1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ያገረሸው የኢቦላ ወረርሽኝ በኡጋንዳ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 19 2015

የኢቦላ በሽታ በኡጋንዳ በፍጥነት እየተስፋፋ ሲሆን የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር እንዳስታወቀው በሽታው በሀገሪቱ ዋና ከተማ ካምፓላም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።በዚህ የተነሳ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። የሀገሪቱ ባለስልጣናት ግን በሽታው በቁጥጥር ስር ነው ይላሉ።

Uganda Ausbruch von Ebola
ምስል፦ Nicholas Kajoba/Xinhua News Agency/picture alliance

በኡጋንዳ እስካሁን ክ100 በላይ ሰዎች በኢቦላ ተይዘዋል።

This browser does not support the audio element.


ተላላፊው የኢቦላ በሽታ በኡጋንዳ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው።የሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር እንዳስታወቀው በሽታው በሀገሪቱ ዋና ከተማ  ካምፓላም የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።በዚህ የተነሳ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋትም እየጨመረ ነው። የሀገሪቱ  የጤና ባለስልጣናት ግን በሽታው በቁጥጥር ስር ነው ይላሉ።
ተላላፊው የኢቦላ በሽታ በኡጋንዳ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው።በሽታው ቀስበቀስ ወደ ዋና ከተማዋ ካምፓላም እየተዛመተ ነው። የኡጋንዳ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጄን ሩት አሴንግ በሳምንቱ መጀመሪያ  ዘጠኝ ተጨማሪ ሰዎች በኢቦላ ተዋህሲ መያዛቸውን አስታውቀዋል። በካምፓላ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ48 ሰአታት ውስጥ ወደ 14 ከፍ ብሏል። ባለፈው ረቡዕ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወጣው ይፋዊ መረጃ መሰረት በኡጋንዳ ወረርሽኙ ከጀመረ ከአንድ ወር  ወዲህ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ109 በላይ ሰዎች በተዋህሲው ተይዘዋል። ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ 36 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። 
ይህንን ተከትሎ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሙቤንዴ እና  አጎራባች የካሳንዳ ወረዳ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል አዘዋል። የተዋህሲውን ስርጭት ለመግታት በእነዚህ ወረዳዎች የጭነት እና የመንገደኞች እንቅስቃሴ ላይ እገዳው ከጥቅምት 16 ጀምሮ ተግባራዊ ሲሆን ለ21 ቀናት እንዲቆይ ተወስኗል።
በዙሪያው ያሉ ጎረቤት ሀገራትም ስጋት ውስጥ ገብተዋል። በቅርቡ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ከኡጋንዳ ጋር በሚኖራቸው ድንበሮች ላይ ኢቦላን ለመከላከል የሚደረገውን ክትትል ቀስ በቀስ ጨምረዋል። 
በካምፓላ የሚገኙ ባለስልጣናትም ነፃ የስልክ ጥሪ እና ሁለት የዋትስአፕ ቁጥሮች በማዘጋጀት በበሽታው ስለ ኢቦላ መረጃ ለማግኘት ተዘጋጅተዋል።  በኡጋንዳ የሚታተመው "ዘ ዴይሊ ሞኒተር" ጋዜጣ በበኩሉ ታማሚዎችን በፍጥነት  ወደ ካምፓላ ሆስፒታሎች ለማድረስ ተጨማሪ አምቡላንሶች መዘጋጀታቸውን ዘግቧል።
ያም ሆኖ እስካሁን ድረስ በዋና ከተማዋ ካምፓላ ገደቦች  አልተጣሉም።.የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አሴንግ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ሰኞ  እንደተናገሩት "በካምፓላ ያለው ሁኔታ አሁንም በቁጥጥር ስር ነው። እናም የሰዎችን የመንቀሳቀስ ነፃነት የምንገድብበት ምንም ምክንያት የለም" ብለዋል።የኡጋንዳ  የህብረተሰብ ጤና ክፍል ኃላፊ ዳንኤል ጄ. ኪባይንዜ እንደተናገሩት በሽታውን የሚያስተላልፉት ምልክት ያለባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። 
«በካምፓላ ሁሉም በኢቦላ  መያዛቸው ከተረጋገጠ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ዝርዝር  ቀደም ሲል በባለሥልጣናት ዘንድ ይታወቃሉ።በሽታው እንዳይዛመት በለይቶ ማቆያ ይቀመጣሉ።  ወይም ክትትል ይደርግላቸዋል።ስለዚህ በሽታው በካምፓላ ከምናውቃቸው ሰዎች ዝርዝር ወጭ አይሄድም። በሽታውን የሚያስተላልፉትም  ምልክት የታየባቸው ሰዎች ብቻ  ናቸው።»
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) በኡጋንዳ የሚገኙ የጤና ባለሥልጣናት የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል በአንፃራዊነት በደንብ የተዘጋጁ ናቸው። ሀገሪቱ ተዋህሲውን ለመለየት የሚያስችል የቤተሙከራ ፣ የክትትል ፕሮግራም እና የሰለጠኑ ባለሙያዎች አሏት።ብሏል።ይህም የካምፓላ ነዋሪዎቸነ በበሽታው የመያዝ ስጋት ቀንሷል ።
ቀደም ሲል በከተማዋ ውጥረት ነግሶ የነበረ ቢሆንም የካምፓላዋ ነዋሪ ዲያና ናንሱኮመንቦሳ  የደህንነት ስሜት ይሰማታል።
«መንግስት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ብዬ አስባለሁ።በአሁኑ ጊዜ ስለ ወቅታዊው ወረርሽኝ ስጋት የለኝም።በደንብ እየተያዘ ነው ብዬ አስባለሁ።»
ኡጋንዳ በ2000 ዓ/ም የተከሰተውን እና  ከ200 በላይ ሰዎችን የገደለውን ጨምሮ በርካታ የኢቦላ ወረርሽኞች የተከሰቱባት ሀገር ነች።እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ  ከአስር አመታት ወዲህ በኡጋንዳ  ሱዳን የተባለው  የኢቦላ ዝርያ ሲታወቅ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ምንም እንኳን ለዚህ  አይነቱ የተለዬ ተዋህሲ እስካሁን ምንም አይነት ክትባት ባይኖርም ጉዳዮችን አስቀድሞ ማወቅ እና ምልክቶችን ማከም የመዳን እድልን በእጅጉ ይጨምራል። ኢቦላ በቀጥታ የአካል ንክኪ የሚተላለፍ ሲሆን ብዙ ጊዜ ከፍተኛ ትኩሳት እና የውስጥ ደም መፍሰስን ያስከትላል።
በጎርጎሪያኑ  2014-16 ዓ/ም በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ደግሞ ከ11,000 በላይ ሰዎችን ገድሏል።ይህም እስካሁን በበሽታው የተመዘገበ ከፍተኛ የሞት መጠን ነው።
ኢቦላ በ1976 ዓ/ም በደቡብ ሱዳን እና በኮንጎ ኢቦላ ወንዝ አቅራቢያ ባለ መንደር ውስጥ የተከሰተ ሲሆን የበሽታው ስያሜም ከዚሁ መንደር የተወሰደ ነው። 
የሳይንስ ሊቃውንት የኢቦላን መነሻ እስካሁን በውል አያውቁትም። ነገር ግን በተዋህሲው የተያዘው የመጀመሪያው ሰው በበሽታው ከተያዘ እንስሳ ጋር በመነካካት ወይም የዚህን እንስሳ ጥሬ ስጋ በመብላት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።

ምስል፦ Hajarah Nalwadda/Xinhua/picture alliance
ምስል፦ AP
ምስል፦ Hajarah Nalwadda/Xinhua/picture alliance

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW