1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደቡብ ሱዳናዊዉ የሰብዓዊ ጉዳዮች ተሸላሚ

ሐሙስ፣ መስከረም 17 2011

የደቡብ ሱዳን የሕክምና ዶክተር ኤቫን አታር አደሃ ፤ ስደተኞችን በመርዳት ላሳዩት የላቀ አስተዋፅኦ የ2018 የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት « UNHCR» ን ናንስን ሽልማትን አገኙ። ከጎርጎረሳዊዉ 1954 ጀምሮ የሚበረከተዉ ናንሰን ሽልማት ፤ ለስደተኞች ከፍተኛ ግልጋሎትን ባበረከቱት የኖርዌ ዜጋ በፍሪድጆፍ ናንሰን የተሰየመ ነዉ።

Evan Atar Adaha
ምስል፦ Getty Images/AFP/H. McNeish

ዋናዉ ነገር ችግሮቻችንን ፈተን መፍትሄን ማስገኘት ይጠበቅብናል

This browser does not support the audio element.

የደቡብ ሱዳናዊዉ የዘንድሮ ተሸላሚ ዶክተር ኤቫን አታር አደሃ ለሽልማት የበቁት በተለይ የእርስ በርስ ጦርነት በበረታበት በደቡብ ሱዳን ለስደተኞች የማያቋርጥ ርዳታን በማበርከታቸዉ ነዉ።

የተመ የስደተኞች መርጃ ድርጅት « UNHCR» በያዝነዉ ወር ጄኔቫ ላይ የዘንድሮዉን ሽልማት ለደቡብ ሱዳናዊዉ የሕክምና ዶክተር ኤቫን አታር አደሃ የሕክምና ቁሳቁስ ከፍተኛ እጥረት ባለበት እና በእርስ በርስ ጦርነት በሚያናዉጣት ደቡብ ሱዳን ለ200 ሺህ ስደተኞች የማያቋርጥ ርዳታን በማበርከታቸዉ ነዉ። በሰሜናዊ ምስራቅ ደቡብ ሱዳን  ማባም አዉራጃ ፤ ቡንጂ መንደር በሚገኝ ሆስፒታል ለ 20 ዓመታት በማገልገል ላይ የሚገኙት ደቡብ ሱዳናዊዉ ዶክተር በአንድ ፈረቃ ለ 48 ሰዓታት ይሰራሉ ፤  በሳምንት  60 የቀዶ ጥገና ሕክምናም ያከናውናሉ።    

« ማባም አካባቢዉ ላይ መንደር ወይም ከተማ የሌለበት ወጣ ያለ ቦታ ነዉ። እዚህ ቦታ ላይ ወደ 200 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ይኖራሉ። በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነቱ እንደተቀሰቀሰ እዚህ አካባቢ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤ ሰዎች የሕክምና ቁሳቁስ ፤ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር። የስደተኛዉም ቁጥር ጨምሮ እጅግ አስቸጋሪ ነበር።»      

ምስል፦ UNHCR/Will Swanson

ደቡብ ሱዳናዊዉ የሕክምና ዶክተር ኢቫን አታር በአካባቢው ሁለት ሆስፒታሎችን አስገንብተዉ ለወጣቶች የሕክምና ሞያ እና የአዋላጅነት ሥልጠናም ሰጥተዋል።

በጎርጎረሳዊው 2011 ዓ,ም በደቡብ ሱዳን የርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሀገሪቱ 1.9 ሚሊዮን ሕዝብ ከመኖሪያ ቀየዉ ተፈናቅሏል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ሞተዋል።  በርግጥ ደቡብ ሱዳናዊዉ የሕክምና ዶክተር የዓለሙ መንግሥታት ደቡብ ሱዳንን ችላ ብለዋታል ብለዉ ያስቡ ይሆን?

«  አዎ ይህን ነዉ የማስበዉ። ምናልባት ሰዎች በደቡብ ሱዳንዋ ማባም ያለዉን እጅግ አስከፊ የሆነ ሁኔታ አላጤኑት ይሆናል። የሰዎችን ችግርና ስቅየት ቢያዉቁትና ቢያጤኑት ኖሮ በረዱን ነበር። ምናልባትም በሌሎችም ሃገራትና አካባቢዎች እንደዚሁ ጦርነትና ግጭት በመኖሩ ይሆናል።  »

የርስ በርስ ጦርነት በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰበት ወቅት ዶክተር ኤቫን አታር አደሃ አካባቢዉ ላይ ቆይተዉና የሕክምና አገልግሎት ለሕዝባቸዉ በመስጠታቸዉ ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል።  ዓለም የደቡብ ሱዳንን የርስ በርስ ጦርነት ለመግታት ጠንካራ ርምጃን ሳያደርግ ዶክተር ኤቫን አታር አደሃ ላበረከቱት ሰብዓዊ ግልጋሎት ይህን ከፍተኛ እዉቅና መስጠቱ ሚዛናዊ ያልሆነ የሰብዓዊ አያያዝ ነዉ በሚል የሚተቹ አልጠፉም። ደቡብ ሱዳናዊዉ የሕክምና ባለሞያ ግን እንዲህ ይላሉ። 

ምስል፦ UNHCR/Will Swanson

« ይህን እንኳ አላስብም ፤ ማንም ተጠያቂ ማድረግ አልፈልግም። እዚህ ላይ ዋናዉ ቁም ነገር ፤ ርዳታ በሚያስፈልግ ቦታ ላይ ተገኝተን መስጠት መቻላችን ብቻ ነዉ።  ይህን ነዉ አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ  ያለብን። ደሞም መርዳት እንችላለን» 

የጁባዉ መንግሥት የስደተኞቹን ችግር ተመልክቶ የሆነ አይነት ርዳታን ለማቅረብ ጥረት ያደርግ ይሆን? DW ለዶክተር ኤቫን አታር አደሃ ያቀረበዉ ጥያቄ ነበር ።

«እንደ ሕክምና ዶክተር፤ በእንዲህ ሁኔታ እና በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ላሉ ሰዎች ርዳታን መስጠት ለኔ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ቢሆን አስፈላጊ ነገር ይመስለኛል። ምክንያቱም ጦርነት ምን ያህል አፀያፊ  ነገር መሆኑን ሁላችንም እናዉቃለን።  ዋናዉ ነገር ችግሮቻችንን ፈተን ፤ ለሁኔታዎች ሁሉ መፍትሄን ማስገኘት ይጠበቅብናል። ይህ በማባም ብቻ ሳይሆን በደቡብ ሱዳንና በዓለም ዙርያ ሁሉ መሆን አለበት።» 

ይላሉ የዘንድሮዉ የተመ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ድርጅት የ« UNHCR» 2018  ናንስን ሽልማትን የተቀበሉት ደቡብ ሱዳናዊዉ ዶክተር ኤቫን አታር አደሃ ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ    

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW