ደቡብ ሱዳንና ሽምግልናው
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2006ተደራዳሪዎች በአሁኑ ጊዜ የወደፊቱን ድርድር አጀንዳ በመቅረጽ ላይ መሆናቸውን አደራዳሪዎች ገልጸዋል። ተቀናቃኞቹ ወገኖች እስካሁን የድርድሩ ቀዳሚ ዓላማ በሆኑት እና ሦስት ሳምንት ያስቆጠረውን ጦርነት ማስቆም እና የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዚደንት የሪክ ማቸር ደጋፊዎች ተወካዮች የደቡብ ሱዳን መንግሥት ያሰራባቸውን 11 አባላቱን ለማስፈታት ላቀረቡት ጥያቄ መፍትሔ ማስገኘት በሚያስችሉት ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ገና መደራደር አለመጀመራቸውን ባለሥልጣናቱ አክለው አስረድተዋል።
የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኤል በሺር በደቡብ ሱዳን ስለቀጠለው ደም አፋሳሹ ውዝግብ ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ሳልቫ ኪር ጋ ለመምከር ዛሬ ወደ መዲና ጁባ ተጓዙ። የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት የሪክ ማቸር ደጋፊዎች ካለፈው ታህሳስ ወዲh በርካታ ከተሞችን በቁጥጥራቸው ያስገቡ ሲሆን፣በተመድ ግምት መሠረት፣ በሪክ ማቸር ደጋፊዎች እና በፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር መንግሥት ጦር መካከል የቀጠለው ጦርነት በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብን አፈናቅሎዋል።
ከደቡብ ሱዳን ጋ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ንግድ ግንኙነት ያላት ቻይና በዚችው ሀገር የሚፋለሙት ተቀናቃኝ ወገኖች የኃይሉን ተግባር ባስቸኳይ እንዲያበቁ እና የተኩስ አቁም ደንብ እንዲደርሱ ጥሪ አሰምታለች።
በኢትዮጵያ ጉብኝት የጀመሩት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋንግ ዪ እንዳስታወቁት፣ ተፋላሚዎቹ ወገኖች በደቡብ ሱዳን ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ የቀጠለውን እና በይፋ ከ1,000 የሚበልጥ ሰው ሕይወት አጥፍቶዋል የሚባለውን ጦርነት የሚያበቁበትን መንገድ ለማስገኘት ቻይና ጥረት በማድረግ ላይ ናት። የደቡብ ሱዳን መንግሥት በጦርነቱ የተነሳ የነዳጅ ዘይቱን ምርት በአንድ አምስተኛ መቀነስ ተገዶዋል።
በእርስ በርስ ውጊያ ላይ የሚገኙትን የደቡብ ሱዳንን መንግሥትና በቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሪኤክ ማቻር የሚመሩትን ተቀናቃኝ ወገኖች ለመሸምገል አዲስ አበባ ውስጥ ሰሞኑን ጥረት ሲደረግ ነው የሰነበተው፤ ሁለቱን ወገኖች ፊት ለፊት አገናኝቶ እንዲደራደሩ ለማድረግ አድካሚ ሁኔታ ያጋጠመ ቢመስልም፤ ረዘም ያለ ጊዜ ይወስድ እንጂ ሽምግልናው መሥመሩ እንደማይቀር ብሩኅ ተስፋ አለ ተብሏል ።
ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ
ተክሌ የኋላ
አርያም ተክሌ