1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያ ትውልድ ተቋም የኢትዮጵያ አብዮትን 50ኛ ዓመት ዘከረ

እሑድ፣ የካቲት 17 2016

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው “ያ ትውልድ” የተባለ ተቋም 50 ዓመት የሞላውን የኢትዮጵያ አብዮት የሚዘክር መርሐ-ግብር ባለፈው ሣምንት አዘጋጅቶ ነበር። ንጉሣዊውን ሥርዓተ መንግሥት ከሥልጣን ባወረደው እንቅስቃሴ የተሳተፉ አብዮተኞች በታደሙበት ውይይት የዘመኑ ዋና ዋና ጥያቄዎች ተነስተዋል።

 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ
በየካቲት 1966 የተቀሰቀሰው አብዮት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከአምስት ወራት በኋላ ከሥልጣን አውርዷልምስል World History Archive/picture alliance

ያ ትውልድ ተቋም የኢትዮጵያ አብዮትን 50ኛ ዓመት ዘከረ

This browser does not support the audio element.

በያዝነው የካቲት ወር፣የ1966 የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ከፈነዳ 50 ዓመት ደፈነ።ይህን የ1966 የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት እዚህ በአሜሪካ የሚገኘው የ"ያ ትውልድ ተቋም" የወርቅ ኢዮቤልዩ  በዓሉን አስመልክቶ ሰሞኑን የዙም ስብሰባ አካሄዷል።

አቶ ነሲቡ ስብሐት፣ የ" ያ ትውልድ ተቋም" የቦርድ ሊቀመንበርና ዳይሬክተር ናቸው። "ሃምሣ ዓመት ቀላል አይደለም፤የወርቅ ኢዮቤልዩ እንለዋለን። እኛ ደግሞ በዚያ ጊዜ፣በሀገር ውስጥም በውጭም ያለን፣የተማሪው ወታደሩም  የኅብረተሰቡ ክፍል ያ እንቅስቃሴ ላይ በአንድ ላይ ነው የተነሳው የተማሪውም በለው የፖለቲካ ድርጅት የለም በእዚያን ጊዜ ወይም በደንብ አይታወቁም።"

ይኸው የሃምሣኛው ዓመት ዝግጅት ዓላማውም፣ በወቅቱ የነበረውን ህዝባዊ ቁጣ በማስታወስ፣ የካቲት ምን አሉታዊ እና አዎንታዊ ገጽታዎች እንደነበሩት ለመዳሰሰስ መሆኑን አቶ ነብዩ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል።

50 ዓመታት፦ የኢትዮጵያ አብዮት ውርስ ምንድነው?

"እንግዲህ የካቲት 1966 ስትል ዋናው ምንድነው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሃገሪቷ ውስጥ ትልቅ ለውጡ ተሳካ አልተሳካ የተፈለገው ለውጥ መጣ አልመጣ፣ ግን ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነው።ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት በዚያ መኻከል አንዳንድ እክሎች ቢገጥማትም፣የተዳደረችው በንጉሣዊ በዘውድ አገዛዝ በዚያ መልክ ነው የሄደችው።በየመኻል ያሉት እንደእነ ዩዲት ጉዲት ዘመን እንደግራኝ መሐመድ ዘመን፣ እንደ የጣሊያን ወረራ፣የመሳፍንት ዘመን እንደእዛ ብለን መሐል መሐል ቢገባም በተዋረድ ግን የሦስት ሺ ዓመት ታሪክ ከእዛን ጊዜ ጀምሮ በንግስና ከአንዱ ወደ አንዱ እየተሸጋገረ ነው የመጣችወ እና ይኼ የንግስ የዘውዳዊ ስርዓት ሙሉ በሙሉ የተበጠሰበት ወቅት ነው የየካቲት 1966 እንቅስቃሴ።"

የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ

በዝግጅቱ ላይ የኢህአፓ መስራች የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ፣ የካቲት 1966ን በወፍ በረር በቃኙበት ገለጻቸው፣ በወቅቱ ስለተነሳው የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ የሚከተለውን ተናግረዋለን።
"ኢትዮጵያን ሰቅዞ ከያዙ ጉዳዮች መኻከል፣ይህ የብሔረሰብ ማለትም  ማለትም የማንነት ጥያቄ አንዱ በመሆኑ፣በ1966 ዓ ም ከተነሱ ጉዳዮች መኻከል አንዱ ሆነ። የተማሪው ንቅናቄ 1961 ዓ.ም ጀምሮ ያቀነቀነው ይህ ጥያቄ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል።"
በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው በበኩላቸው የየካቲት 1966 እንቅስቃሴን አስመልክቶ የሚከተለውን ተናግረዋል።

አጼ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን የወረዱት በመስከረም 1967 ነበር። ምስል privat

"ይህ ኢትዮጵያን በተለያዩ የታሪኩ ወቅቶች ውስጥ ያስቀመጠ ቀን ነው። ማለት ኢትዮጵያ ትተዳደርበት የነበረው ዘውዳዊ ስርዓት እና ባለአባታዊ መንግስት እንዲቀር የተማሪው ፍላጎት ባይሆንም፣ በወታደራዊ አምባገነንነት ከዛም ደግሞ በዘረኞች እና ጎሰኞች የጎሳ ክልል ውስጥ እንድንተዳደር የመጣበት ጊዜ ነው።"

የኢትዮጵያ አብዮት አርባኛ ዓመትና ፖለቲካዋ

የየካቲት 1966 ጥያቄዎች

ከ ያ ትውልድ ተቋም አቶ ለይኩን ካሣሁን፣በወቅቱ ሲቀነቀኑ የነበሩ ዋና ዋና ጉዳዮችን ቃኝተዋል። "ስለፊውዳል አስተዳደር፣ምን ዓይነት አስተዳደር እንደሆነ፣ስለፊውዳሊዝም ዐይተናል በደንብ።የበላይ ዘለቀ የመገደል ጉዳይ፣በውይይቱ ውስጥ የነበረ ነው።በዘመድ ነው ስራ የሚገኘው የሚባሉ ጉዳዮች ነበሩ።የጎጃም ገበሬዎች ንቅናቄ ነበር።የመንግስቱ ንዋይ ግልበጣ ነበር።የኮሪያ ዘማቾች ገንዘብ ተከልክለው ያካሄዱት የነበረውን አቤቱታ እናውቃለን። ሳንሱር የሚባል ነገር ነበር ማንም ጽሁፍ አይወጣም በቀላሉ።ከዛም በተረፈ የነአበበ ቢቂላ በማራቶን ማሸነፍ፣ የአሜሪካ ፒስ ኮር አስተማሪዎች መምጣት አስተማሪዎች መምጣት የመሳሰሉ ነገሮች፣ የሱማሊያ ጦርነት  የብሄራዊ ስሜታችን ያሳደጉና ያጎለበቱ ነበሩ።" 

የዶይቸ ቨለ ሚና

በዚሁ ዝግጅት ላይ  በቀረቡ ሌሎች በርካታ ጽሁፎች ፣ የአብዮቱ ጉዞ ፍጻሜ ምንም ይሆን ምን፣አብዮቱ በሃገራችን ትልቅ የሆነ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ፣ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ መሠረት የነበረውና፣ የብዙ ወገኖችን ህይወት ያስገበረ የኢትዮጵያና ህዝቦቿ የታሪክ አካል መሆኑ ተወስቷል።
የየካቲት 1966 አብዮት አምሳኛ ዓመትን አስመልክቶ በተዘጋጀ ክብረ በዓል ላይ፣ የጀርመኑ ዓለም አቀፍ ሬዲዮ ጣቢይ ዶይቸ ቨለ የአማርኛው አገልግሎት በወቅቱ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን ቁልፍ ሚና መጫወቱ ተነስቷል። 
ታሪኩ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW