ይርጋለም፦የግዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ብሶት
ዓርብ፣ ሰኔ 5 2012
ይርጋለም ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የሐዋሳ ዮንቨርስቲ አዳዋ ካምፓስ ሰሞኑን የደረሱን ፎቶዎች እና ቪዲዮ ለማመን ያዳግታሉ። ካምፓሱ የለይቶ ማቆያ ሆኗል። በውስጡም በአንድ ቦታ ተሰብስበው የቆሙ በርካታ ወጣቶች ፣ ብርድ ልብስ እና አንሶላ የሌላቸው ባዶ አልጋዎች፣ በየቦታው የተጣሉ የውኃ መጠጫ ላስቲኮች እና ሌላም ሌላም ይታያሉ። « ዩንቨርስቲ ውስጥ የተዘጋ በር ከፍተው ነው ያስገቡን። የተዘጋጀ ነገር አልነበረም። እንደተሳፈርንበት መኪና ለይታችሁ አስቀምጡን ብለን ጠይቀን ነበር።ለዛ ፍቃደኛ አልነበሩም። እንደዚህ አይነት ጥያቄ ለሚያነሳም ከፖሊስ ዱላ ነበር። አንድ ክፍል ውስጥ በአካማይ ከአራት እስከ ስምንት ሰው አለ። ለ 11 ቀን ሙሉ የቧንቧ ውኃ አልነበረም። » ቃለ መጥይቅ ያደረግንላቸው ሰዎች ለደህንነታቸ ሲባል ስማቸውን እንዳንጠቅስ ጠይቀውናል። ዶርም ውስጥም ምንም ቁጥጥር የለም። ሰውም እንደልቡ ይንቀሳቀሳል። አብዛኞቹ ወደዚህ ማቆያ የገቡት ሰዎች እንደገለፁልን ኑሮዋቸውን በዚህ አይነት ሁኔታ ሲገፉ 13 ቀናት ሆኗቸዋል። ወንድ እና ሴቶች በተለያየ ዶርም ነው የሚገኙት። ሴቶቹ ጋር ያለው ሁኔታ ጭራሽ ይባስ የሚያስብል ነው። « ልብስ የለም ፣ ሞዴስ የለም። ብርድ ልብስ የለም።» ትላለች የአካባቢው ነዋሪ የሆነችው ወጣት።
ሌላዋ ነፍሰ ጡር እንደሆነች የገለፀችልን ሴት ደግሞ ከዚህ በፊት ለአምስት ቀን ሌላ ማቆያ ከቆየች በኋላ ነው ወደ አዋዳ ካምፓስ የተዛወረችው። እሷ እንደምትለው በፊት ከነበረችበት ጭራሽ የባሰ ነው። ነፍሰ ጡሯ እንደምትለው ፅንስ የተጨናገፈባቸው ሴቶች ሁሉ በለይቶ ማቆያው ውስጥ ይገኛሉ። ሌሎች በርካታ ህፃናት ልጆች የያዙም ሴቶች አሉ። ከሁሉም ግን የብዙዎችን ልብ የበላችው የወንዶች ዶርም የምትገኘው የአንድ ወር ከስድስት ወር የሆነችው ህፃን ናት። « የሚመጣውን ምግብ እንኳን ለሷ ለእኛም አይበላልንም። በጣም ተቸግራ ነው ያለችው። የሽንት ጨርቅ የላትም» የህፃኗ ወንድ አያቷ ስራ ከበዛባት ልጃቸው ተቀብለው ወደ ባለቤታቸው ጋር ሊወስዷት መኪና ውስጥ ሳሉ ነው በአጋጣሚ እሳቸውም እንደሌሎቹ ሰዎች ለይቶ ማቆያ ውስጥ የገቡት ይላሉ ታዛቢዎች። ሌላው ያነጋገርናቸው ደግሞ ለይቶ ማቆያ እስከመሆኑም የሚጠራጠሩት እኝህ አዛውንት ናቸው።« ምክንያቱም ባልታወቀ ሁኔታ ነው ታፍሰን የመጣነው። የኔ ናሙና የተወሰደው ለምሳሌ ግንቦት 24 ቀን ነው ግን እስካሁን ይኑርብኝም አይኑርብኝም አልተነገረኝም። ብዙ ሰው የጭንቀት በሽታ ይዟቸዋል።»
ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ በጉዞ ላይ ሲሄድ በዚሁ ለይቶ ማቆያ የገባውም ወጣት እንደሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ተሞክሮ ነው እያደረገ ያለው። « ጥቁር ውኃ የሚባል አካባቢ ነው መኪናችንን ያስቆሙት። ከዛ ሹፌሩን ወደ ዮንቨርስቲው ንዳ አሉት። » በርካታ ሰዎችም ከዚህ ማቆያ ለማምለጥ ሞክረዋል።« ወደ 40 የሚሆኑ ልጆች አምልጠው ወጥተዋል» ይላል ወጣቱ።
አቶ ቀድረላ አህመድ የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ዳሬክተር ናቸው። በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያለውን ይዞታ እና ወቀሳ በተመለከተ ያላቸው ምላሽ « አቅም የፈቀደልንን እያደረግን ነው» የሚል ብቻ ነው። በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲያድሩ የሚደረጉትም የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑትን ነው።
አቶ ቀድረላ በዚህ ማቆያ ውስጥ ያሉት ሰዎች በትህዋሲው የተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው እና የተጠረጠሩ ሰዎች ናቸው ይበሉ እንጂ ቃለ መጠይቅ የሰጡን የገለፁልን ምኑንም ሳያውቁ ከተሳፈሩበት አውቶቢስ በቀጥታ ወደዚህ ቦታ መወሰዳቸውን ነው። « ግንቦት 23 ቀን እሁድ ዕለት ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ሐዋሳ የሚገባ ሰው መንገድ ላይ እየተያዘ ነበር።» ከአዲስ አበባ የጠፉ ሰዎች ስላሉ ለማጣራት እና ለመለየት ስለምንፈልግ ነውም ተብለው ነበር። አቶ ቀድረላ ግን ያስተባብላሉ ። « ታፍሰው አይደለም እየተወሰዱ ያሉት። እዛ የሚገቡት ከቫይረሱ ጋር ከተያዙ ሰዎች ጋር ንኪኪ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው። ለእነሱ ጤንነት ተብሎ እንጂ ለቅጣት አይደለም መንግስት እዛ እያስገባ ያለው። አቶ ቀድረላ ናሙና ለተወሰደባቸው ሰዎች ውጤቱን ማሳወቅ እንደነበረበት ግን ይስማማሉ።
በለይቶ ማቆያው ያሉ ወንዶች እንደገለፁልኝ ሰሞኑን ከእነሱ ብሎክ ተህዋሲው ተገኝቶባቸዋል የተባሉ ሁለት ልጆች ወደ ሌላ ህክምና ጣቢያ ተወስደዋል። ከእነሱ ጋር አንድ ክፍል ይተኙ የነበሩትም ልጆች ተለይተዋል። ይሁንና ተህዋሲው የተገኘባቸው ልጆች በጊዜው ስላልተለዩ በሽታው በካምፓሱ ተዛምቶ ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ለይቶ ማቆያ ከገቡ ሁለተኛ ሳምንታቸውን እየጨረሱ ቢሆንም መቼ ከለይቶ ማቆያው እንደሚወጡም አያውቁም። ሰሞንኑን ግን መውጫችሁ ስለተቃረበ ክፍላችሁን እና ግቢውን አጽዱ ተብለው ሲያፀዱ እንደነበር ገልፀውልናል።
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ