1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

ያልታወቁ በራሪ አካላት ምድራችንን እየጎበኟት ይሆን?

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2016

የአሜሪካ የህዋ ሳይንስ ምርምር ተቋም፤ናሳ ገለልተኛ የጥናት ቡድን በማቋቋም ምንነታቸው ያልታወቁ ክስተቶችን /UFO/ በተመከተ ምርመራ እንዲያካሂድ አድርጓል። ናሳ የምርመራ ውጤቱን አስመልክቶ ባለ 33 ገጽ ዘገባ ያለፈው ሀሙስ ይፋ አድርጓል። ለመሆኑ የናሳ ዘገባ ስለ ዩፎዎች ምን ይላል? ያልታወቁ በራሪ አካላትስ ምድራችንን እየጎበኟት ይሆን?

ናሳ በሰሞኑ በምርመራው ሳይንሳዊ ድምዳሜ ላይ መድረስ አልቻለም
ናሳካልታወቁ በራሪ ክስተቶችን ጋር የተያያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክስተቶችን የመረመረ ሲሆን፤ በዚህ ምርመራ መሰረት  ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት ስለመኖራቸው ማስረጃ እንዳላገኘ አስታውቋል። ምስል፦ NASA/ESA/CSA/AFP

አዲሱ የናሳ ሪፖርት ባልታወቁ በራሪ አካላት ላይ

This browser does not support the audio element.


ያልታወቁ በራሪ አካላት በእንግሊዝኛው ምህፃሩ /UFO/የህዋ ሳይንስ ሙህራንን ለበርካታ ዓመታት ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። ከጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ወዲህ በአሜሪካ መንግስት  ምንነታቸው ያልታወቁ የአየር ላይ ክስተቶች በእንግሊዝኛው /Undifined Aerial  phenomena /እየተባሉ የሚጠሩት እነዚህ ክስተቶች ያለፈው ዓንድ አመት   በአሜሪካ በተለዬ ሁኔታ የበለጠ መነጋገሪያ ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ ምንነታቸው የማይታወቅ በራሪ አካላትን  አይተናል የሚሉ የአሜሪካ ወታደሮች፣ የአውሮፕላን አብራሪዎች እና የባህር ሀይል ሰራተኞች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ነው።የቀድሞዋ የአሜሪካ ባህር ሀይል ባልደረባ አሌክሲ  ዲትሪች ክስተቱ ካጋጠማቸው መካከል አንዷ ናቸው።«ስለዚህ ይህ ገጠመኝ በ2004 ዓ/ም ከዛሬ 17 ዓመት ገደማ በፊት አጋጥሞኝ ነበር.።»ብለዋል።
ልክ እንደ ዲትሪች ሶስት ባልደረቦቻቸው በሳን ዲዬጎ ካሊፎርኒያ የባህር ዳርቻ ተመሳሳይ ክስተት አይተዋል። ይህም ሌሎች አብራሪዎች ከተመለከቱት  በርካታ ክስተቶች መካከል ነው።
የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት በየኮቪድ19 ወረርርሽኝ ወቅትም በአሜሪካ በርከት ያሉ  ሰዎች ይህንኑ ክስተት ሪፖርት ማደረጋቸው ተገልጿል።እነዚህን  መሰል  የሴራ ንድፈ ሐሳቦች በአሜሪካ  ለብዙ አሥርተ ዓመታት የዘለቁ ቢሆንም፤ጉዳዩ የበለጠ የተቀጣጠለው አውሮፕላን የሚመስሉ  እና ከሚታወቀው የሰው ልጆች ቴክኖሎጂ በሚበልጥ ፍጥነት  የሚበሩ  ነገሮችን የሚያሳይ በአብራሪዎች የተነቀረፀ  ቪዲዮ በፔንታጎን ከተለቀቀ ወዲህ  ነው።ከዚህ

የሴራ ንድፈ ሐሳቦች በአሜሪካ  ለብዙ አሥርተ ዓመታት የዘለቁ ቢሆንም፤ጉዳዩ የበለጠ የተቀጣጠለው አውሮፕላን የሚመስሉ  እና ከተለመደው በሚበልጥ ፍጥነት  የሚበሩ  ነገሮችን የሚያሳይ   ቪዲዮ በፔንታጎን ከተለቀቀ ወዲህ  ነውምስል፦ Alex Brandon/AP/picture alliance

በመነሳት ዓለማችንን ያልታወቁ በራሪ ፍጡሮች እየጎበኟት ነው የሚሉ ቢኖሩም፤የአሜሪካው የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት ፔንታጎን ግን አይቀበለውም። መስሪያ ቤቱ ሁሉንም  ክስተቶች ያልታወቁ የአየር ላይ ክስተቶች ወይም /UAP/ ከማለት ውጭ ለክስተቱ ምንም ማብራሪያ ሳይሰጥ ለዓመታት  ሚስጥራዊ አድርጎ ያስቀምጣቸዋል።ዲትሪች ግን በእሳቸው እና በባልደረቦቻቸው ገጠመኝ ላይ ተመስርቶ በጉዳዩ ላይ የተለየ ሳይንሳዊ አቀራረብ እና ማብራሪያ እንዲኖር ሀሳብ ያቀርባሉ።
«ተስፋ አደርጋለሁ።ቸልተኝነትን በመቀነስ የታሰበበት እና ጥልቅ መረጃ የተሰበሰበበት ሪፖርት የማቅረብ ሂደትን በማስተዋወቅ ወይም በማበረታታት  የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግ። ስለዚህ ይህ እርምጃ ትንታኔ ለመስጠት ብቁ የሆኑ ግለሰቦች ለእነሱ የሚያስፈልገው መረጃ እንዲኖራቸው ፣ጥልቅ ምርመራ እና ትንታኔ እንዲያካሂዱ እንዲሁም የተወሰነ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ያደርጋል።»የብሩህ ትውልድ መስራቾቹ ጥንድ ሳይንቲስቶች
ያም ሆኖ ጉዳዩ የሚመለከተው የፔንታጎን ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ሾን ኪርፓትሪክ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለሕግ  አውጪዎች እንደተናገሩት  እስካሁን ድረስ ከመሬት ውጭ እንቅስቃሴ፣ ከዓለም ውጪ ቴክኖሎጂ፣ ወይም የታወቁትን የፊዚክስ ህጎች የሚጻረሩ ነገሮች ስለመኖራቸው ተዓማኒነት ያለው ማስረጃ አላገኘንም ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ የቀድሞው ደህንነት መኮንን ዴቪድ ግሩሽ   ለአሜሪካ ኮንግረስ እንደገለፁት የአሜሪካ ባለስልጣናት ምንነታቸው ያልታወቁ  በራሪ አካላትን በተመለከተ  ማስረጃዎችን እየሸፋፈኑ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።በጎርጎሪያኑ ያለፈው ሀምሌ መጨረሻ  የቀድሞ የአየር ሀይል የደህንነት መኮነን ዴቪድ ግሩሽን  ጨምሮ ሶስት የአሜሪካ የቀድሞ ወታደራዊ ባለስልጣናት ታዩ ስለተባሉት ክስተቶች በአሜሪካ ኮንግረንስ ፊት ምስክርነት ሰጥተዋል። ግሩሽ እንደተናገሩት  በስራ ላይ በቆዩበት በርካታ አመታት ስለ UAP ዘገባ ሲደርሳቸው  ቆይቷል። በሰበሰቡት መረጃ መሰረትም ይህንን መረጃ ለአለቆቻቸው እና ሪፖርት አድርገዋል። ስለ መረጃው ዝርዝር አስተያየት ባይሰጡም ግሩሽ በእነዚህ ያልታወቁ አካላት ላይ ቀጥተኛ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በግል ቃለ መጠይቅ እንዳደረጉም ተናግረዋል።  ከብዙዎቹ  አሳማኝ ማስረጃዎችን በፎቶግራ መልክ እና በቃል ምስክርነት ይፋዊ ሰነዶችን መጋራታቸውን አስረድተዋል። 

የአሜሪካ ኮንግረንስ ምንነታቸው ባልታወቁ በራሪ ክስተቶች ላይ ከቀድሞው የአሜሪካ አየር ሀይል ባልደረባ ምስክርነት ሰምቷልምስል፦ Elizabeth Frantz/REUTERS

ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት  ለበረራ ደህንነት ስጋት ናቸው የሚሉት የቀድሞው የአየር ሀይል ባልደረባ ፤ጉዳዩ ከሰው አልባ አውሮፕላን ጋር የሚያያዝ  ከሆነ አስቸኳይ መልስ የሚፈልግ የብሄራዊ ደህንነት ችግር ነው ብለዋል።ሌላ ነገር ከሆነም የሳይንሳዊ ትንታኔ  የሚፈልግ በመሆኑ ባስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በዚህ ሁኔታ  በአሜሪካ ኮንግረንስ ጭምር እያከራከረ ባለው በዚህ ክስተት፤የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ድርጅት በእንግሊዝኛው ምህፃሩ ናሳ፤በዚህ አመት ግንቦት ወር ላይ  በእነዚህ ምንነታቸው ባልታወቁ  ክስተቶች /UAP/ ላይ የመጀመሪያውን ህዝባዊ ስብሰባ አድርጓል።ክስተቱን ለማብራራት የበለጠ ጥብቅ ሳይንሳዊ አቀራረብ እንደሚፈልግ አመልክቷል።
ራቪ ኩማር ኮፖላኩ የተባሉ የናሳ ሳይንቲስት በበኩላቸው በዩፎች ላይ በዘርፉ እስካሁን ምንም የታወቀ ሳይንሳዊ መረጃ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ሳይንሳዊ ጥናት ላይ እንዲተኮር ይፈልጋሉ።
«ከሳይንስ ሊቃውንት እይታ አንፃር ዩፎዎች ምን እንደሆኑ አናውቅም። የዩፎዎችን ምንነት ለማወቅ ትክክለኛ መረጃ በእነሱ ላይ ካልተሰበሰበ በቀር ምን እንደሆኑ ተፈጥሯራዊ ባህሪያቸውን መገመት አንችልም።እናም የኔ ተስፋ  በዩፎዎች ሳይንሳዊ ጥናት ላይ እናተኩር እና  እነሱን ለመመርመር ማንኛውንም ጥርጣሬ እና ግምቶች እናስወግዳለን።»የሩሲያ የዩክሬን ጦርነት ዳፋ በጠፈር ምርምሩ ዘርፍ
ናሳ፤ ከአንድ አመት በፊትም  16 አባላት ያሉት ገለልተኛ የጥናት ቡድን በመመደብ በሰማይ ላይ ታዩ  ስለተባሉት ምንነታቸው ባልታወቁ ክስተቶች ላይ ምርመራ እንዲያካሄድ አድርጓል።ናሳ  ስለ ክስተቶቹ መልስ ይሰጣል ተብሎ  ሲጠበቅ የነበረውን  የዚህን ምርመራ ውጤትም ያለፈው ሀሙስ ይፋ አድርጓል።ናሳ  ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክስተቶችን የመረመረ ሲሆን፤ በዚህ  ምርመራ መሰረት  የተባሉት ምንነታቸው ያልታወቀ በራሪ አካላት ስለመኖራቸው ማስረጃ እንዳላገኘ አስታውቋል።በድርጅቱ ባወጣው ባለ 33 ገጽ ሪፖርት ዩፎዎች ስለመኖራቸው ወይም ስላለመኖራቸው ተጨባጭ ማስረጃ ባያቀርብም ፤ ሙሉ በሙሉ ክስተቶቹን ከጉዳዩ ጋር የሚገናኛቸው ዕድል የለም ብሎ መደምደምም ግን እንደማይቻል ጠቁሟል።

የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ፤ባልታወቁ በራሪ አካላት ላይ ምርመራ አድርጓልምስል፦ John Raoux/AP/dpa/picture alliance

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአስትሮ ፊዚክስ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን በላይ እንደሚገልፁት  በህዋ ሳይንስ ምርምር  ዘርፍ ብዙ ያልተደረ,በት ነገር አለ።እሳቸው እንደሚሉት ያልታወቁ  በራሪ አካላት ጉዳይም ሳይንሳዊ መረጃ ማቅረብ ከማይቻልባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።ከዚህ አንፃር የናሳ ሪፖርት ተቀባይነት አለው ይላሉ። እነዚህ ክስተቶች ለረዥም ጊዜ ሳይንሳዊ ድምዳሜ ያላገኙትም እንደ ዶክተር ሰለሞን ጥልቅ ትንታኔ ላማድረግ የሚያስችል የተሟላ መረጃ ባለመገኘቱ ነው።  
ናሳ በሀሙሱ ዘገባው እነዚህ ክስተቶች ወደ ምድር ለመድረስ ስርዓተ ፀሀይን/solar system/ መዞራቸውን ጠቁሟል።ነገር ግን በክስተቶቹ ላይ ያሉት ምልከታዎች እና የጥናት  ዘዴዎች እስኪሻሻሉ ድረስ ሳይንሳዊ ድምዳሜዎችን መስጠት የማይቻል ነው ሲል  በርካታ  ምሳሌዎችን እንደ ማስረጃ በመጠቀም  አመልክቷል።
ከከፍተኛ ሚስጥራዊ የመንግስት ሰነዶች ይልቅ በመደበኛ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ ናሳ ባቀረበው ሪፖርት  እንዳመለከተው፤ በሰማይ ላይ የታዩ   ፊኛዎች፣ አውሮፕላኖች ወይም የተፈጥሮ ታዋቂ ክስተቶች ተብለው ሊታወቁ የማይችሉ ነገሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ታይተዋል።ከዚህ ባሻገር በሳይንሱ ተቀባይነት ባያገኙም በሜክሲኮም 1800 ዓመት ያስቆጠረ የዩፎዎች ቅሬት አካል መገኘቱን ከሰሞኑ ተገልጿል።
ያም ሆኖ ስለ ክስተቶቹ የሚያስረዱ  ምልከታዎች ውስን በመሆናቸው ፤ ለሚሰራጩት የሴራ ትንታኔዎች  ትክክለኛ ሳይንሳዊ ድምዳሜ ለመስጠት  መረጃዎች እንደሌሉት ናሳ ገልጿል።በመሆኑም የአሜሪካው የህዋ ሳይንስ ምርምር ድርጅት ናሳ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናት ለማካሄድ እና የተሻለ መረጃ ለማግኘት በበይነመረብ መረጃ ለመሰብሰብ አቅዷል።ለዚሁ ጥናት አዲስ የምርምር ሀላፊ እንደሚሾም የገለፀው ናሳ፤ በምድራችን ዙሪያ ምን እየተካሄደ ነው የሚለውን በትክክል ለመመርመርም የላቀ ሳይንሳዊ ዘዴ እና ቴክኖሎጂ  እንደሚጠቀም አስታውቋል። ምክንያቱም ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት  ለበረራ ደህንነት አስጊ ናቸው የሚለው ሀሳብ እየጎላ መጥቷል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW