1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ያደገው ዓለም የዘነጋው የቆዳ በሽታ «ቁንጭር»

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2016

በረሃማ አካባቢ በብዛት ያጋጥማል። ከደን መመናመን ጋር ተያይዞ ግን በአሁኑ ጊዜ ወትሮ በማይታይበት አካባቢም መከሰት ጀምሯል። በተለያየ አካባቢ አጠራሩ ቢለያይም ቁንጭር በመባል ይታወቃል። በመላው ዓለም በየዓመቱ ወደ 12 ሚሊየን ሰዎችን ያጠቃል የቆዳ በሽታ ነው። ያደገው ዓለም ግን ዘንግቶት ምርምር አያደርግበትም፤ መድኃኒትም አልተገኘለትም።

ሳንድፍላይ የተሰኘችው በራሪ ነፍሳት
ሌስማንያሲስ ወይም ቁንጭር በመባል የሚታወቀውን የቆዳ በሽታ የምታስከትለው በእንግሊዝኛው ሳንድፍላይ የተሰኘችው በራሪ ነፍሳትምስል፦ picture-alliance/dpa/CDC/F. Collins

ያደገው ዓለም የዘነጋው የቆዳ በሽታ «ቁንጭር»

This browser does not support the audio element.

በተለያየ አካባቢ አጠራሩ የሚለያየው የቆዳ በሽታ «ቁንጭር»

በረሃማ አካባቢ በብዛት ያጋጥማል። ከደን መመናመን ጋር ተያይዞ ግን በአሁኑ ጊዜ ወትሮ በማይታይበት አካባቢም መከሰት ጀምሯል። በተለያየ አካባቢ አጠራሩ ቢለያይም ቁንጭር በመባል ይታወቃል። በመላው ዓለም በየዓመቱ ወደ 12 ሚሊየን ሰዎችን ያጠቃል የቆዳ በሽታ ነው።

ባሕራን የተባሉ የዶቼ ቬለ አድማጭ ናቸው ዛሬ የቆዳ ህክምና ባለሙያ እንድናነጋግር ምክንያት የሆኑን። ከሳምንታት በፊት ከአድማጫችን የተላኩት ጥያቄዎች ሁለት ነበሩ፤ እናቴን እያጠቃ ነው በሚል ስለአጥንት መሳሳት ችግር ላቀረቡት ባለፈው የዘርፉን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ በማነጋገር በቂ ማብራሪያ ማቅረባችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ እሳቸው ጨንቁር ብለው የጠሩት፤ ሌሎች ስለተጠቀሰው የቆዳ በሽታ እናውቃለን ያሉኝ ደግሞ ጭንቁር ስላሉት ሆኖም ግን የቆዳና አባላዘር በሽታዎች ከፍተኛ ሀኪምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አኒሳ በፈቃዱ በሳይናሳዊ መጠሪያውና በይፋ ይታወቅበታል ባሉት ስያሜ ስለገለጹት የቆዳ በሽታ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናል።

የበሽታው መጠሪያና አመጣጥ

ዶክተር አኒሳ በፈቃዱ በቆዳና አባላዘር በሽታዎች ከፍተኛ ሀኪምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። በእንግሊዝኛው ኪውታኒየስ ሌሽማኒያሲስ ተብሎ የሚጠራው ይህ የቆዳ በሽታ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ቁንጭር ተብሎ እንደሚጠራ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ቁንጭር ተብሎ የሚታወቀው የቆዳ በሽታ በዋነኝነት ሌሽማኒያ ኢትዮፒካ በሚባል ተሐዋሲ አማካኝነት እንደሚመጣም ነው የገለጹት። በሽታው በእንግሊዝኛ ሳንድ ፍላይ በተብለው በሚጠሩ በራሪ ነፍሳት ንክሻ ወይም ንድፊያ አማካኝነት እንደሚመጣ ያመለከቱት ዶክተር አኒሳ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ሀገሪቱ በምትጎራበትበት አካባቢ፤ በደቡብም እንዲሁ ከኬንያ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ፤ ከዚህ በተጨማሪም በመሀል የሀገሪቱ ክፍል አልፎ አልፎም በሸዋ በብዛት እንደወረርሽኝ ሁሉ እንደሚከስትም አመልክተዋል።  

ዶክተር አኒሳ እንደገለጹት በሽታው በተጠቀሱት ነፍሳት በመነደፍ ወይም በመነከስ ነው የሚመጣው። በራሪዎቹ ነፍሳት ሲነድፉ በሽታውን የሚያመጣው ተሐዋሲ ወደሰው ቆዳ ይገባል። የተጠቀሰው የጤና ችግር ቆዳ ላይ የሚከሰት ይሁን እንጂ ተሐዋሲው የውስጥ ደዌም ያስከትላል ነው የሚሉት ዶክተር አኒሳ።

በሌሽማንያሲስ ወይም ቁንጭር በተሰኘው የቆዳ በሽታ የተጎዳ አካልፎቶ ከማኅደር ምስል፦ CAVALLINI JAMES/BSIP/picture-alliance

የበሽታው ምልክቶች

በተጠቀሰችው በሽታ ተሸካሚ ነፍሳት የተነከሰ ሰው የተለያዩ የህመም ዓይነቶች በበሽታው ምልክትነት ሊታዩበት ይችላሉ። የነፍሳቷ ንክሻ እንደተፈጸመበት የሰውነት ክፍልም ሊለያይ ይችላል። መረጃዎች እንደሚሉትም የአተነፋፈስ ችግር፤ ውሎ አድሮ ለመዳን ረዥም ጊዜ የሚወስድ ቁስል የሚያስከትል የቆዳ ላይ እብጠት፤ የአፍንጫ መጠቅጠቅ፣ የንፍጥ መብዛት እንዲሁም የአፍንጫ መድማት፤ ጉሮሮ ላይም የመዋጥ ችግር፤ የአፍ ውስጥ ቁስለት፤ ምላስ፤ ድድ፣ ከንፈር፣ የውጭና የውስጥ የአፍንጫ መቆረጥና የመሳሰሉት የዚህ የጤና ችግር መገለጫዎች ናቸው። ይህ ከላይ የሚታይ በዚህ በሽታ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን ከቆዳም አልፎ የውስጥ ደዌ የሚሆንበት አጋጣሚም እንዳለ ነው ባለሙያው ያመለከቱት።

ቁንጭር፤ ዓለም የዘነጋው በሽታ

በዚህ የቆዳ በሽታ እጅግ በርካታ ሰው እንደሚጠቃ ነው ዶክተር አኒሳ ያመለከቱት። በዓለም ደረጃ በዓመት 12 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ በዚህ የቆዳ በሽታ ይጠቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በጤና ተቋማት ደረጃ በተወሰደ መረጃ መሠረት እስከ አምስት ሺህ እንደሚደርሱ ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ አብዛኛው ሰው ወደ ጤና ተቋማት ሳይመጣ በባህላዊ መንገድ እንደሚታከም በማመልከት፣ ቁጥሩ ቢሰላ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችልም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ቁንጭር ምንም እንኳን በርካታ ሚሊየኖችን በየዓመቱ ለጉዳት ቢዳርግም ከተዘነጉ የበሽታ ዓይነቶች አንዱ በመሆኑ ያደጉትን ሃገራት ቀልብ ያልሳበ ብዙም ምርምር ያልተደረገበት በዚህም ምክንያት መድኃኒት ያልተገኘለት የቆዳ በሽታ ነው። በዚህ ላይ ምርምር ካካሄዱት አንዱ የሆኑት ዶክተር አኒሳ መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርሰውን ጉዳት በማስተዋል ትኩረት ሰጥተው ምርምር እንዲካሄድበትና መድኃኒቱ እንዲፈለግ እንዲያደርጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ለጥያቄዎቻችን ምላሽ ለመስጠት የተባበሩንን ዶክተር አኒሳ በፈቃዱን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW