ዩክሬን እና ሩሲያ ለሁለተኛ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር ምርኮኞች ተለዋወጡ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 16 2017
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ትልቅ እንደሆነ የሚነገርለትን ውጊያ የገጠሙት ሩሲያ እና ዩክሬን ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ቅዳሜ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር ምርኮኞች መለዋወጣቸውን በየፊናቸው አረጋገጡ። ከሦስት ዓመታት በላይ የተዋጉት ሁለቱ ሀገሮች በሺሕዎች የሚቆጠሩ የጦር ምርኮኛ ይዘው ይገኛሉ።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ሁለቱም ሀገራት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ የጦር ምርኮኞችን እየለቀቁ ወደ የሀገራቸው ሲመልሱ ቆይተዋል። ይሁንና ከትላንት ዓርብ ጀምሮ እየተካሔደው ያለው ልውውጥ በጦር ምርኮኞች ብዛት ከፍተኛው ነው።
ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ 307 የዩክሬን ወታደሮች ዛሬ ቅዳሜ ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን አረጋግጠዋል። ቀደም ብሎ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ተመሣሣይ ቁጥር ያላቸው ሩሲያውያን የጦር ምርኮኞች ከዩክሬን መቀበሉን ገልጿል።
የመጀመሪያው የጦር ምርኮኞች ልውውጥ የተካሔደው ትላንት አርብ ሲሆን እያንዳንዳቸው 390 ሰዎች ከሌላው ተቀብለዋል። በአጠቃላይ 1,000 የጦር ምርኮኞች ይለዋወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዜሌንስኪ “የምርኮኞች ልውውጡ ነገ ይቀጥላል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል።
ሩሲያ የምርኮኞች ልውውጡ ከተጠናቀቀ በኋላ ጦርነቱን ለማብቃት የምታዘጋጀውን ምክረ-ሐሳብ ለዩክሬን እንደምታቀርብ ፍንጭ ሰጥታለች።
ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማሸማገል ሞክረው እስካሁን ያልተሳካላቸው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጦር ምርኮኞች ልውውጡ ለሁለቱም “እንኳን ደስ አላችሁ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ትራምፕ “ይህ ወደ ትልቅ ነገር ሊያመራ ይችላል?” ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተባለ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ጽፈዋል።
ሁለቱ ሀገሮች የጦር ምርኮኞች መለዋወጣቸውን ይፋ ያደረጉት ሩሲያ በኪየቭ በድሮን እና በሚሳይል በፈጸመችው ኃይለኛ ጥቃት 15 ሰዎች በቆሰሉበት ዕለት ነው።
የዩክሬን አየር ኃይል ሩሲያ ለሊቱን በ14 ሚሳይሎች እና 250 ድሮኖች ጥቃት መፈጸሟን አስታውቋል። ይሁንና ስድስት ሚሳይሎች እና 245 ድሮኖች ማክሸፉን የዩክሬን ኃይል እንዳከሸፈ መግለጹን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የጥቃቱ ዋንኛ ዒላማ የዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ነበረች።
በጥቃቱ በኪየብ ከተማ 15 ሰዎች ሲቆስሉ በኻርካይብ አምስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ በእያንዳንዱ እንዲህ ያለ ጥቃት ሞስኮ ጦርነቱን የማራዘም ፍላጎት እንዳላት ዓለም እርግጠኛ ሆኗል በማለት ሩሲያን ወንጅለዋል።
የሩሲያ ጦር በበኩሉ ዩክሬን በ788 ድሮኖች እና ሚሳይሎች ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ጥቃት እንደፈጸመች ከሷል። በሞስኮ ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ድሮኖች ባለፈው አንድ ሣምንት ውስጥ ማክሸፉንም ይፋ አድርጓል።