1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍትህ ተደራሽነት ጥያቄ በደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2016

የቀድሞው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ የሚታዩ ጉዳዮችን ለመመለከት ተዘዋዋሪ ምድብ ችሎት በሃድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ያስችል እንደነበር የሚያስታውሱት ጠበቃ አስፋው “ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚል በአዲስ ከተዋቀረ በኋላ ግን ሲሰጥ የነበረው የተዘዋዋሪና ምድብ ችሎት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡

አርባምንጭ ከተማ
አርባምንጭ ከተማ ምስል DW

በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የሚናገሩት አረጋ ሴባ በተዘዋዋሪና ምድብ ችሎት መቋረጥ ምክንያት ተመሳሳይ መጉላላት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ፡፡

This browser does not support the audio element.

በጥብቅና ሙያ የተሰማሩት በሃድያ ዞን የሆሳዕና ከተማ ነዋሪው አቶ አስፋው ማዴቦ ቀደም ባሉት ጊዜያት የደንበኞቻቸውን ጉዳይ ለመከታተል ብዙም ችግር እንዳልነበራቸው ይናገራሉ ፡፡ የቀድሞው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ የሚታዩ ጉዳዮችን ለመመለከት ተዘዋዋሪ ምድብ ችሎት በሃድያ ዞን  ሆሳዕና ከተማ ያስችል እንደነበር የሚያስታውሱት ጠበቃ አስፋው “ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚል በአዲስ ከተዋቀረ በኋላ ግን ሲሰጥ የነበረው የተዘዋዋሪና ምድብ ችሎት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ይህም በፍትህ አሠጣጥ ሥራው ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል ፡፡ አሁን ላይ ይግባኝ ባይ ባለጉዳዮችም ሆኑ ጠበቆች ለችሎት ተጨማሪ ወጪ በማውጣት  ወደ ሀላባ ከተማ ለመሄድ ተገደዋል “ ብለዋል ፡፡

የቀጠለው የሃድያ ዞን መምህራን አቤቱታ

ሌላው በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የሚናገሩት አረጋ ሴባ በተዘዋዋሪና ምድብ ችሎት መቋረጥ ምክንያት ተመሳሳይ መጉላላት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ ፡፡ በቀድሞው የደቡብ ክልል የፍትህ  ሥርዓቱም በተዘዋዋሪ ምድብ ችሎት ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ይሰጥ ነበር የሚሉት አቶ አረጋ “ አካባቢው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚል ከተዋቀረ ወዲህ አገልግሎቱ ተቋርጧል ፡፡ አንዳንድ ነዋሪዎችም የመጓጓዣ አቅም ስለሌላቸው ብቻ ፍትህ እንዳያገኙ ምክንያት እየሆነ ይገኛል“ ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ለምን ተቋረጠ ?

ዶቼ ቬለ ባለጉዳዮቹ ባነሱት ቅሬታ ዙሪያ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት  አቶ ቦጋለ ፈይሳ ለማነጋገር ቢሞክርም  ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ ቀጠሮዎችን ከሰጡ በኋላ ለስልክ ጥሪም ሆን ለአጭር የጽሁፍ መልዕክት ምለሽ ባለመሰጠታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ ግን  “ የተዘዋዋሪና ምድብ ችሎት አልግሎትን ማስቀጠል ያልተቻለው ነባሩ የደቡብ ክልል በተለያዩ አስተዳደራዊ ክልሎች መዋቀሩን ተከትሎ የዳኞች ቁጥር በማነሱና የበጀት እጥረት በማጋጠሙ ነው “ ብለዋል ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በኢትዮጵያ በተከታታይ በተካሔዱ ሕዝበ ውሳኔዎች ከተመሰረቱ ክልሎች አንዱ ነውምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሃድያ ዞን መምህራን እና ሐኪሞች የደሞዝ ጥያቄ ከምን ደረሰ?

በቀድሞው የደቡብ ክልል ሀዋሳ ላይ የነበሩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ለደቡብ ኢትዮጵያ እና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሁለት ቦታ መደልደላቸውን የጠቀሱት አቶ አቶ ኤርሲኖ “ በዚህ መሠረት የእኛ ክልል ስድስት ዳኞች ብቻ ነው የደረሰው ፡፡ በእዛ ላይ የበጀት እጥረቱ ተዳምሮ ሥራውን ፍትህ ፈላጊውን ህብረተሰብ በተዘዋዋሪና ምደብ ችሎት በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት ለመስጠት አላስቻለንም “ብለዋል።

አስተዳደራዊ ጥቄዎች እና የፍትህ ተደራሽነት

ዶቼ ቬለ በምድብና በተዘዋዋሪ ችሎት መቋረጥ ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ አቶ ብርሃኑ ገኔቦ አዳዲሶቹ ክልሎች አስተዳደራዊ ጥቄዎችን ለመመለስ በሚያደርጉት ሂደት የዜጎች ፍትህ የማግኘት ህገ መንግሥታዊ መብቶች እንዳይጓደሉ  በጥንቃቄ ሊሠሩ ይገባል ይላሉ ፡፡ የክልል መንግሥታቱ የአስተዳዳራዊ እና የፍትህ ተቋማት መቀመጫዎችንና የፍትህ ሥርዓት ተደራሽነትን አቀናጅተው ሊያከናውኑ እንደሚገባ ነው አቶ ብርሃኑ የተናገሩት ፡፡

አሁን ላይ በተወሰነ ደረጃ ተዘዋዋሪ ችሎት ለመጀመር እንቅስቃሴ ለማድረግ እየሞከሩ እንደሚገኙ የሚናገሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ “ በሂደት ግን ያለብንን የሰው ሀይል እና የበጀት እጥረት ለመቅረፍ ምድብና ተዘዋዋሪ ችሎቶች የሚሰጡባቸው ማዕከላትን በጥናት ለመለየት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ አቅደን እየሠራን እንገኛለን “ ብለዋል፡፡

 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW