1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ኮሬ ዞን ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች ተገደሉ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ መስከረም 3 2017

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡ ታጣቂዎቹ አርሶአደሮቹን ለመለቀቅ፤ የጠየቁትን 100ሺ ብርና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራን ከተቀበሉ በኋላ ነው፡፡ የኮሬ ዞን መስተዳደር የድርጊቱ ፈጻሚዎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድኖች ናቸው ብሏል፡፡

Äthiopien Segen Zuria
ምስል privat

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ኮሬ ዞን ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች ተገደሉ

This browser does not support the audio element.

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤  ኮሬ ዞን ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች ተገደሉ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ገለጹ ፡፡ ታጣቂዎቹ ግድያውን ትናንት የፈጸሙት አርሶአደሮቹን ለመለቀቅ በመያዥነት የጠየቁትን አንድ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራ ከተቀበሉ በኋላ ነው ተብሏል ፡፡ የአርሶአደሮቹን መገደል ያረጋገጠው የኮሬ ዞን መስተዳደር በበኩሉ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድኖች ናቸው ሲል አስታውቋል ፡፡

በኮሬ ዞን ታግተዉ የነበሩ አራት አርሶአደሮች ተገደሉ 
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞንበታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት አርሶአደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ገለጹ ፡፡ ታጣቂዎቹ ግድያውን ትናንት ሐሙስ የፈጸሙት አርሶአደሮቹን ለመልቀቅ በመያዣነት የጠየቁትን አንድ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራ ከተቀበሉ በኋላ ነው ተብሏል፡፡


የታጋቾቹ ግድያ
አርሶአደሮቹ የታገቱት ትናንት ሐሙስ ማለዳ ከብት እያሠማሩ ባሉበት ወቅት መሆኑን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ሦስት የሟች የቅርብ ዘመዶች “ ታጣቂዎቹ ወደ ቀበሌው የገቡት ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በመነሳት ነው ፡፡ ታጋቾቹን ከያዙ በኋላ ካሊያ ተብሎ ወደ ሚጠራው ጫካ ውስጥ ነው ይዘው የሄዱት ፡፡ አንድ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራ ከተሰጣቸው እንደሚለቋቸው መልዕክት ልከውብን ነበር ፡፡ በተጠየቅነው መሠረት የተባልነውን ብንልክም ገንዘቡን እና ትምባሆውን ከተቀበሉ በኋላ ገድለዋቸው ሄደዋል ፡፡  ቀብራቸውም ዛሬ ዓርብ  እየተፈፀመ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡


ዶቼ ቬለ በአርሶአደሮቹ ግድያ ላይ የኮሬ ዞን አስተዳዳሪንም ሆነ የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የሥራ ሃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አመራሮቹ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ ያም ሆኖ የአርሶአደሮቹን መገደል በተረጋገጠ የፌስ ቡክ ገጹ የገለጸው የዞኑ መስተዳድር  የድርጊቱ ፈጻሚዎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድኖች ናቸው ሲል አስታውቋል ፡፡
መፍትሄው ምንድ ነው ?


ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በኮሬ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ ዶክተር አወቀ ሀምዛዬ እገታና ግድያውን የፈፀሙት አካላት በቁጥር 16 አካባቢ የሚሆኑ ታጣቂዎች መሆናቸውን ከነዋሪዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል ፡፡ በአካባቢው ግድያና ጥቃት በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም የጠቀሱት ዶክተር አወቀ “ መፍትሄው ሁለት ነው ፡፡ እሱም የፀጥታ ሀይሉ ጠንካራ ዘመቻ በማድረግ ታጣቂዎችን ማጽዳት ወይም ህዝብ ራሱን እንዲከላከል በህጋዊ መንገድ ማስታጠቅ ያስፈልጋል “ ብለዋል  ፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ርዕሰ መዲና አዲስአባባን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች በዜጎች ላይ የሚፈጸመው  እገታ እየተባባሰ  መምጣቱ ይታወቃል ፡፡ በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የታገቱ ቤተሰቦቻቸውን  ለማስለቀቅ በእምነት ተቋማት ደጆች ምፅዋት እስከመጠየቅ የተደረሰበት ሁኔታም ተስተውሏል ፡፡ በድርጊቱ የሚሳተፉ ሰዎችን በህግ ቁጥጥር ሥር እያዋለ  እንደሚገኝ የገለጸው መንግሥት ህብረተሰቡ ከጎኑ እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW