1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ያለ ፈተና የፀና ሕልውና የለም» - የኢትዮጵያ የውጭ ገዳይ ሚኒስቴር

ሐሙስ፣ ጥር 9 2016

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪቃ ቀጣና «ያለመረጋጋት ሳይሆን የመረጋጋት መንስኤ ናት» ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ ዛሬ ምላሽ ሰጠ ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ፦ አምበሳደር መለስ ዓለም፦ ግብጽ ኢትዮጵያን የአካባቢው አለመረጋጋት መንስኤ አድርጋ መክሰሷን «ቧልት» ብለውታል።

Äthiopien Ambassador Melles Alem
ምስል Solomon Muchie/DW

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ግንኙነት ላይ የተፈጠረ ለውጥ አለ?

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪቃ ቀጣና «ያለመረጋጋት ሳይሆን የመረጋጋት መንስኤ ናት» ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ለግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  መግለጫ ዛሬ ምላሽ ሰጠ ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ፦ አምበሳደር መለስ ዓለም፦ ግብጽ ኢትዮጵያን የአካባቢው አለመረጋጋት መንስኤ አድርጋ መክሰሷን «ቧልት» ብለውታል። ኢትዮጵያ ራሷን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ ከምትጠራው እና ሶማሊያ የግዛቴ አካላ ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋ የወደብ ጉዳይን በሚመለከት የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል ። የአረብ ሊግ በዚሁ ጉዳይ የሰጠውን መግለጫም አምባሳደር መለስ፦ «ለአፍሪቃውያን ንቀት» ብለውታል ።  በግብጽና በአረብ ሊግ መካከል ያለውን ግንኙነት «የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ» ሲሉ አክለዋል ። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት (IGAD) በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አለመሳተፏንም አረጋግጠዋል።  

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ግንኙነት ላይ የተፈጠረ ለውጥ አለ?

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ለኢትዮጵያ የባሕር በር ፣ ለሶማሊላንድ ከግዙፍ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ድርሻ እንዲሁም እንደ ሀገር ዕውቅና ማግኘት የሚያስችላት የተባለለትን ስምምነት ከተፈራረሙ ጀምሮ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የከረረ ውዝግብ  ተነስቷል።

ብዙ ሀገራት እና ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ ባወጧቸው ተከታታይ መግለጫዎች የሶማሊያ ሉዓላዊነት እንዲከበር ሲያሳስቡ የአፍሪቃ ሕብረት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የተስተዋለውን ውጥረት እንዲያረግቡ ጠይቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ሰሞነኛውን ውዝግብ ተከትሎ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለውጥ ስለመኖር አለመኖሩ በጋዜጠኞች ተጠይቀው "የለም" ብለዋል። "የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የንግድ እንዲሁም የአቪየሽን ግንኙነትን በተመለከተ የተለወጠ ነገር የለም" ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ "የአለመረጋጋት መንስኤ አይደለችም ።"

የምስራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ያገባናል ባዮች በርካቶች ናቸው። በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሰላም አስከባሪዎች ሶማሊያ ውስጥ ለሀገሪቱ መረጋጋት እየሠሩ ይገኛሉ። ሰሞነኛውና ቀጣናውን የበለጠ ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ያደረገው ገዳይ ሀገራቸውን ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ጦርነት ሊያስገባት እንደሚችል የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር መናገራቸው ሥጋቱን አባብሶታል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን የአካባቢው አለመረጋጋት መንስኤ አድርገው መፈረጃቸውን ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ አለም አጣጥለውታል። "ኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ሳይሆን የመረጋጋት መንስኤ ናት ለዚህ አካባቢ" የአረብ ሊግ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ካደረገ በኋላየኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድን ስምምነትበዓለም አቀፍ ደረጃ የተቃጣ ጥቃት አድርጎ ወስዶታል። ለዚህ ቀጥተኛ ምላሽ የሰጡት አምባሳደር መለስ አለም "ለአፍሪካዊያን ንቀት ነው" ብለውታል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘትን ጉዳይ አንገብጋቢ የፍትሕ እና የፀጥታ አጀንዳዋ አድርጋ የያዘችው መሆኑንም ቃል ዐቀባዩ አብራርተዋል። "ጉዳዩ የፍትሕም፣ የርትዕም ፣ የልማትም የሰላምም ጉዳይ ስለሆነ ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ ያስፈልጋታል።"

አወዛጋቢው የበርበራ ወደብ፤ ሶማሊላንድ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Brian Inganga/AP/picture alliance

ኢትዮጵያ በኢጋድ አስቸኳይ ስብሰባ አልተሳተፈችም

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (IGAD) ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በገቡበት ልዩነት ዙሪያ ዛሬ ለመምከር አባል ሀገራቱን ለአስቸካይ ስብሰባ የጠራ ቢሆንም ኢትዮጵያ አለመሳተፏ ተገልጿል።

ሆኖም ኢጋድ ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ድርጅት በመሆኑ እንዲጠናከር እንደሚሰሩ ፣ የድርጅቱ ጥንካሬ ለኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። የኬንያ መንግሥት ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን አዲስ የመግቢያ ፈቃድ እንዲተገበር ከሰሞኑ ወስኗል። የሁለቱ ሀገራት ዜጎች አንዱ ወደሌላው ሲጓዝ የቪዛ ሂደት ቅድመ ሁኔታ አልነበረም። ቃል ዐቀባዩ የዚህ የኬንያ አዲስ ሕግ መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ባይገልፁም ተነጋግረን መፍትሔ የምንሰጥበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት መሠረታዊ "የፀጥታ እና የስትራቴጂ ጉዳይ" መሆኑን የጠቀሱት ቃል ዐቀባዩ "ያለ ፈተና የፀና ሕልውና የለም" ሲሉ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ተከትሎ የደረሰባትን ጫና ገልፀዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገጠመው ችግር መነሻ የተፈጠረው ውዝግብ እንዲፈታ ባንኩ ከመንግሥት ጋር ሰፊ ውይይት እያደረገ መሆኑንም በመግልጫቸው አንስተዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW