ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ርዕሰ-መስተዳድሮች ተሾመላቸው
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13 201512ኛ የፌዴሬሽኑ አካል በመሆን በአዲስ የተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚል ራሱን ያደራጀው የቀድሞው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በየፊናቸው መሥራች ጉባዔዎቻቸውን አካሄድዋል፡፡ ትናንት ምሥረታቸውን በይፋ ያበሰሩት ክልሎች በዛሬው ውሏቸው የየምክር ቤቶቻቸውን አፈጉባኤዎችና ርዕሳነ መስተዳድሮችን ሲመርጡ ውለዋል፡፡
የሁለቱ ጉባዔዎች ሹመት
ጉባዔውን በወልቂጤ ከተማ ያካሄደው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀደም ሲል በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ በሃላፊነት ሲሰሩ የነበሩትን አቶ እንዳሻው ጣሰውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል ፡፡ አንዲሁም በአርባምንጭ ከተማ መሥራች ጉባዔውን ያደረገው “ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” በአንጻሩ የቀድሞው የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ ሹመት ሰጥቷል።
የደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በፌዴሬሽን ም/ቤት ጸደቀ
ሁለቱ ተሾሚዎች ህዝባቸውን በቅንንት ለማገልገል ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን በተለይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው መልካም አስተዳድርን ጨምሮ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን አጀንዳዎች በመለየት ምላሽ እንደሚሰጡ ለጉባዔተኛው ተናግረዋል ፡፡
አዳዲስ መዋቅሮች
የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ተጨማሪ በአዳዲስ የዞንና የልዩ ወረዳ ማዋቅሮችን እንዲደራጁ ውሳኔ አሳልፈዋል። ጉባዔዎቹ መዋቅሮች እንዲደራጁ ውሳኔ ያሳለፉት በአደረጃጀቱ ዙሪያ ለምክር ቤቶቹ የቀረቡ ሞሽኖችን በሙሉ ደምፅ በማጽደቅ ነው ።
በዚህም መሠረት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የም ዞን፣ ምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ ጠምባሮ ልዩ ወረዳ፣ ቀቤና ልዩ ወረዳ እና ማረቆ ልዩ ወረዳ ሆነው የአስተዳደር መዋቅራቸው እንዲሻሻል በሞሽኑ ቀርቦ ፀድቋል።
በተመሳሳይ የደቡብ ኢትዮጽያ ክልላዊ መንግስት የአማሮ፣የደራሼ፣ የባስኬቶ፣የቡርጂ፣የአሌ፣ልዩ ወረዳዎች እያንዳንዳቸው እራሳቸውን ችለው በዞን ይደራጃሉ።
ከደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ፣የሐመር፣የበና ጸማይ፣የሰላማጎ፣የኛንጋቶም የዳሰነች ወረዳ እና የቱርሚ ከተማ አስተዳደር በጋራ በዞን የሚደራጁ ይሆናል።
በሌላ በኩል ከደቡብ ኦሞ ዞን የደቡብ አሪ፣ የወባ አሪ የባካ ዳውላ፣የሰሜን አሪ ወረዳዎች እንዲሁም የጂንካ ከተማ አስተዳደር እና የገሊላ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች በጋራ ሆነው በሌላ ዞን ለማደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቋል።
ዳግም የተነሳው የክላስተር ድልደል ቅሬታ
በማዕካላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታ ላይ የአስፈጻሚ ቢሮዎች ድልድል በዚህኛው ጉባዔ ላይም አከራካሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ በተለይም በድልደሉ አንድ የግብርና ቢሮ ብቻ አግኝቷል የተባለው የከምባታ ጠምባሮ ዞን ተወካዮች በጉባዔው ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ከከምባታ ጠንባሮ ዞን መወከላቸውን የጠቀሱት ሁለት የምክር ቤት አባላት “ለየከተሞቹ የተሰጠው የአስፈጻሚ ቢሮዎች ድልድል መሥፈርት በቅድሚያ በዝርዝር ቀርቦ መተማማን መፍጠር ይገባ ነበር ፡፡ የተደለደለበት አግባባም ግልጽ አይደለም “ ብለዋል ፡፡
በአባላቱ ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ የሰጡት የቀድሞው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው “የተነሳው ቅሬታ ወደፊት ካለው አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ተጠንቶ ዳግም በምክር ቤቱ ሊታይ እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ ይገባል“ ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የልማት እንቅስቃሴውን ሲመሩ የነበሩ ተቋማት ማሻሻያዎች ተደርጎላቸውና ተስተካክለው እንዲቀጥሉ የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡
የክላስተር አዋጭነት እስከምን ድረስ?
አዲስ የተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዎላይታ ሶዶ ከተማን፤ ራሱን መልሶ ያደራጀው “ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል “ ደግሞ የሆሳዕና ከተማን በርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት መቀመጫነት እንዲያገለግሉ መርጠዋል ፡፡ የተቀሩት ቢሮዎችና ተቋማት ደግሞ በየዞንና ልዩ ወረዳ ከተሞች በክላስተር ተደልድለው አገልግሎት እንዲሰጡ ነው የተደረገው ፡፡ ቢሮዎቹ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሄዳቸው ቀደምሲል “ ልማት አላገኘንም ፣ ትኩረት አልተሰጠንም “ በሚል ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን ለመመለስ አንደሚያስችል በማሰብ የተደረገ መሆኑን ክልሎቹ ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ አባላት በተነሳው አከራካሪው የክላስተር ድልድል ዙሪያ ዶቼ ቬለ DW አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የፖለቲካ ተንታኝና የቀድሞው የተወካዮች ምክር አባል አቶ ዳያሞ ዳሌ የክላስተር አደረጃጀት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ይመልሳል የሚል እምነት አንደሌላቸው ይናገራሉ ፡፡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት ጉዳዮችን በአንድ መሰኮት መጨረስ አሥፈላጊ መሆኑን በምሳሌነት ያነሱት አቶ ዳያሞ “አንድ በእርሻ ዘርፍ ለመሠማራት የፈለገ ባለሀብት ግብርና ቢሮን ለማግኘት ዲላ ፣ ኢንቨስመንት ፍቃድ ለማውጣት አርባ ምንጭ ግብር ለመክፈል ደግሞ ሌላ ከተማ መሄድ ሊጠበቅበት ነው፡፡ ይህ አዋጭ አይደለም ፡፡ በእኔ እምነተ መልካ ምድራዊ አቀማመጡ አማካኝ የሆነ አንድ ከተማ በመምረጥ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በአንድ ቦታ የሚያገኝበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ይሆናል“ ብለዋል፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ