ያልተገመቱ ውጤቶች የበዙበት 34ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ
ዓርብ፣ ጥር 24 2016
34ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ዛሬና ነገ የሚቀጥል ሲሆን በዛሬው ዕላት ናይጄሪያ አንጎላን፤ ዴሞክራቲክ ጎንጎ ጊኒን የሚገጥሙ ሲሆን ነገ ቅዳሜ ደግሞ ማሊ ከኒጀር ኮትዲቯር ደግሞ ደቡብ አፍሪቃን ይገጥማሉ። የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጭ ለየት ያሉ ክስተቶችን ያስተናገደ ሆኗል። የተገመቱ ቡድኖችን እየገነደሰ ያልተጠበቁ ቡድኖችን ወደ ፊት እያመራ 8 ቡድኖችን ያፋጠጠው 34ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ብዙ ክስተቶችን የተስተዋለበት ነበር። ለዘገባ ወደ አቡጃን በአውቶቢስ ሲጓዙ የነበሩ ጋዜጠኞች መጠነኛ አደጋ መድረሱን፤ ጊኒ የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ ካሸነፈች በኋላ በዋና ከተማዋ ኮናክሪ ደጋፊዎች በፈንጠዝያ ሲጨፍሩ የሞት አደጋ መድረሱን ጨምሮ ጨዋታው ያልተጠበቀና ለየት ያሉ ክስተቶችን ያስተናገደ እንደነበር የስፖርት ዘጋቢው ኦምና ታደለ ለዶቼቨለ ተናግሯል።
"አዘጋጅዋ ሃገር ኮት ዲቯር በስታድዮም ዝግጅት የተዋጣላት ነበረ። ስታድዮሚሙቹ ሳይጓተቱ ነበር የተጠናቀቁት። ሌላው ደግሞ በተመልካች ብዛትም ካለፉት ሁለት የአፍሪቃ ዋንጫዎች የበለጠ እንደነበር ታይቷል። ሌላው ተጠባቂ ቡድኖች ሩብ ፍጻሜ እንኳን መድረስ ያልቻሉበትና በዚህም እጅግ ልዮ የሚያደርገው ነው።
ለዋንጫ ይደርሳሉ ተብለው ቅድመ ግምት ተሰጥቶባቸው ከነበሩት ቡድኖች መካከል በቀጠር በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ የ4ኛ ደረጃነትን ይዞ በከፍተኛ ብቃትና አድናቆት የጨረሰው የሞሮኮ ቡድን ይገኝበታል። በዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ግን ሞሮኮ በጊዜ ከተሰናበቱት ቡድኖች መሰለፉ ብዙዎችን አስደምሟል።የሞሮኮ ውድቀት " ቡድኑ የዝግጅት ችግር የለበትም። ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ላይ የተሳተፈ ቡድን ነው። ሆኖም ግን ከጎንጎ ጨዋታ በኋላ ችግሮች ነበሩበት። ይህም ዋጋ አስከፍሎታል። " ይላል የስፖርት ጋቢው ኦምና።
ተጠባቂ ከነበሩት ነገር ግን ያልተጠበቀ ውጤት በማምጣት ደጋፊዎቻቸውን ኩም ካደሩጉት ሌላኛው ቡድን የ33ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ አሸናፊ የሰኔጋል ብሔራዊ ቡድን ቢሆንም በጊዚ ከተሰናበቱት ቡድኖች ጎራ መቀላቀሉን ደጋፊዎቹን አሳዝኗል።።
የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ተገማች አለመሆኑን ውድድሩን በጉጉት እንዲካሄድ ካደረጉት ምክንያቶች በዋነኝነት ይጠቀሳል። ከዚህ ቀደም በነበሩት ውድድሮች የሰሜን አፍሪቃ ሃገራት ከምድብ ጨዋታ ሲሰናበቱ እምብዛም እንዳልተለመደ የሚገልጸው የስፖርት ዘጋቢው ኦምና ፍጻሜውም በዚሁ እንደሚቀጥል ያለውን ግምት ይገልጻል። የስፖርት ዘጋቢው ኦምና ታደለ ኮትዲቯር እንደሚያሸንፍ ግምቱን ሰጥቷል። እናንተስ በተለይም በፌስቡክና በቴሌግራም የምትከታተሉን አድማጮች በአስተያየት መስጫው ግምታችሁን እንድታስቀምጡ እንጋብዛለን።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ