1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ በደቡብ ሱዳን መጽደቁ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 11 2016

ደቡብ ሱዳን የናይል/የዓባይ/ ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ (CFA) የተባለውን ስምምነት ሰሞኑን ማጽደቋ ኢትዮጵያን አስደስቷል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሱዳንን ውሳኔ «ይህ ዲፕሎማሲያዊ እመርታ በናይል ተፋሰስ ቀጣናዊ ትብብር ለማድረግ ባለን የጋራ ምኞት ጉልህ እርምጃ ነው» በማለት፣ እርምጃውንም «ታሪካዊ» ብለውታል።

ግንጽ፤ ዋራቅ ደሴት፤
የዓባይ ወንዝ የግብጽ ግዛትን ከሚያቋርጥባቸው አካባቢዎች አንዱ፤ ከዋና ከተማ ካይሮ በስተሰሜን ወጣ ብሎ የሚገኘው የዋራቅ ደሴት፤ ፎቶ ከማኅደር ምስል AFP

የደቡብ ሱዳን ውሳኔ ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ

This browser does not support the audio element.

የደቡብ ሱዳን እርምጃ ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

የናይል/የዓባይ/ ወንዝ 11 ተፋሰስ ሃገራት ቢኖሩትም አሁን ድረስ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመው ውል ወንዙን በበላይነት ለመጠቀም ግብጽ እና ሱዳን ጥያቄ ያነሳሉ።  

ይህንን ኢ- ፍትሐዊ ነው የሚባለውን የሃገራት የናይል/ዓባይ/ ውኃ አጠቃቀም ነባራዊ ሁኔታ ለመቀልበስ የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን የስምምነት ሀሳብ በሰባት የላይኛው ተፋሰስ ሃገራት መንጭቶ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ከ 14 ዓመታት በፊት እንዲሁም ቡሩንዲ አስከትላ ፈርመውታል። ኬንያ ስምምነቱን ብትፈርምም እስካሁን አላፀደቀችውም። በዚሁ ሳምንት መጀመርያ ደግሞ ጎረቤት ደቡብ ሱዳን ይህንን ስምምነት ያጸደቀች ስድስተኛ ሀገር ሆናለች።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ «ይህ ዲፕሎማሲያዊ እመርታ በናይል ተፋሰስ ቀጣናዊ ትብብር ለማድረግ ባለን የጋራ ምኞት ጉልህ እርምጃ ነው» በማለት የደቡብ ሱዳንን ውሳኔ «ታሪካዊ» ብለውታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖን ይህ የደቡብ ሱዳን እርምጃ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ ተጠይቀው፤ «በስምምነቱ ሰነድ መሠረት ስድስት አገሮች ካጸደቁት እና የመጨረሻው ስድስተኛው ሀገር ስምምነቱን ያጸደቀበትን ሰነድ ለአፍሪካ ሕብረት ገቢ ካደረገ፤ በ60 ቀን ውስጥ ሕብረቱ ለአባላቱ ያስታውቃል። .... የኢትዮጵያ ጥቅም ወደር የለሽ ነው ለማለት ይቻላል። የሃይድሮ ዲፕሎማሲ ድሏ እዚህ ላይ የተቋጨ፣ ለሚቀጥለው እርምጃ ደግሞ መሠረትና መንደርደሪያ ይሆናል» ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ፎቶ ከማኅደርምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

 

ከግብጽ እና ሱዳን በኩል ምን ምላሽ ሊኖር ይችላል?

በዋነነት የናይል/ዓባይ/ ወንዝ ውኃ ከፍተኛው ድርሻ የሚመነጭባት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎቹ የውኃ ምንጭ ሃገራት ይህ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ለዘመናት በግብጽ እና ሱዳን ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም ሙግት በማስወገድ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር ተገቢ ያሉት መርሕ እንዲያበጅ የሚያጠይቅ ነው። በግብጽ እና ሱዳን በኩል ግን አሁንም የዕድገት መሠረታችን ነው የሚሉት የወንዙ ውኃ ደኅንነታቸውን እና ታሪካዊ የሚሉትን ድርሻ የሚያረጋግጥ ሊሆን ይገባል በሚል ስምምነቱን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሱዳንን እርምጃ አድንቀው በኤክስ ከጻፉት መልእክት ሥር ይህ «በእርግጥም በናይል ቤተሰብ መካከል ትብብርን እና ክልላዊ ውሕደትን ያበረታታል» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። ይህ ስምምነት ተግባራዊ መሆን የሚችልበት ዕድል ከሰፋ በግብጽ እና ሱዳን በኩል ምን ሊከሰት ይችላል? የሚለው መሰረታዊ ገዳይ ነው። «እነሱ[ ግብጽ እና ሱዳን] በፊርማውም አልተሳተፉም፣ በዚህ የተነሳ ለማጽደቅም ፍላጎት አልነበራቸውም። እንዳይጸድቅም ብዙ ትግል ሲያደርጉ እና ሲቃወሙ ቆይተዋል። ስለዚህ መቃወማቸው የሚቀር አይመስለኝም።....ይህንን መቃወም ማለት ከእነዚህ አገሮች ጋር ሁሉ መጣላት ማለት ነው።» ነው ያሉት ይህ ስምምነት የቅኝ ግዛት የውኃ አጠቃቀም ውልን ያስቀር ይሆን?

የኢንቴቤ ስምምነት ተብሎ የሚታወቀው ይህ በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል ልዩነት የፈጠረው የውኃ አጠቃቀም የስምምነት ማእቀፍ «ለእያንዳንዱ የናይል ተፋሰስ ሀገር በግዛቱ ውስጥ የናይል ወንዝ ውኃን የመጠቀም መብት» የሚሰጥ ነው። ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እንዲኖርም ያግዛል። ይህ የደቡብ ሱዳን ስምምነቱን የማጽደቅ እርምጃ  ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንዲቋቋምም ያስችላል ነው የሚባለው። 

አብዛኞቹ የወንዙ ተፋሰስ ሃገራት ይህንን ስምምነት ተቀብለው ተግባራዊ ወደማድረጉ መግባት ቢችሉ የወንዙን አጠቃቀም በተመለከተ በቅኝ ግዛት ስምምነቶች ላይ ያለውን አታካች ክርክር ይፍቅ ይሆናልም ተብሎ ይታመናል። ይህ በቀላሉ ይሆናል ወይ ? የሚለው ግን ሌላ ብርቱ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚጠይቅ የቤት ሥራ ነው።

ግብጽ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ባልተቋረጠ ሁኔታ ወደኋላ ጎታች እርምጃዎችን የሚወስዱትም ለዚሁ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW