1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ጦር ላይ አዲስ ማዕቀብ ልትጥል ነው

ቅዳሜ፣ ግንቦት 16 2017

ከጎርጎሮሳዊው ሰኔ 6 ቀን 2025 ዓ.ም. አንስቶ የሚጣለው ማዕቀብ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሱዳን የሚገቡ ሸቀጦችና ከዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ብድርን ያግዳል። ከአንድ ሳምንት በኋላ የሚጣለውም ማዕቀብ በዋነኛነት በኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ነው። ሱዳን ግን ጦሯ ኬሚካዊ የጦር መሣሪያዎች ተጠቅሟል መባሉን ሀሰት ስትል አስተባብላለች።

በጦርነቱ የተጎዳ ኻርቱም የሚገኝ የገበያ ስፍራ
በጦርነቱ የተጎዳ ኻርቱም የሚገኝ የገበያ ስፍራ ምስል፦ AFP

ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ጦር ላይ አዲስ ማዕቀብ ልትጥል ነው

This browser does not support the audio element.

 ሕጋዊ እውቅና ባይኖራቸውም ሱዳን በሚመሩትየሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዝ በጀነራል አብዱል ፈታህ ቡርሀን ላይ ዩናይትድ ስቴትስ አዲስ ማዕቀብ ልትጥል ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ የሱዳን ጦር ኃይል በተቀናቃኙ በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ላይ ኬሚካዊ የጦር መሣሪያዎችን ተጠቅሟል ሲል ከሷል። የዩናይትድ ስቴትሱ ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሹን ኃይል ተዋጊዎች ሁለት ጊዜ በክሎሪን ጋዝ አጥቅቷል ሲል ዘንድሮ በጥር ወር ዘግቦ ነበር። ከፊታችን ጎርጎሮሳዊውሰኔ 6 ቀን 2025 ዓ.ም. አንስቶ የሚጣለው ማዕቀብ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሱዳን የሚገቡ ሸቀጦችንና ከዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ብድርን ያግዳል።ሱዳን ግን ጦሯ ኬሚካዊ የጦር መሣሪያዎች ተጠቅሟል መባሉን ሀሰት ስትል አስተባብላለች።

የዩናይትድ ስቴትስ የእርዳታ ቢሮ እንደሚለው በ2024 ለሱዳን 790 ሚሊዮን ዶላር ተሰጥቷል።  ከዚህ ውስጥ 750 ሚሊዮን ዶላሩ ለሰብዓዊ እርዳታ የተመደበ ነው። ሆኖም በአዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለሱዳን ይሰጥ የነበረውን እርዳታ አቋርጧል። ከአንድ ሳምንት በኋላ የሚጣለውም ማዕቀብ በዋነኛነት በኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ እንደሚሆን በጀርመኑ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ተመራማሪ  አገር አሊ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። 

ከፖርት ሱዳን አውሮፕላን ማረፊያ ከርቀት የሚታይ ጢስ ምስል፦ AFP

«የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት አሁን ማዕቀቦችን መለማመዳቸውን መገመት ይቻላል። ይህ እስካሁን የመጀመሪያው ማዕቀብ አይደለም። እነዚህ ማዕቀቦች ከጎርጎሮሳዊው ሰኔ 6 ቀን 2015 ዓም አንስቶ ተግባራዊ ይሆናሉ።  አብዛኛዎቹ የኤኮኖሚ ማዕቀቦችን ያካተቱ ናቸው። ለምሳሌ  ከዩናይትድ ስቴትስ የሚገቡ ሸቀጦች እና ከዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ብድር ላይም ተጽእኖ ይኖረዋል። ግን ተፋላሚዎቹ ብዙም አይበደሩም ። ማዕቀቡ ጦር ኃይሉን ከመጉዳት ይልቅ ከሁለት ዓመት በፊት አንስቶ አሰቃቂ ሰብዓዊ ችግር ውስጥ የወደቀውንና የተፈናቀለው የሱዳን ህዝብን አበሳ የሚያባብስ መሆኑ አይቀርም ነው የሚባለው።  በጥር ወር የተሰናበተው የባይደን አስተዳደር በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች  ላይ ማዕቀብ ጥሎ ነበር። በመጀመሪያ ፈጥኖ ደራሹን ኅይል የሚመሩት ጀነራል መሐመድ ዳጋሎ በዘር ማጥፋት ወንጀል እና በከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

በዚያው በጥር የባይደን አስተዳደር ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን በሚመራው የሱዳን ጦር ኃይሎች ላይ ሰላማዊ ዜጎችን ለሞት የዳረጉ በተባሉ  ጥቃቶች እና የዴሞክራሲ ሽግግር ግቡን በማጣጣል ተከሶ ማዕቀብ ተጥሎበታል ።በቅርብ ጊዜው የተመድ መረጃ መሠረት በጦርነቱ 13 ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅሏል። በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝቡ ረሀብ አፋፍ ላይ ነው ። የተመድ የሴቶች ጉዳይ የሚመለከተው ክፍል እንዳስታወቀው በተለይ የሱዳን ሴቶች ህጻናትና ልጃገረዶች ፆታዊ  ጥቃትንና መደፈርን ጨምሮ የተለያዩ ከባድ ችግሮች ውስጥ ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅ ወደ 150 ሺህ እንደሚጠጋ ይገመታል። 

ካሚል ኢድሪስ አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓም ምስል፦ Gerhard Leber/IMAGO

ከዚህ ሌላ ሀገሪቱ ለሁለት ወደ መከፈል ልትሄድ ትችላለች የሚል ስጋት አለ። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በመጋቢት ወር የሰላምና የአንድነት የተባለው ትይዩ መንግስት ለመመስረት ከአጋሮቹ ጋር ተፈራርሞ ነበር። የሱዳን ጦር ኃይል ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር ለሚገኙት ማዕከላዊ እና ሰሜንና ምስራቅ ሱድን የሰላም ፍኖተ ካርታቸውን አስተዋውቀው ነበር። በዚሁ በመጋቢት ወር የሱዳን ጦር ዋና ከተማይቱን ኻርቱምን መልሶ ቢቆጣጠርም ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ከአማጽያን ነጻ ያደረገው ከሁለት ወራት በኋላ ነው። ይህ የሆነውም ቡርሀን የ71 ዓመቱን የቀድሞ የተመድ ዲፕሎማትካሚል አል ታይብ ኢድሪስን አዲሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው በሾሙ በማግስቱ ነበር።

 
ከሁለት ወራት በፊት ኻርቱም ነጻ ወጣች ከተባለ በኋላ ሶር ኃይሉ የማስተዳደር ማዕከላዊ ሱዳንን የመቆጣጠር ችሎታውን እንዴት ማሳየት እንደሚችል ሲያስብ ነበር ያሉት የሱዳን ፖሊሲ ተንታኝ ሀሚድ ካሊፋ ፣ተሿሚውን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ምን የሚፈይዱ አይሆኑም ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።  
« የሱዳን መከላከያ ጦር ሙያዊ የፊት ገጽታው በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትና ተዓማኒት ለማግኘት እየተጠቀመበት ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ አስቸጋሪ ታሪኮች አሏቸው። በብዙ ምክንያት ሲታይ አድርባይ ሰው ናቸው። ስለዚህ ምንም ማለት አይደሉም። ታሪካቸውን እና የፖለቲካ ልምዳቸውን ከግምት ውስጥ ስናስገባ ለሱዳን መከላከያ ጦር አሻንጉሊት ከመሆን ውጭ ምንም ማለት አይደሉም።»  ይሁን 22 አባል ሀገራት ያሉት የአረብ ሊግ እና የአፍሪቃ ኅብረት ሹመቱን ተቀብለዋል።  

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW