1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደንበጫ በግጭቱ ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገድለዋል

ረቡዕ፣ ሰኔ 7 2015

ሰሞኑን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በሚገኙ ሦስት ከተሞች ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት በሕይወትና በአካል ጉዳት ካደረሰ በኋላ መብረዱን የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለስልጣናት ተናግረዋል ። በግጭቱ ቢያንስ 5 ሰዎች ሲገደሉ ሁለቱ ከመከላከያ ናቸው ተብሏል ። 30 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለስልጣናትና የሕክምና ተቋማት አመልክተዋል ።

Infografik Karte Äthiopien AM

«መከላከያዎቹ ለምን ወደ ከተማ ገቡ? ነው» ነዋሪዎች

This browser does not support the audio element.

ሰሞኑን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በሚገኙ ሦስት ከተሞች ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት በሕይወትና በአካል ጉዳት ካደረሰ በኋላ መብረዱን የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለስልጣናት ተናግረዋል ። በነበረው ግጨት ቢያንስ 5 ሰዎች ሲገደሉ ሁለቱ ከመከላከያ ናቸው ተብሏል ። 30 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለስልጣናትና የሕክምና ተቋማት አመልክተዋል ።

ባለፈው እሁድ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ከተማ መነሻው በውል ባልታወቀ ምክንያት በተፈጠረ ችግር የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና በርካቶች መቁሰላቸውን ባለስልጣናት፣ የህክምና ምንጮችና ነዋሪዎች አመልክተዋል ፡፡ አስተያየት ከሰጡን አንድ የደንበጫ ከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የከተማዋ ወጣቶች  የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ወደ ከተማዋ መምጣት በመቃወም ችግሩ እንደተፈጠረና ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ እንደሚያውቁ ገልፀዋል ፡፡

«መከላከያዎቹ ለምን (ወደ ከተማ) ገቡ? ነው፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፣ ምንም አልተፈጠረም ። መደበኛ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ነው የወጣቶች ጥያቄ ። በዚህ መካከል በተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ሁለቱም ርምጃ ወሰዱ ። ወጣቱም መከላከያም ። ተጀመረ (ተኩስ) ወጣቱ ሆ ብሎ ወጣ ። መንገዶችን ዘጋ ። በየአቅጣጫው የሚመጡ መኪናዎችን እንዳይተላለፉ መንገድ ዘጋ ። ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ወጣቶች እንዲፈቱ ጠየቁ ። እናስፈታለን ሲሉ ፖሊሶች ተመጣጣኝ ያልሆነ ርምጃ ወሰዱ ። ከሰላማዊ ሰዎች ሦስት ተገድለዋል ። 

ደንበጫ ከተማ ላይ የተከሰተው የፀጥታ ሁኔታ ወደ አጎራባች ጂጋና ፍኖተሰላም ከተሞች በመስፋፋት ጉዳቶች መድረሳቸውን የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪ ይናገራሉ ፡፡ አስተያየት ሰጪው የግጭቱና የአለመግባባቱ መነሻ ከሰሞኑ የምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ግጭት ጋር ያያይዙታል፣ «ጥያቄያቸው ሁለት ነው ። አንደኛው እስክንድር ነጋ በዚህ አካባቢ አለ የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ፋኖን ትደግፋላችሁ የሚል ነው ። እሁድ ደንበጫ ላይ እንደዚያ ያለ ችግር ነበረ ።  ሰኞ 4 ሰዓት አካባቢ (አለመረጋጋቱ) ወደ ጂጋ እየተስፋፋ መጣ ። አለመረጋጋቱ ፍኖተ ሰላም ላይ 4 ሰዓት ተጀመረ ። መንገድ ተዘጋ ። ማኅበረሰቡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ አስፋልት ላይ ቅሬታውን እየገለፀ ነበረ ። በዚህ ሰዓት አንድ ፖሊስ ተነስቶ ተኩስ ከፈተ ። ከ10 በላይ የቆሰሉ አሉ፤ በዓይኔ ያየኋቸው ። አንድ ሰው ተገድሏል ። አንደኛው ወደ ባሕር ዳር ለከፍተኛ ህክምና ተልኳል ።»

አንድ የደንበጫ ሆሰፒታል ባለሞያ 18 የቆሰሉና 2 የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመው 4 ሰዎች አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተው ለከፍተኛ ህክምና መላካቸውን ነግረውናል ።
የደንበጫ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ላቀ ወንድይፍራው በደምበጫ በነበረው ግጭት የቆሰሉትን ቁጥር ማወቅ ባይቻልም እስካሁን ባላቸው መረጃ 5 ሰዎች ከሁለቱም ወገን መገደላቸውን አረጋግጠዋል ፡፡ 

የምዕረብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳች መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመኑ ታደለ ዝርዝር ጉዳዮች ገና በምርመራ ላይ ቢሆኑም ግጭት ተነስቶባቸው በነበሩ የዞኑ ከተሞች የሞቱት ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ ከ3 እንደማይበልጥ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል ፡፡ የነበረው አለመግባባትና ግጭት ከአካባበው ነዋሪዎችና ከወጣቶች ጋር በተደረገ ውይይትና ምክክር የከተሞቹ መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ተደርጓል ብሏል፡፡

እሁድና ሰኞ እለት ሥራ አቋርጠው የነበሩ አገልግሎት መስጫ ተቀቋማት አገልግሎት መጀመራቸውን፣ ተዘግተው የነበሩና ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወስዱና የሚመልሱ መንገዶች ከትናንትና ጠዋት ጀምሮ ለትራፊክ ክፍት መሆናቸውን የየከተሞቹ ነዋሪዎችና ባለስልጣናት አመልክተዋል ፡፡ በቅርቡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ ሥላሴ አንድነት ገዳም በነበረ ተመሳሳይ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉና ብዙዎች መቁሰላቸው አይዘነጋም ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW