1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬን የኃያላን መፋለሚያ ሜዳ

ሰኞ፣ የካቲት 20 2015

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ባለፈዉ አንድ ዓመት ከ6ሺሕ በላይ ሰላማዊ ዩክሬናዊ ተገድሏል።ከ8 ሺሕ በላይ ቆስሏል።ከ4.7 ሚሊዮን በላይ ሕዝቧ አንድም ከየቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ደግሞ በጦርነቱ የመጀመሪያ ወር ብቻ ከ560 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የዩክሬን የመሰረተ ልማት አዉታር ወድሟል።

Deutschland Berlin | Peacezeichen aus Kerzen vor dem Brandenburger Tor
ምስል Paul Zinken/dpa/picture alliance

የሰላም ጥሪና ዕቅዱ እስካሁን ሰሚ አላገኘም።

This browser does not support the audio element.

የሩሲያ ጦር «ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ» ባለዉ ጥቃት ዩክሬንን ከወረረ ባለፈዉ አርብ ዓመት ደፈነ።የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ዩክሬን ዛሬም እንደአምና ሐቻምናዉ ቆማለች ይላሉ።የአዉሮጳና የእስያ ተከታዮቻቸዉ የዋሽግተኖችን አባባል ያፀድቃሉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን የሟች፣ ቁስለኞ፣ ስደተኞችን ቁጥር፣ የጠፋ ሐብት ንብረትን ብዛት ይዘረዝራል።የቱርክ፣ የብራዚል፣የቻይና መሪዎችና ባለስልጣናት ድርድር እንዲደረግ ይባትላሉ።የኪቭ፣የሞስኮ፣ የዋሽግተን፣ የለንደን-ብራስልስ ተፋላሚዎች ግን ለተጨማሪ ዉጊያ ይፎክራሉ።ኢትዮጵያ ተወልደዉ፣ኪቭ ተምረዉ፣ ለተባበሩ መንግስታት ድርጅት ተቀጥረዉ ሞስኮ የሰሩት ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅወያ ዩክሬን እንዳትጠገን ሆና ወድማለች ይላሉ። ዓለም ከስራለችም። 

በልማዱ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት የሚባለዉ ዉጊያ የተጀመረበት አንደኛ ዓመት   ከመዘከሩ ከሳምት በፊት ደቡባዊ ጀርመን ሙኒክ ዉስጥ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ ተደርጎ ነበር።ከ850 የሚበልጡ የሐገራት መሪዎች፣ ሚንስትሮች፣የጦር አዛዦችና ዲፕሎማቶች በተሳተፉበት ጉባኤ ዩናይትድ ስቴትስን የወከሉት ምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ ነበሩ።

«ዛሬ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ኪቭ አሁንም እንደቆመች መሆንዋን እናዉቃለን።ሩሲያ ተዳክማለች።የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ትብብር ከመቼዉም ጊዜ ይበልጥ ተጠናክሯል።»

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት ባይሳ ዋቅ ዋቅያ ስዊድንና ስዊዘርላንድ ይኖራሉ።በቅርቡ ሩሲያን ጎብኝተዋል።በምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ ያሉትን አይተዉ ይሆን?

«ከጦርነቱ ትልቋ አትራፊ አሜሪካ ብቻ ናት።የአዉሮጳ ሐገራትን ገፍታ እዚሕ ዉስጥ ስትከት እንቢኝ ማለት አይችሉም።ያዉ አሜሪካናት የምታዛቸዉ።የማይፈልጉት ጦርነት ዉስጥ ገብተዉ እየተሰቃዩ ነዉ።ዤኔቫ፣ ፈረንሳይ ስዊድን መሐከል ነዉ የምኖረዉ።በነዚሕ ሐገራት ያለዉን የኑሮ ዉድነት ስታይ ከምታምነዉ በላይ የአዉሮጳ ሕዝቦች እየተሰቃዩ ነዉ።ራሽያም በስራ ምክንያት እሔዳለሁ።አሁን ራሽያኖች የአዉሮጳና ያክል አልተሰቃዩም።በምንም መልኩ በቤንዝንም፣በጋዙም፣በምግብ----»   

በርሊን የሰላም ጥሪ ባደባባይ ሰልፍምስል Monika Skolimowska/dpa/picture alliance

 

የምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ መልዕክት አስገምግሞ ሳያበቃ አለቃቸዉ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በድብቅ ተጉዘዉ «እንዳለች ቆማለች» የተባለችዉን ከተማ ጎበኙ።ሰኞ።እንዳለች በቆመችዉ ኪቭ ግን  ከሰዓታት በላይ መቆየት አልቻሉም።ወደ ዎርሶ-ፖላንድ ተመለሱ።የምክትላቸዉን አባባል ደገሙት።

«ካንድ ዓመት በፊት ዓለም ኪቭ ትማረካለች ብሎ አስቦ ነበር።ኪቭን ጎብኝቼ መመለሴ ነዉ።ኪቭ እንደጠነከረች ሞቆሟን መናገር እችላለሁ።ኪቭ በኩራት ቆማለች፣ እንዲያዉም ይበልጥ ተልቃለች፤ ከሁሉም በላይ በነፃነት ቆማለች።»

አቶ ባይሳ ግን እዉነታዉ ተቃራኒ ነዉ ባይ ናቸዉ።የአሜሪካ መሪዎችን መልዕክትም ለግብር ከፋዩ አሜሪካዊ ማስታገሻ «ኪኒን» ይሉታል።

«ምንድነዉ አሁን ዛሬ ስታየዉ ዩክሬን የለችም።ወደመች እንደሐገር።አሜሪካኖች የሚሉት ዝም ብለዉ ዩክሬን እያሸነፈች ነዉ።እናሸንፋለን።ክራሚያን ሁሉ እናስመልሳለን የሚባለዉ፣ለአሜሪካ ግብር ከፋዮች ኪኒን ናት፣ ማስታገሻ ናት።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ባለፈዉ አንድ ዓመት በትንሽ ግምት ከ6ሺሕ በላይ ሰላማዊ ዩክሬናዊ ተገድሏል።ከ8 ሺሕ በላይ ቆስሏል።ከ4.7 ሚሊዮን በላይ ሕዝቧ አንድም ተሰድዷል አለያም ከየቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ደግሞ በጦርነቱ የመጀመሪያ ወር ብቻ ከ560 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የዩክሬን የመሰረተ ልማት አዉታር ወድሟል።

ባለፈዉ አንድ ዓመት ዩናይትድ ስቴትስ የአዉሮጳ ሕብረት፣ብሪታንያ፣ካናዳ፣አዉስትሬሊያ፣ ጃፓንና ሌሎች ተባባሪዎቻቸዉ ከ120 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ጦር መሳሪያ  ለዩክሬን ጦር አስታጥቀዋል።ዉጤት? እንደገና አቶ ባይሳ።

«አሜሪካ ለዩክሬን የረዳችዉ፣ ሩሲያ ባንድ ዓመት ዉስጥ ለጦርነት ከምታወጣዉ በላይ ነዉ።የአሜሪካ ግብር ከፋዩን ሕዝብ ለማሳመን ወይም ለማባበል ‚እያሸነፉ ነዉ፣ ሐገሪቱ ድል እየተቀዳች ነዉ ብሎ ማዉራት አለብሕ።እዉነታዉ ግን ከዚሕ የተለየ ነዉ----»

በጦርነቱ የተገደሉት የዩክሬንና የሩሲያ ወታደሮች፣ የሁለቱ ተባባሪ ታጣቂዎች ትክክለኛ ቁጥር አይታወቅም።ገማቾች እንደሚሉት ግን ከሁለቱም ወገን ከ7 እስከ አስር ሺሕ የሚገመት ወታደርና ታጣቂ ተገድሏል።

ምስል AFP

ምዕራባዉያን መንግስታት በሩሲያ ላይ የጣሉት 11 ሺሕ ዓይነት ማዕቀብም ምዕራባዉያን እንዳሰቡት ባይሆንም የሐብታም-ኃያሊቱን ሐገር ምጣኔ ሐብት ክፉኛ ጎድቶታል።ዓለም ባጠቃላይ በትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ደርሶባታል።

የጦርነቱ መራዘም የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ-ወዳጆችን ብቻ ሳይሆን የቤጂንግ-ሞስኮ-ቴሕራን-ፒዮንግዮንግን ትብብር እያጠናከረም ነዉ።ምናልባት የኑክሌር ቦምብ «ቀለበት ሊያስብ» ይችላል የሚለዉ ስጋትም እየናረ ነዉ።

አዉዳሚ-አስጊዉን ጦርነት በድርድር ለማስቆም ባለፈዉ ዓመት የቱርኩ ፕሬዝደንት ጠይብ ኤርዶኻን ከፍተኛ ጥረት ጀምረዉ ነበር።ከኔቶ አባል ሐገራት ሁሉ በሕዝብ ቁጥርም፣ በጦር ኃይል ብዛትም ሁለተኛዉን ደረጃ የያዘችዉ ቱርክ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ሆና የዩክሬን ስንዴ ለዓለም እንዲቀርብ የሞስኮና የኪቭ ባለስልጣናትን አምና አስማምታለች።

የቱርኩ መሪ በነካ እጃቸዉ የሩሲያና የዩክሬን ባለስልጣናትን ለማደራደር ያቀረቡትን ሐሳብ የሞስኮና የኪቭ መሪዎች በግልጽ አልተቃወሙትም።እስካሁን ግን ሐሳቡ ገቢር አልሆነም።የብራዚሉ ፕሬዝደንት ሉዊስ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫም ተፋላሚ ኃይላትን የሚያደራድሩ የሐገራት ስብስብ ለመሰረት እየጣሩ መሆናቸዉን ባለፈዉ ወር አስታዉቀዋል።

ሉላ እንደሚሉት ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያና ቻይና በአደራዳሪዎች ስብስብ ዉስጥ እንዲካተቱ ይፈልጋሉ።የቤጂንግ ዲፕሎማቶች የሉላን ጥሪ ተቀብለዉ  ይሁን ወይም በራሳቸዉ ፈቃድ ጦርነቱ በድርድር እንዲቆም አዲስ ጥረት ጀምረዋል።

ሙኒክ-ጀርመን ዉስጥ በተደረገዉ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ዪ በጉዳዩ ላይ ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተነጋግረዉበታልም።የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ ተፋላሚ ኃይላትን ለማግባባት ቻይና ባለ 12 ነጥብ የመደራደሪያ ሐሳብ አቅርባለች።

በሕንፃ ፍርስራሽ መሐል ምስል Privat

ሩሲያ የቻይናን የሽምግልና ሐሳብ እንደምትቀበለዉ አስታዉቃለች።የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላይን ግን ቻይና ያቀረበችዉ የድርድር ዕቅድ ሳይሆን መርሕ ነዉ ይላሉ።

 «እዉነት ነዉ።የቻይና ወረቀት፣ እንደሚመስለኝ ያጋሩትን መርሕ ማየት አለባችሁ።የሰላም ዕቅድ አይደለም ያጋሩት መርሆዎች ናቸዉ።»

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ፀሐፊ የንስ ሽቶልተንበርግ ደግሞ ከፎን ዴር ላይንም ጠንከር ብለዉ ቻይና ለአደራዳሪነት አትታመንም ባይናቸዉ።

«በመጀመሪያ ደረጃ ቻይና ብዙም የምትታመን አይደለችም ምክንያቱም (ቻይኖች) ዩክሬን በሕገ ወጥ መንገድ መወረሯን ማዉገዝ አልቻሉም።»

የቱርክ፣የብራዚል፣ የቻይናም ሆነ የሌሎች ሐገራት የሰላም ጥሪና የማደራደር ጥያቄ ገቢር የሚሆነዉ-አቶ ባይሳ እንደሚሉት በሐሳቡ ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ ሲስማሙበት ብቻ ነዉ።

ጦርነቱ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የአዉሮጳ ሐገራት  አደባባይ የወጣዉ ሕዝብም በጦርነቱ መሰላቸቱን በግልፅ አስታዉቋል።በተለይ ጀርመን ዉስጥ የተsl,ፈዉ ሕዝብ የጀርመን መንግስት ለዩክሬን ጦር መሳሪያ ማጋዙን አቁሞ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልግ ጠይቋል።

ምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ በሙኒኩ ጉባኤ ምስል Thomas Kienzle/AFP/Getty Images

ከ6 መቶ ሺሕ የሚበልጡ የጀርመን ፖለቲከኞች፣ሙሕራንና ጋዜጠኞችም መንግስታቸዉ ለዩክሬን ከባድ ጦር መሳሪያ መስጠቱን አቁሞ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ፈርመዉ አሰራጭተዋል።እስካሁን ግን የሰላም ጥያቄዉ ከጥያቄ አላለፈም።ዉጊያ፣ የተጨማሪ ዉጊያ ዝግጅት ቀጥሏል። እልቂት ጥፋቱም።

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW