎች የሚያመርት መኾኑን፣ የኮሎምቢያው መሳሪያ አምራች ኩባንያ ደግሞ የኮሎምቢያ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚያቀርብ መኾኑንም ተመራማሪዋ ገልጸዋል።

አደራዳሪዎቹም ጦርነቱን በማባባስ ይከሰሳሉ

በሱዳን ላለው የእርስ በርስ ጦርነት መባባስና በፍጥነት አለመቋጨት አንዱ ምክንያት፣ የተለያዩ ሃገራት ለኹለቱም ተፋላሚ ወገኖች የሚያደርጉት ድጋፍ መኾኑን ተንታኛች ይናገራሉ። ዩናይትድ ስቴትስ እገዳ መጣሏን ያስታወቀችውም ለኹለቱም ተፋላሚ ወገኖች ድጋፍ ያደርጋሉ ባለቻቸው ግለሰቦችና አካላት ላይ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ ራሷ የሱዳንን ጦርነትለመፍታትና ለመሸምገል እየሰራች ያለችው ግን ተፋላሚዎቹን በመደገፍ ከሚከሰሱት ሃገራት ጋር ነው። ከዩናይትድ ስቴትሰ ጋር በመኾን የሰላም ውይይቶችን ለማመቻቸት የሚሰሩትና በአጭሩ "ኩአድ" በመባል የሚታወቁት እነዚህ ሃገራት ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶችና ግብፅ ናቸው።

ሳዑዲ አረቢያና ግብፅ በጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራውን የሱዳን ጦር ኃይል፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች ደግሞ በጀኔራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በመደገፍ ጦርነቱን እያባባሱ ነው በሚል ይወቀሳሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ግን "ኩአድ" በሚባለው ቡድን ስር  በአሸማጋይነት እየሰራች ያለችው ከነዚህ ሃገራት ጋር ነው።

ሱዳን መጠቀሚያ ሆናለች

ተመራማሪዋ እንደሚሉት ለዚህ ምክንያቱ ዩናይትድ ስቴትት ከሃገራቱ ጋር ያላት የኹለትዮሽ ግንኙነት ነው።

 "እነዚህ ሃገራት ተፋላሚዎቹን ወገኖች በመደገፍ። በሱዳን ጦርነት ተሳታፊ እንደኾኑ ከመታሰባቸው አንጻር፣ እንዴት ዩናይትድ ስቴትስ እምነቷን በነሱ ላይ ጣለች የሚለው ጥያቄ በጣም የሚያነጋግርና ጠቃሚ ጥያቄ ነው። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ሱዳን ስለ ጉዳይዋ ውይይት የሚደረግላት ከመኾን ይልቅ በ "ኩአድ" አባል ሃገራት መካከል፣ ግንኙነቶችን ለማጠናከር፣ ተጨማሪ ስምምነቶችን ለመፈረምና የኹለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማሻሻል መጠቀሚያ እየኾነች ነው" በማለት ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሱዳን ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ ሰሞኑን ኒውዮርክ ውስጥ ለጋዜጠኛች ሲናገሩ፣ አለምአቀፉ ተቋም በ"ኩአድ" አባል ሃገራት የሚደረገውን የማደራደር ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል። ምስል፦ AP Photo/picture alliance

የኹለትዮሽ ግንኙነቶች ከሱዳን እየበለጡ ነው

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር የሚከተለው ፖሊሲ መኾኑን አመልክተዋል።

"የትራምፕ አስተዳደር፣ በተለይ ከቴክኖሎጂና የሰው ሰራሸሰ አስተውሎት ዘርፍ አንጻር ከዩናይትድ አረብ ኤምሬቶችና ከሳዑዲ አረቢያ  ጋር ግንኙነቱን የማስፋት ጠንካራ ፍላጎት አለው። በትራምፕና በመሐመድ ቢል ሳልማን መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ ነው። እና ከነዚህ ሃገራት ጋር ለመገናኘትና ግንኙነትን ለማጠናከር ሱዳን ጥሩ ሰበብ ወይም ምክንያት ሆናለች" ብለዋል።በሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ የጄኔራል አልቡርሃንን ጦር በመደገፍ እንደምትሳተፍ ከምትወቀሰው ግብፅ ጋር ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ መኾኑን ተመራማሪዋ አስረድተዋል።

"ከግብፅ ጋርም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው- ግብፅ ለእሰራኤልና ለጋዛ ካላት ቅርበት አንጻር ስልታዊ አጋር በመኾኗ ምክንያት- ለሊቢያም ቅርብ ናት። እና ዩናይትድ ስቴትስ ጥሩ ግንኙነቷን ማስጠበቅ የምትፈልግባት መካከለኛ ኃያል ሃገር ናት። ስለዚህ የሃገራቱ ግንኙነት ኹሉንም ነገር ያካተተ ነው።-ከሱዳን ጉዳይ በስተቀር። ስለኾነም ሱዳን የነሱ መገናኛ መሳሪያ ናት። ይህ አካሄድ ደግም በባይደን አስተዳደር ወቅትም የተመለከትነው ነው" በማለት አብራርተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሱዳን ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ ሰሞኑን ኒውዮርክ ውስጥ ለጋዜጠኛች ሲናገሩ፣ አለምአቀፉ ተቋም በ"ኩአድ" አባል ሃገራት የሚደረገውን የማደራደር ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል። "ምኛታችን "ኩአድ" በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቅም እንዲኖር ለማድረግ የያዘውን ጥረት እንደሚገፋበት ነው" ብለዋል። የተኩስ አቁም መኖር፣ ከሲቪሉ ማኀበረሰብ አንጻር ላለው ሀኔታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከሚያዝያ 2023 አንስቶ በሱዳን  የተቀሰቀሰውና ከሦስት አመታት በላይ ለኾነ ጊዜ የቀጠለው የሱዳን ጦርነት ቁጥራቸው 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

እስክንድር ፍሬው

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW