1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልታየው የቱሪዝም መስህብ፤ የጅማው ሰቃ ፏፏቴ

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2016

በኦሮሚያ ክልል የሰላም ደሴት እየመሰለች በመጣችው ጅማ ዞን ቱሪስቶች ሊጎኟቸው የሚችሉ በርካታ መስዕቦች ይገኛሉ። ከጅማ እጅግ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ሰቃ ፏፏቴ ከፍተኛ የቱሪዝም አቅም ካሏቸው ስፍራዎች አንዱ እንደሆነ ቢጠቀስም እስካሁን ምንም አይነት ጎብኚዎችን የሚስብ መሠረተ ልማት የሌለውና የማስተዋወቅ ሥራም አልተሠራለትም።

ሰቃ ፏፏቴ ጅማ
ጎብኚዎችን ሊስቡ ከሚችሉ የጅማ የተፈጥሮ ሃብቶች አንዱ ሰቃ ፏፏቴ ምስል Seyoum Getu/DW

የጅማው ሰቃ ፏፏቴ

This browser does not support the audio element.

 

በኦሮሚያ ክልል የሰላም ደሴት እየመሰለች በመጣችው ጅማ ዞን ቱሪስቶች ሊጎኟቸው የሚችሉ በርካታ መስዕቦች ይገኛሉ። ከጅማ እጅግ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ሰቃ ፏፏቴ ከፍተኛ የቱሪዝም አቅም ካሏቸው ስፍራዎች አንዱ እንደሆነ ቢጠቀስም እስካሁን ምንም አይነት ጎብኚዎችን የሚስብ መሠረተ ልማት የሌለውና የማስተዋወቅ ሥራም አልተሠራለትም። አሁን አሁን ግን ግን ቦታውን በኢኮ-ቱሪዝም ማዕከልነት በመከለል ስፍራው በመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ወይም የኢንቨስተሮች ዓይን ውስጥ እንዲገባና የሚጎበኝ ስፍራ ሆኖ እንዲለማ ማቀዱን የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ያስረዳል።

«በዚህ በሰቃ ፏፏቴ ቱሪስቶች ይመጣሉ። የአካባቢውም ሰው እየመጣ ይጎበኘዋል። ቢሠራበት ደግሞ ይበጥ ትልቅ የቱሪስት መስዕብ ሊሆን የሚችል ቦታ ነው» የሚሉት በጅማ ዞን ሰቃ ጮቆርሳ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰብስብ አባፊጣ ናቸው። ይህ ከጅማ 18 ኪ.ሜ. ከወረዳው ሰቃ ጮቆርሳ ከተማ ደግሞ 2 ኪሎ ሜትር ገደማ ብቻ ወጣ ብሎ የሚገኘው ስፍራ በደን የተከበበና ከፍተኛ መጠን ያለው ውሀ ከላይ ወደ ታች ሲወርድ በሚፈጥረው ድባብ የተዋበ ነው። ቦታውም የሰቃ ፏፏቴ ይሰኛል። ቦታው ለቱሪዝም መዳረሻነት ከፍተኛ አቅም ያለው ነው።

ይህ ከፍተኛ መጠን ያለውና ፏፏቴን የሚፈጥረው ውሀ ዓመቱን በሙሉ ይፈሳል። የጅማው በኬ ጉዶ ወይም ዲምቱ ሸኮታ ተራራማ ስፍራ ደግሞ መነሻው ነው። ይሕ ተራራማ ስፍራ ወደ ጊቤ ከሚፈሰው ከዚህ ወንዝ በተጨማሪ ወደ ጎጀብና አጋሮ ለሚፈሱ ከፍተኛ መጠን ላላቸው ወንዞችም ቁልፍ መነሻ ነው።

የቱሪዝም ባለሙያው ሰብስብ አባፊጣ በተለይም በክረምት ወቅት በከፍተኛ መጠን የሚጨምረው የሰቃ ፏፏቴ ውሀ ሰውንም የማያስቀርብ ነው ይላሉ። «ክረምት በዚህ አካባቢ ያለው ሜዳ በሙሉ በውሀ ስለሚጥለቀለቅ ማንም እዚህ ድርሽ አይልም» ነው ያሉት።

የሰቃ ፏፏቴ ከጅማ 18 ኪ/ሜ፤ ከወረዳው ሰቃ ጮቆርሳ ከተማ ደግሞ 2 ኪ/ሜ ገደማ ብቻ ወጣ ብሎ የሚገኝ በደን የተከበበ ስፍራ ነው። ምስል Seyoum Getu/DW

ስፍራው የአካባቢው ማኅበረሰብ በጋራ ጊዜውን ለማሳለፍ የሚመርጠው ቦታው ነው። ከጅማ ከተማ መጥታ ከጓደኞቿ ጋር በስፍራው ስትዝናና ያገኘናት ወጣት ኢክራም ማሻዓላህም ቦታው ማራኪ ከመሆኑም ያለፈ መልካም አየርና መዓዛ የሚገኝበት በመሆኑ ብዙ ጊዜያቸውን 18 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘው በመምጣት እንደሚያሳልፉበት ትገልጻለች።  የአካባቢው ተወላጅ ወጣት ማቴዎስ ለገሠም ከከተማ ወደ ዚህ ስፍራ እንግዶች በማመላለስ ገቢም እንደሚያገኝበት ይናገራል።

የሰቃ ጮቆርሳ ወረዳው የቱሪዝም ባለሙያው ሰብስብ አባፊጣ ይህ ስፍራ ቦታውን በሚያውቁት የአካባቢው ማኅበረሰብ እጅግ ተመራጭ ቦታ ቢሆንም ወረዳው ለጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆን አድርጎ ስላልሠራበት እንደ መንግሥት የሚገኝ ገቢ የለም ባይ ናቸው።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን መክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት ደግሞ ይህ ስፍራ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በቱሪስት መዳረሻነት ከተያዙ 18 የኢኮ-ቱሪዝም ስፍራዎች አንዱ ነው። የመሰል ቦታዎች የኢንቨስትመንት አቅም ትልቅ ነው የሚሉት አቶ ነጋ ወዳጆ ኮሚሽናቸው ቦታውን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ሀሳቦቹን ወደ ተግባር የመቀየር ሥራ መጀመሩንም አስረድተዋል።

«ቦታው በኢኮ-ቱሪዝም ስር መግባቱ ለተለያዩ የአገልግሎቶች ግንባታ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ቦታው ለሚመጡ ባለሀብቶች እምብዛም ጭቅጭቅ የማያስነሳ ስለሆነ ተመራጭ ነው» ብለዋልም። ለዚህም ከባለ ድርሻ አካላቱ ጋር ለመዳረሻ ልማቱ በጋራ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW