1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደቡብ አፍሪቃ የምታስተናግደው በአፍሪቃ የመጀመሪያው የቡድን ሀያ ጉባኤ

ዓርብ፣ ኅዳር 12 2018

የዋሽንግተንና የደቡብ አፍሪቃ ግንኙነት ተበላሽቷል። ዋሽንግተን ፕሪቶሪያ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ጥላባታለች። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያለአንዳች ተጨባጭ መረጃ በደቡብ አፍሪቃ በነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ይካሄዳል ብለው ደምድመዋል። የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በበኩሉ የትራምፕን ውንጀላ ሐሰት ሲል አስተባብሏል።

የዘንድሮውን የቡድን ሀያ ጉባኤ የምታስተናግደው የጆሀንስበርግ ከተማ
የዘንድሮውን የቡድን ሀያ ጉባኤ የምታስተናግደው የጆሀንስበርግ ከተማ ምስል፦ CELINE CLERY/AFP/Getty Images

ደቡብ አፍሪቃ የምታስተናግደው በአፍሪቃ የመጀመሪያው የቡድን ሀያ ጉባኤ

This browser does not support the audio element.

በአፍሪቃ ምድር ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው፤ በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 22 እና 23 ቀን፣ 2025 ዓም በደቡብ አፍሪቃ በጆሀንስበርግ ከተማ የሚካሄደው የቡድን ሀያ ጉባኤ። አሰተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ በዚህ ጉባኤ በአየር ንብረት ለውጥ ለተባባሰው የተፈጥሮ አደጋ ሊፈለግለት የሚገባውን መፍትሔ ጨምሮ ድሀ ሀገራት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጣቸው ትፈልጋለች። ባለፀጋ ሀገራት እና ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተጨማሪ ርዳታ እንዲሰጡ ጥሪም ታቀርባለች። አፍሪቃ ለዚህ ጉባኤ ትልቅ ቦታ ነው የምትሰጠው ። ዶቼቬለ ስለ ቡድን ሀያ ጉባኤ ያነጋገራቸው የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ሽግግር ማዕከል የተባለው ድርጅት ፕሬዝዳንት ፣ማቪስ ኦዉሱ ግያምፊ ጉባኤው የሚካሄደው አፍሪቃ ለዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች የመፍትሔ ማዕከል ናት በሚል ዓለም ዕውቅና በሰጠበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል። በእርሳቸው አስተያየት የዓለም እድገት እና መረጋጋት በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ጉዞ ላይ የተመሰረተ ነው። 

«ደቡብ አፍሪቃ የምታስተናግደው የቡድን 20 ጉባኤ የሚመራው በትብብር በእኩልነት እና በዘላቂነት መርኆች ነው። እነዚህ ደግሞ የአፍሪቃ ሕዝብ ይኹነኝ ብሎ የያዛቸው ሦስት ጉዳዮች ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ፦ ጉባኤው የሚካሄደው አፍሪቃ አሁን የገጠሙ ብዙ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ማዕከላዊ መሆኗን ዓለም መገንዘብ በጀመረበት ወቅት ይመስለኛል። በመጀመሪያ አፍሪቃ  በዓለም በፍጥነት ቁጥሩ እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለው ወጣት ሕዝብ መኖሪያ ናት። እንደምታውቁት፣ በእድሜ የገፉ ነዋሪዎች ቁጥር በፍጥነት  እየጨመረ በመሄድ ላይ ባለባት ዓለም አፍሪቃ በ2030 አንድ ሦስተኛውን የሠራተኛ ኃይል ትወክላለች። የአየር ንብረት ቀውስን እየተቋቋምን በዚያውም ለአረንጓዴ እድገት ከምንፈልጋቸው ወሳኝ ማዕድናት ውስጥ በርካታ ማዕድናት አሉን። ስለዚህ የዓለም እድገት እና መረጋጋት የሚወሰነው የአፍሪቃ አኅጉር አቅጣጫ ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑ ላይ ነው።»

ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ አፍሪቃ በሚካሄደው የቡድን ሀያ ጉባኤ ላይ ለምን አትካፈልም?

ዩናይትድ ስቴትስ በዙር የሚደርሰውየቡድን ሀያ ጉባኤፕሬዝዳንትነትን በጎርጎሮሳዊው ታኅሣስ አንድ ቀን፣ 2025 ዓ.ም. ትረከባለች ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በጆሀንስበርጉ የቡድን ሀያ ጉባኤ ላይ እንደማትሳተፍ ዐሳውቃለች። ከዚህ ሌላ የዋሽንግተንና የደቡብ አፍሪቃ ግንኙነት ተበላሽቷል። ባለፈው የካቲት  በዩ ኤስ ኤ አይ ዲ በኩል የሚደረጉ ርዳታዎች መቀነሳቸው አንዱ ነው። ይህም በሺዎች የሚቆጠሩ ተጋላጭ ደቡብ አፍሪቃውያንን ነክቷል። ከዚያም ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ አፍሪቃ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ጥላባታለች። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያለአንዳች ተጨባጭ መረጃ በደቡብ አፍሪቃ በነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን ላይ ያነጣጠረ «የዘር ማጥፋት» ይካሄዳል ብለው ደምድመዋል። የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በበኩሉ ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካነርስና ሌሎች ነጭ ደቡብ አፍሪቃውያንን በደቡብ አፍሪቃ  እየተሳደዱ ነው ማለታቸውን ሐሰት ሲል አስተባብሏል።

የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 21 ቀን 2025 ዓ.ም.በዋይት ሀውስ ደቡብ አፍሪቃን ነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን በመጨቆንና የዘር ማጥፋት ሰለባ በማድረግ ከሚከሱት ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ምስል፦ Jim Watson/AFP

 

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በወሰደችው ርምጃ ሰበብ ፣ደቡብ አፍሪቃ፣ በዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት በመሰረተችው ክስ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ አፍሪቃ ላይ ቅሬታ አሳድራለች። ሲግናል ሪስክ በተባለው የጥናት ተቋም ባልደረባ የፖለቲካ ስጋት ተንታኝ ሜንዚ ንድህሎቭ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት፣ ቡድን ሀያ ጉባኤ ላይ አለመሳተፍ ሌላ መልዕክት አለው። እንደ ቡድን 20 ባሉ መድረኮችም የደቡብ አፍሪቃን አመራር ሕጋዊ ለማድረግ ትሞክራለች። ይህ ስለ ደቡብ አፍሪቃ ሕጋዊነት እና የአመራር ደረጃዋ በዓለም አቀፍ የኃይል መዋቅሮች ውስጥ ባሉ ከፍተኛ ደረጃዎች ውስጥ ስላላት ድርሻ ነው።
«ደቡብ አፍሪቃ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን አቋም እና አለኝ የምትለውን የመሪነት ደረጃዋን ተቃውማለች ። ያም ብቻ አይደለም፦ ደቡብ አፍሪቃ እንደ ቡድን 20ባሉ ጉባኤዎች ላይ ያላትን ሚናም ማኮሰስ ትሻለች።  ይህ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥትን ሕጋዊ ሥልጣንን ፣የአመራር ደረጃውን እና በዓለም አቀፍ የሥልጣን መዋቅሮች ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ደረጃን አለማክበር ነው። አሜሪካን በተለይ ደግሞ ሪፐብሊካኖች ደቡብ አፍሪቃን በእንግሊዘኛ ምህጻሩ DEI ማለትም፦ በብዘኃነት ፣እኩልነት እና አካታችነት ሰበብ አድልዎ የሚፈጸምባት አገር አድርገው ነው የሚመለከቷት ። ሪፐብሊካኖች ይህን አይነቱ መርኅ በአሜሪካ ተግባራዊ መሆኑን ይቃወማሉ። ይህንንም በዓለም አቀፉ መድረክ እንደ ምሳሌ ለመጠቀም ደቡብ አፍሪቃን በዚህ መልኩ አቅርበዋል። በነገራችን ላይ እንደዚህ ዓይነት ፖሊሲዎች መኖራቸው የተለየ አይደለም።»

የቡድን ሀያ አባል ሀገራት በዓለም ካርታ ላይ ምስል፦ AP / CC_Marcin n_nc

በርካታ የቡድን ሀያ ተሳታፊዎች ይጠበቃሉ

ሆኖም ወደ 85 በመቶ የዓለም አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ፣ 60 በመቶው የዓለም ሕዝብ ፣ከ75 በመቶ በላይ የዓለም ንግድ የሚወከልበትን ድርጅት ማግለል አሁንም የሚተኮርበት ጉዳይ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ ባትገኝም የአውሮጳ ኅብረትንና የአፍሪቃ ኅብረትን ጨምሮ የዓለም 19 ግዙፍ ኤኮኖሚዎችን ባቀፈው የቡድን ሀያ ጉባኤ ላይ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ያም ሆኖ ንድሆሎቩ አሜሪካን በጉባኤው ላይ አለመገኟቷ ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ይናገራሉ። ይህ የሚሆነውም እርሳቸው እንደሚሉት፣ በኢኮኖሚው እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ባላት ተጽዕኖ ምክንያት ነው። ነገር ግን ደቡብ አፍሪካ ይህን ጉድለት ማሟላት የሚያስችላት መንገዶች አሏት ብለዋል።

«ለምሳሌ ትራምፕ በጉባኤው ላይ እንደማይገኙ ሲያሳውቁ ከደቡብ አፍሪቃ የተሰጠው ምላሽ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር ። በቁጣ ከመመለስ ይልቅ፣ በጣም ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መልስ ነበር መልስ የተሰጠው። በጉባኤው ለመሳተፍ ለሚመጡ ሁሉም በአጠቃላይ የመልካም አቀባበል መልዕክት ተላልፏል። ይህ የመጀመሪያው ርምጃ ነው። የሚቀጥለው ርምጃ የበለጠ አስፈላጊ ነው እላለሁ፣ ይህም አሜሪካ በሌለችበትና መግባባት ባለበት ቦታ ሊሠሩ የሚችሉ ውሳኔዎችን መፈለግ ነው። » 

ታዋቂዋ  የኤኮኖሚ ምሁር ኦዉሱ ጊያምፊ ደቡብ አፍሪቃ የቡድን ሀያ የፕሬዝዳንትነት ዘመንዋን በአሁኑ ጊዜ ለዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች መፍትኄ ያለቻቸውን ጉዳዮች አጉልታ ለማውጣት እንደተጠቀመችበት አስታውሰዋል። የእዳ ማሻሻያም ይሁን ፣የአየር ንብረት ለውጥ ድጎማ ፣ንግድ፣ በቡድን ሀያ የጋራ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው የምታቀርባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ቻይ ኖይ ኔቤ /ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW