1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ «ገጸ በረከትነቱ ቀርቶ ሸክም መሆኑ በቀረልን »

ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2017

ግንባታው ተጀምሮ ለአስራ አራት ዓመታት ገደማ ቆሞ የቀረው የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ሃገራዊ ፋይዳው ቀርቶ ከተተከለበት አካባቢ ማህበረሰብ ትከሻ በወረደ ይላሉ ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ። በካሳ የእርሻ መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮች አሁን በተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ነዋሪዎች እና የመስተዳድር አካላት አረጋግጠዋል።

Äthiopien Yayo 2025 | Gescheiterte Düngemittelfabrik in der Region Oromia als Symbol für Industrieprobleme
ምስል፦ Privat

የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ከሀገር ኪሳራነት ወደ አካባቢያዊ ሸክምነት

This browser does not support the audio element.

የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውሱ

አቶ አብዶ ይባላሉ በኢሉ አባቦራ ወረዳ ያዮ ወረዳ የዊጠቴ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው ። 100 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የያዮ የማዳበሪያ ፋብሪካ በቀበሌያቸው መገንባት ሲጀምር በስፍራው ነበሩ ። ምንም እንኳ ፋብሪካው ያረፈበት መሬት የርሳቸውን ባለመንካቱ የመነሳት ስጋት ባይኖርባቸውም በሌሎች ላይ የሆነውን እና የደረሰውን በቅርበት ለመታዘብ ችለዋል። 
« የመጀመሪያ ካሳ እንደወሰዱ ፧ካሳው በቂ አይደለም ተብሎ በድጋሚ እንዲታይላቸው ተደርጎ ነበር ። ነገር ከጊዜ በኋላ ካሳውን የወሰዱትም ገንዘቡን ጨርሰው እንዳይሆን ነው ያሉት፤…ከእነርሱ ውስጥ ትንሽ ራሳቸውን ለመቻል የሞከሩ ከሁለት እና ሶስት ሰዎች አይበልጡም»
ለተመሳቀለ ማህበራዊ ህይወት ከተዳረጉ አርሷደሮቹ ውስጥ ህይወታቸውን እስከ ማጥፋት የደረሱ እንደነበሩ አቶ አብዶ ይናገራሉ ።
« በዚሁ ምክንያት ራሳቸውን ያጠፉ ሶስት ሰዎችም አሉ ።

የያዮ የድንጋይ ከሰል እና የጥቅም ግጭት

የብሔራዊ ሐብት ብሔራዊ ኪሳራ

አቶ ማቴዎስ በቀለ የግብርና እና የተፈጥሮ ባለሞያ ናቸው ።ነዋሪነታቸው እዚህ ጀርመን ቢሆንም የአካባቢው ተወላጅ ናቸው። የፋብሪካው ቆሞ መቅረት ያደረሰውን ማህበራዊ ኪሳራ ይገልጻላሉ።
« የአካባቢው ማህበረሰብ ከአርሶአደርነት ወደ ቀን ሰራተኛነት ተቀይሮ ህይወቱ ከነበረበት በታች አዘቅት ውስጥ ገብቶ እየኖረ ነው። ሀገሪቱም ያንን ሁሉ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሳ ያለውጤት ቀርታለች »
ኢትዮጵያ በምዕተ ዓመቱ መባቻ የመጀመሪያው ምዕራፍ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ አካል የሆነው የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ በ2004 ዓመት ነበር ግንባታው የተጀመረው ። በወቅቱ በ11 ቢሊዮን ብር ወጪ በሁለት ዓመታት ውስጥ ግንባታዉን አጠናቆ ለማስረከብ ውል የያዘው ደግሞ የብሔራዊ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ (MetEC) ነበር ።
በወቅቱ የበርካታ ስኳር ፋብሪካዎችን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ወስዶ የነበረው ሜቴክ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የተጨማሪ 9 ቢሊዮን ብር ቢጠይቅም ስራውን በፍጹም ወደ ፊት ማራመድ ሳይቻለው ቀርቷል። 

ኢትዮጵያ በምዕተ ዓመቱ መባቻ የመጀመሪያው ምዕራፍ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ አካል የሆነው የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ በ2004 ዓመት ነበር ግንባታው የተጀመረው ።ምስል፦ Privat

የፋብሪካው በቆመበት መቅረት ከዊጠቴ ቀበሌ እስከ ሀገር ያደረሰው እና እያደረሰ ያለው ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳት ቀጣይነት አሳሳቢ ሆኗል።
አቶ አጂቡ ከድር የያዮ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ ናቸው ። እርሳቸው እንደሚሉት የፋብሪካው ግንባታ ተቋርጦ መቅረት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ካደረሰው ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳት ባሻገር ወረዳውን ለተጨማሪ አስተዳደራዊ ወጭ ዳርጎታል።
« እንደ መንግስት ብረታብረትን ጨምሮ በብዙ ሚሊዮን  ብር የሚቆጠር የተለያዩ ንብረቶች በስፍራው ተከማችተው ስለሚገኙ ንብረቶቹ ለስርቆት ስለሚጋለጡ የማስጠበቁ ኃላፊነት በእኛ ላይ ወድቋል። የወረዳውንም በጀት በከፍተኛ ሁኔታ ወስዶብናል።»

ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ከያዮ እና ድሬዳዋ በዳንጎቴ ኢንቨስትመንት ፊቷን ወደ ጎዴ አዞረች

የፋብሪካው በጅምር መቅረት የጤና ጠንቅም ፈጥሯል።
የፋብሪካው ቆሞ መቅረት መዘዝ በዚህ ብቻ አያበቃም የሚሉት እኚሁ የአካባቢው ባለስልጣን ፤ ለግንባታው የተቆፋፈሩ መሬቶች ለውሃ ማቆር መጋለጣቸውን ተከትሎ ሌላ የጤና ስጋት ይዘ,ው መጥተዋል ይላሉ ።

« በብዙ ቦታ ላይ የተቆፋፈርው መሬት ዉሃ ቋጥሮ ለወባ መራቢያ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ የአካባቢውን ህዝብ ለበሽታ አጋልጧል፣፤ እኛንም እንደ ወረዳ ለተለየ ወጭ ዳርጎናል።» 
አቶ ማቴዎስ የፋብሪካውን ወቅታዊ ሁኔታ በአይን ካዩት ምስክርነታቸውን ሲገልጹ በአንድ ወቅት ከህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት ባክኖ መቅረት አሳዛኝ ነው ይላሉ።
«ከአንድ ከሁለት ሶስት ወር በፊት እዚያ ነበርኩ ቤተሰቦቼም እዚያ ስላሉ ፤ አይዜ የሚያሳዝን ነገር ነው። ሳር በቅሎበት ፣ የተገነቡ ህንጻዎች ፈርሰው ፣ እዚያ የሚገኙ ቁሳቁሶች ዝገው ፣ ሌላው ደግሞ በተደራጁ ኃይሎች ተሰርቀው ማየት የሚያሳዝን ነው።»
 በርግጥ ነው የያዮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመር ሲሰማ በወቅቱ ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለምታወጣ ሀገር እፎይታን ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ፋብሪካው በሚገነባበት አካባቢ ያለው ማህበረሰብም ለአካባቢው ጥሩ የዕድገት ተስፋ ሰንቆ ነበር ። 

ሞሮኮ በ2.3 ቢሊዮን ዶላር በድሬዳዋ ፋብሪካ ልትገነባ ነው

ሸክምነቱ ይነሳልን ፤ ነዋሪዎች
አቶ አብዶ እንደሚሉት በወቅቱ በትምህርት ላይ ያሉ ልጆቻችን ደርሰው በፋብሪካው በሞያቸው ተቀጥረው ህይወታችንን ይቀይራሉ የሚል ተስፋ ሰንቀው እንደነበር ነው ። አሁን ከአስራ ምናምን ዓመታት በኋላ ግን ያ ያለሙት የለም።
«ፋብሪካው ቢጀምር ልጆቻችን የስራ ዕድል ያገኙልንናል ብለን ነበር። ያ ግን አልሆነም ፋብሪካውም በቆመበት ቀረ። በዚያን ጊዜ ተስፋ ያደርግንባቸው ልጆቻችንም አሁን የልጆች ወላጆች ሆነው ከእኛ ጋር ናቸው። » 
የያዮዋ ዊጠቴ ቀበሌ በአንድ ወቅት ሀገር ተስፋ ጥላበት በነበረው ግዙፍ ፕሮጀክት ተስፋ አድርጋ ነበር ። አሁን ያ ተስፋ ደብዝዟል። የአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ መስተዳድሩ የፋብሪካው ገጸበረከትነት ቀርቶ ሸክሙ በተነሳልን ግን ፈጣን መልስ የሚሻ ጥያቄያቸው ነው። 

ታምራት ዲንሳ 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW