1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬን! የአሸናፊ መለያዉ ምንድነዉ?

ሰኞ፣ ግንቦት 29 2014

ፀሎት፣ ምሕላ፣ ተማፅኖ ጥሪዉ ጦርነቱን ለማስቆም አይደለም የማስቆም ተስፋ እንኳን ለመፈንጠቅ አቅመቢስ መሆኑ ነዉ ቀቢፀ-ተስፋዉ።የሕይወት፣ የሐብት፣ንብረት ጥፋቱም የተፋላሚ ኃይላት መሪዎችን ልብ የሚያራራ አልመሰለም

Paris Normandie Treffen | Putin Zelenskyy
ምስል Mikhail Metzel/TASS/dpa/picture alliance

ጦርነቱ ባጭር ጊዜ ይቆማል የሚል ተስፋ ዝግ ነዉ

This browser does not support the audio element.

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊና የዩክሬን ቀዉስ አስተባባሪ አሚን አዋድ በዩክሬኑ ጦርነት ጥፋት እንጂ አሸናፊ አይኖርም ይላሉ።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ «የወንድማማቾች» ያሉትt ጦርነት ሚሊዮኖችን ለመከራ፣ ለስቃይ ሰቆቃ ዳርጓል።አስር ሺዎችን ፈጅቷል።ሚሊዮኖችን አሰድዷል።ዩክሬንን አዉድሟል።የሩሲያን ምጣኔ ሐብት አሽመድምዷል።አፍሪቃን ለምግብ እጥረት፣ የምዕራቡን ዓለም ለኑሮ ዉድነት አጋልጧል።ቀጥላሏም።መቶ ሶስት ቀኑ።ተፋላሚ ኃይላት ግን ለተጨማሪ ዉጊያ እንደተሰላለፉ ነዉ።የዩክሬን አስታጣቂዎች ፉከራ አላበራም።የሰላም ጥሪዉ ባዶነት፣የጦርነቱ ጥፋትና የቀጣዩ ጦርነት ዝግጅት ያፍታ ጥንቅራችን ትኩረት ነዉ።

                                        

ጥንትም፣ድሮ፣ በቅርቡም አዉሮጳ በጦርነት ስትነድ፣መካከለኛዉ ምስራቅ በእልቂት-ፍጅት ሲዋጅ፣ አፍሪቃ፣እስያና ደቡብ አሜሪካ ሲወድም እንደነበረዉ ሁሉ ዘንድሮም የዲፕሎማቶች ጥሪ፣ የሰላም አራማጆች ምክር የኃይማኖት መሪዎች ምልጃ ሰሚ አላገኘም።

ዓለም አዲሱን ዓመአት ከጀመረ ጀምሮ ከኢራቅ እስከ አፍቃኒስታን፣ ከኮንጎ እስከ ፍልስጤም-እስራኤል ከምያንማር እስከ ሊቢያ፣ ከየመን እስከ ሱዳን፣ ከሶሪያ እስከ ኢትዮጵያ በርካታ ሐገራት ወይም አካባቢዎች ወድመዋል።ዓለምን በጉልበትም፣ በብልጠትም፣ በሐብትም የሚቆጣጠሩት ኃያላን አንዳዶቹ ጋ እስከ 20 ዓመት  በቀጥታ፣ሌሎቹጋ በተዘዋዋሪ በተዋጉባቸዉ ጦርነቶች ሚሊዮኖች አልቀዋል።እያለቁም ነዉ።

ምስል Celestino Arce Lavin/ZUMA Press Wire/ZUMAPRESS/picture alliance

በየጦርነቶቹ አሸናፊ የመሰሉት ሲሸነፉ፣ ተሸናፊ የመሰሉት ድል ሲያደርጉ ከማየት በስተቀር አብዛኛዉ ደሐ ዓለም ያተረፈዉ ጥፋት፣ እልቂት፣ ለትዉልድ የሚተርፍ ቂም ነዉ።የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በቀደም እንዳሉት የዩክሬኑ ጦርነት የተጀመረዉ ዓለም ሚሊዮኖችን ከገበረበት ክፉ ደዌ ሳያገግም፣በየስፍራዉ የተቀጣጠሉ ጦርነቶችን ሳያጠፋ ነዉ።ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ያ መቼም እንደ መንፈሳዊ መሪ ወግ ፖለቲከኞችን መማፀናቸዉ አልቀረም።

               

«የጥፋትና የሞት መዓት ባረበበበት፣ግጭቱ በቀጠለበት (በዚሕ ወቅት)፣ ጥፋቱን ማባባስ ለሁሉም ወገን አደገኛ ነዉ።ለመንግስታት መሪዎች ጥሪዬን በድጋሚ አቀርባለሁ።ሰዉን ወደ ጥፋት አትምሩት፣እባካችሁ ሰዉን ከጥፋት አትጨምሩት።»

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተምፅዕኖ ከመሰማቱ ከዕለታት በፊት ባለፈዉ አርብ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ አሚን አዋድም እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ሶስተኛ ወሩን ባጋመሰዉ ጦርነት ከጥፋት በስተቀር አሸናፊ አይኖርም ብለዉ ነበር።

ፀሎት፣ ምሕላ፣ ተማፅኖ ጥሪዉ ጦርነቱን ለማስቆም አይደለም የማስቆም ተስፋ እንኳን ለመፈንጠቅ አቅመቢስ መሆኑ ነዉ ቀቢፀ-ተስፋዉ።የሕይወት፣ የሐብት፣ንብረት ጥፋቱም የተፋላሚ ኃይላት መሪዎችን ልብ የሚያራራ አልመሰለም።ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችበት አንድ መቶኛ ቀን ባለፈዉ አርብ ሲዘከር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት ምክር ሲነገር የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሜር ዜለንስኪ ጦራቸዉ ድል ማድረጉን አስታዉቀዉ ነበር።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ፀሎት-ምሕላ በየመገናኛ ዘዴዉ ሲሰራጭ ትናንት ሌሊት ደግሞ ዜላንስኪ ዶኔትስክ ግዛት  ጦር ግንባር ነበሩ።ምሽግ በመሰለ ቤት ዉስጥ እንደነገሩ በተዘጋጀ የጨለማ ስርዓት «ድል አድራጊ» ያሏቸዉን ወታደሮቻቸዉን ሸለሙ።

«ከዚያ በኋላ ከቢሮ ኃላፊዬ ጋር ወደ ምስራቅ ተጓዝኩ።ሊሻንስክ ግዛት ነበርን።ዞሌደር (ዶኔትስክ ግዛት) ነበርን።ባገኘኋቸዉ ሰዎች ሁሉ፣ እጃቸዉን በጨበጥኳቸዉ፣ድጋፌን በገለጥኩላቸዉ ሰዎች በሙሉ ኮርቻለሁ።ለጦሩ የሆነ ነገር ሰጥተናል።ይሕን ጉዳይ በዝርዝር አልናገርም።ከነሱ ደግሞ ለናንተ ያመጣነዉ የሆነ ነገር አለ።ይሕ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነዉ።ያመጣንላቸዉ በራስ መተማመን ነዉ።»

ምስል ANATOLII STEPANOV/AFP/Getty Images

ዜለንስኪ ዶኔትስክ ግዛት የመሸጉ ወታደሮቻቸዉን በሚያወድሱ፣በሚያሞግሱ፣ በሚሸልሙበት ዉድቅት የሌለኛዋ የምስራቅ ዩክሬን ግዛት የዶንባስከ ከተማ ድሩዥኮቭካ በሩሲያ ሚሳዬል ትፈረካከስ ነበር።ርዕሰ ከተማ ኪየቭ ተደገመች።የታሪካዊቱ፣የስልታዊቱ፣ የዉቢቱ የኦዴሳ  ሰማይም በጋየ አዉሮፕላን ነዲድ፣ ጢስ፣ጠለስ ደፈረሰ።የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ እንዳሉት ጦራቸዉ ኪየቭና ኦዴሳ ላይ የመታዉ የዉጪ መንግስታት ለዩክሬን የላኳቸዉን ጦር መሳሪያዎች ነዉ።

«የሩሲያ ዓየር ኃይል የተኮሰዉ ዒላማዉን ነጥሎ የሚመታ የረጅም ርቀት ሚሳዬል፣የምስራቅ አዉሮጳ መንግስታት ለዩክሬን  የሰጡትን T-72 ታንኮችና ሌሎች ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች የተከማቹበትን ኪየቭ አጠገብ የሚገኘኝ የመኪና መጠገኛ መጋዘንን  አዉድሟል።ኦዴሳ ግዛት ደግሞ የሩሲያ የዓየር መከላከያ ኃይል የጦር መሳሪያና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ጭኖ ይበር የነበረ An 24 የተሰኘዉን የዩክሬን ጦር የዕቃ ማጓጓዣ አዉሮፕላንን መትቶ ጥሏል።»

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ባለፈዉ ሮብ እስንዳስታወቀዉ በጦርነቱ 4ሺሕ 1 መቶ 69 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉን አረጋግጧል።5 ሺሕ የሚጠጉ ቆስለዋል።ፕሬዝደንት ዜለንስኪ እንዳሉት ደግሞ በጦርነቱ የተገደሉት የዩክሬን ሰላማዊ ዜጎች ብዛት በ10 ሺሕ ይቆጠራል።

ዜለንስኪ አክለዉ እንዳሉት  በየቀኑ ከ60 እስከ 100 የሚቆጠሩ የዩክሬን ወታደሮችና ተዋጊዎች ይገደላሉ።የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽነር  UNHCR ባለፈዉ ሳምንት እንደዘገበዉ ጦርነቱ ከቤት ንብረቱ ያፈናቀለዉና ያሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር ከ14 ሚሊዮን በልጧል።

ምስል Jacquelyn Martin/AP/picture alliance

በሩሲያ ጦር ላይ ስለደረሰዉ ጉዳት በትክክል የሚያዉቅ የለም።የብሪታንያ መንግስት ባለፈዉ ሚያዚያ ማብቂያ እንደገመተዉ 15 ሺሕ የሚደርሱ የሩሲያ ወታደሮች ተገድለዋል።በሩሲያ ከሚደገፉ የዩክሬን አማፂያን  መካከል ደግሞ 1 ሺሕ 300 መገደላቸዉ ይገመታል።

በዩክሬን የመሰረተ ልማት አዉታሮች ላይ የደረሰዉ ጥፋትም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።38 ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች ሕንፃዎች፣1 ሺሕ 900 መቶ ትምሕርት ቤቶች፣ መዋዕለ ሕፃናትና የዩኒቨርስቲዎች፣ከ200 በላይ ሐኪም ቤቶች ወድመዋል።500 ሆስፒታሎች በከፊል ጠፍተዋል።300 መኪኖች፣50 የባቡር ድልድዮች፣500 ፋብሪካዎች ጋይተዋል።የፕሬዝደንት ዘለንስኪ ቢሮ የበላይ ኃላፊ እንዳሉት ዩክሬን 600 ቢሊዮን ዶላር ወድሞባታል።ጦርነቱ ያደረሰዉ ሰብአዊና ምጣኔ ሐብታዊ ቀዉስ ሲዘረዘር፣ የዲፕሎማቶች የሰላም ጥሪ፣ የኃይማኖት መሪዎች ልመና ሲደጋገም  የኪየቭ ደጋፊዎች፣ ለተጨማሪ ዉጊያ -ማስታጠቃቸዉ ነዉ-ጉዱ።ዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት መንግስታቸዉ 700 ዶላር የሚያወጣ ጦር ተጨማሪ ጦር መሳሪያ ያስታጥቃል።

 

«ዛሬ ጠዋት ፕሬዝደንት ባይደን ለዩክሬን በጣም ጠቃሚ፣ ተጨማሪ ኃይል ያላቸዉ ዘመናይ የጦር መሳሪያዎችን ያካተተ የፀጥታ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታዉቀዋል።ይሕ እነሱ (ዩክሬኖች) ከሩሲያ ወረራ እራሳቸዉን ለመከላከል በትክክል የሚፈልጉት ነዉ።»

 

የሩሲያ ጦር ዩክሬንን ከወረረበት ካለፈዉ የካቲት ወዲሕ  ዩናይትድ ስቴትስ  4.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጦር መሳሪያ ለዩክሬን አስታጥቃለች።የአዉሮጳ ሕብረት እና አባል ሐገራቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ጦር መሳሪያ፣ ብሪታንያ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጦር መሳሪያ ለኪየቭ ልከዋል ወይም ለመላክ ወስነዋል።

ካናዳ፣ አዉስትሬሊያ፣ ጃፓንና ሌሎች ሐገራት  በቢሊዮን የሚያወጣ ዶላር ማዋጣታቸዉ ተዘግቧል።

ምስል First Hand Films

 

ምዕራባዉያን አጥኚዎች እንደሚሉት ሩሲያ ለጦርነቱ በየቀኑ ከ6 መቶ እስከ 9 መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ትከሰክሳለች።በሩሲያ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ ደግሞ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት እያሽመደመደዉ ነዉ፣ የባለስልጣኖችዋን ዝዉዉር እያስተጓጎለዉ ነዉ።የሩሲያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭን ያሳፈረ አዉሮፕላን በአየር ክልላቸዉ ላይ እንዳይበር ቡልጋሪያ፣ሰሜን ሜቅዶኒያና ሞንቴኔግሮ በመከልከላቸዉ ሚንስትሩ ዛሬ ቤልግሬድ-ሰርቢያን ለመጎብኘት የነበራቸዉን ዕቅድ ለመሰረዝ ተገድደዋል።

 

ጦርነቱ የምዕራባዉያንን ካዝናም እያጎደለዉ ነዉ።ለጦር መሳሪያና ለወታደራዊ ስልጠና ከሚፈሰዉ ገንዘብ በተጨማሪ በተለይ የሩሲያ ነዳጅ ዘይትና ጋስ ጥገኛ የሆኑት የአዉሮጳ መንግስታት የገጠማቸዉ የዋጋ ንረትና የምግብ ሸቀጦች እጥረት ሕዝባቸዉን እያስመረረ ነዉ።የሐገር ጎብኚዎች ዝዉዉር በመቀነሱም ከኮሮና ወረርሽኝ በቅጡ ያላገገመዉ የኢጣሊያ፣ የፈረንሳይና የስጳኝን የመሳሰሉ የመዝናኛና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተንገዳገዱ ነዉ።

 

አፍሪቃዉያን ገዢዎቻቸዉ፣ የገዢዎቻቸዉ-አሳዳሪዎች  ጫና፤  ብሉሹ አሰራርና ተፈጥሮ ከሚያደርሱባቸዉ ረሐብ በተጨማሪ የዩክሬኑ ጦርነት ፈተና ነዉ የሆነባቸዉ።ጦርነቱና መዘዙ  የዩክሬንና የሩሲያን የስንዴ፣የበቆሎና የቅባት እሕሎችን አቅርቦት በማጎሉ አፍሪቃ ዉስጥ የምግብ ሸቀጥ ዋጋ አለቅጥ ንሯል።አፍሪቃ 44 ከመቶ የሚሆነዉን የስንዴ ቀለቧን የምትሸምተዉ ከሁለቱ ሐገራት ነዉ።የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበርና የሴኔጋል ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ባለፈዉ አርብ ሞስኮ ድረስ ተጉዘዉ የሩሲያዉን ፕሬዝደንት የተማፀኑትም ለዚሕ ነዉ።የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ሶስት አማራጮች እንዳሉ ጠቁመዋል።ከሶስቱ አንዱና «ቀላሉ» ያሉት ምርቱን በቤሎ ሩስ በኩል ወደጪ መላክ ነዉ።«በመጨረሻም በጣም ቀላሉ መንገድ እሕሉን በቤሎሩስ ግዛት በኩል ወደ ዉጪ መላክ ነዉ።በጣም ቀላሉና ርካሹ መንገድ ይሕ ነዉ።ምክንያቱም ከዚያ ወዲያዉ ወደ ቦልቲክ ሐገራት ወደቦችና ወደተፈለገዉ የዓለም ክፍል መላክ ይቻላል።ይሕ እንዲሆን ግን በቤሎሩስ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ መነሳት አለበት።»

ይበሉ እንጂ ዩክሬንን የሚያወድመዉ፣ ሩሲያን ከምዕራቦች ያጋጨዉ፣ ዓለምን የሚያከስረዉ፣ አፍሪቃን ለኑሮ ዉድነት የዳረገዉ ጦርነት የማብቃቱ ተስፋ ላሁኑ ዝግ ነዉ።የኪየቭ ወይም የሞስኮዎች ክንድ እስኪዝል ወይም የዋሽግተኖችና የተከታዮቻቸዉ ዕጅ እኪስያጥር መቀጠሉ አይቀርም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ አሚን አዋድ እንዳሉት በጦርነቱ ጥፋት እንጂ አሸናፊ አይኖር ይሆናል።አትራፊ ግን አለ።የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንዮች።

ምስል Mikhail Klimentyev/IMAGO

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW