1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደሞዝ ለጠየቁ መሥፈራሪያ እና እሥር ለምን?

ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2015

በሐድያ ዞን ባድዋቾ ወረዳ እና ሾኔ ከተማ እንደ ጤና ያሉ የመንግሥት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መቋረጣቸውን ተገልጋዮችና ሠራተኞች ተናገሩ። አገልግሎቶቹ የተቋረጡት የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ሳይከፈላቸው በመቅረቱ ነው። የአካባቢው ባለሥልጣናት ሥራ እንዲቆም አስተባብረዋል ያሏቸውን እንዳሰሩ ቅሬታ አቅራቢዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል

Äthiopien Hawassa, Sidama | SNNPR Finance Bureau
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ደሞዝ ለጠየቁ መሥፈራሪያ እና እሥር ለምን?

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን ምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና  በሾኔ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት አገልግት መስጫ ተቋማት ሙሉ በሙሉና በከፊል አገልግሎት ማቋረጣቸውን ተገልጋዮችና ሠራተኞች  ገለጹ፡፡
ተቋማቱ አገልግሎታቸውን ያቋረጡት የወረዳውና የከተማ አስተዳደሩ ለሠራተኞቻቸው ደሞዝ አለመክፈላቸውን  ተከትሎ ሠራተኞቹ  ሥራ መግባት በማቆማቸው ነው ተብሏል፡፡

በወረዳው እና በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የመንግስት የአገልግት መስጫ ተቋማት አብዛኞቹ ሙሉ በሙሉና ገሚሶቹ ደግም በከፊል አገልግሎት ማቋረጣቸውን ሥማቸው በሚስጥር እንዲያዝላቸው የጠየቁ ቅሬታ አቅራቢዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡

አሁን ላይ ሠራተኞቹ ወደ ተቋማቱ ገብተው እየሠሩ እንዳልሆነ  የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ “ በዚህም የተነሳ ከባለፈው የመጋቢት ወር መግቢያ አንስቶ  አሥፈላጊ የሚባሉ የወረዳው እና የከተማው መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፡፡ በተለይ ነዋሪው ጤናን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ማግኘት ባለመቻሉ ህክምና ፍለጋ ወደ አጎራባች የዎላይታ እና ሀላባ ዞኖች ለመጓዝ ተገዷል “ ብለዋል ፡፡

በወረዳውና በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ ከሁለት ሺ በላይ ሠራተኞች ላለፉት ሦስት ወራት የደሞዝ ክፍያ አለመፈጸሙ ለተቋማቱ መዘጋት ወይም መዳከም ምክንያት መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ  ሠራተኞች ከነቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ ከመውደቃቸውም በላይ የቀን ሥራ ፍለጋ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሄዱ ሠራተኞች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
የወረዳውና የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ በማስተወቂያ ጥሪ ቢያደርጉም ሠራተኞቹ ግን ደሞዝ ካልተከፈለን ወደ ሥራ አንመለስም በሚል ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አሰተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡

በሠራተኛው ውሳኔ የተበሳጩት የመስተዳድሮቹ አመራሮች ግን ሠራተኛው ሥራ እንዳይገባ አስታባብረዋል ባሏቸው ግለሰቦች ላይ ማስፈራሪያና እሥርና እየፈጸሙ እንደሚገኙ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ “ እስከአሁን 40 የሚሆኑ ሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ ታሥረው ይገኛሉ ፡፡ ሠራተኞቹ ከታሠሩ አንድ ወር  ከአስራ አምስት ቀን ቢያስቆጥሩም እከከአሁን ክስ እንኳን አልተመሠረተባቸውም “ ብለዋል፡፡

ዶቼ ቬለ በነዋሪዎቹና በመንግሥት ሠራተኞቹ ቅሬታ ዙሪያ የምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ ፣ የሃድያ ዞን መስተዳድር እና የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ቢሞክረም እንዳንዶች ስብሰባ ሌሎች ደግሞ በጉዞ ላይ ነኝ በሚል ምክንያት ምላሽ ለመስጠት ተባባሪ ሳይሆኑ ቀርተዋል ፡፡

በሃድያ ዞን የምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ እና  የሾኔ ከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ሠራተኞችን ደሞዝ በዋስትና በመስያዝ የወሰዱትን የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ባለመክፈላቸው የተነሳ ሠራተኞች በደሞዝ እጦት በችግር ላይ መውደቃቸውን ዶቼ ቬለ ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW