1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዲንካ ባሕላዊ የዳዋሮዎች የሙዚቃ መሳሪያ

ሐሙስ፣ መጋቢት 14 2015

ዲንካ ሙሉ በሙሉ ከቀርከሃ የሚሰራ ሲሆን ድምጽ በሚወጣበት ጫፉ የሚዳቋ ቀንድ ይገጠምለታል። ዲንካ በብሔረሰቡ የተለያዩ የደስታ በአላት ዋና ማድመቂያ እንደሆነ ባለሙያው ነግረውናል።

Äthiopien kulturelles Musikinstrument in der "Dawaro"-Zonenverwaltung
ምስል፦ Edgetu Beyabih/Privat

የዳዋሮዎች ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ዲንካ

This browser does not support the audio element.

የዳውሮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኝ ሲሆን በሰሜን ከጅማ፣ በደቡብ ከጎፋ ዞን፣ በምስራቅ ከወላይታ፣ በምዕራብ ከኮንታ ትዋሰናለች። ዳውሮ የጥንት ስልጣኔ ማሳያ ከሆኑት አንዱ የሆነው የንጉስ ሃላላ የድንጋይ ካብ ቅርስ፤ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የዝሆን መገኛ የሆነውን የጨበራ ጩርጭራ ብሔራዊ ፓርክና ሌሎች የተፈጥሮ መስህቦች መገኛ ናት። ትሁትና እንግዳ ተቀባይ ሕዝቧ ካላቸው ተዝቆ የማያውቅ ባህላዊ እሴቶች መካከል  ባህላዊ የትንፈሽ መሳሪያ የሆነውን ዲንካ ላይ መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን።

አቶ እድገቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ባልደረባ ናቸው። እሳቸው ስለዳውሮ ብሔረሰብ ባሕል፣ መልከ አምድራዊ ውበትና በተለይም ዲንካ እየተባለ ስለሚጠራው ቁመተ ረዥሙ ባሕላዊ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ ብዙ ጽሑፎችና የቪድዮ ዘገባዎችን በማቅረብም ይታወቃሉ። ከሳቸው ጋር አጭር ቆይታ እናደርጋለን አብራችሁን ቆዩ።

ምስል፦ Edgetu Beyabih/Privat

ዲንካ ከትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎች የሚመደብ ሲሆን ርዝመቱ እንደተፈለገው ድምጽ ይለያያል። ረዥሙ እስከ 5 ሜትር እንደሚደርስ አቶ እድገቱ ነግረውናል። ዲንካ የወል መጠሪያ ሲሆን በሚያወጡት ድምጽና ቁመት መሰረት የተያዩ የትንፋሽ መሳሪያዎች እንደሚዘወተሩ አቶ እድገቱ ይገልጻሉ። `` ዲንካ የወል ስም ነው። እንደ የባንዱ ስም በለው። በዚህ ውስጥ የሚነፋው ረዥሙ ዲንኬ የሚባል አለ። የሚመታው በሮ ደግሞ ደርቢ ይባላል። የትንፋሽ መሳሪያው ራሱ አራት አይነት ነው። ቆመቱ ከ1 ሜትር ጀምሮ እንደሚያወጣው ድምጽእስከ 3 ሜትር የሚረዝም ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ነው።``

ዲንካ ሙሉ በሙሉ ከቀርከሃ የሚሰራ ሲሆን ድምጽ በሚወጣበት ጫፉ የሚዳቋ ቀንድ ይገጠምለታል። ዲንካ በብሔረሰቡ የተለያዩ የደስታ በአላት ዋና ማድመቂያ እንደሆነ ባለሙያው ነግረውናል። በዳዋሮ ትልቁ በዓል የዘመን መለወጫ ሲሆን በዚህ በዓል ዲንካ በዓሉን በማድመቅ የአንበሳ ድርሻውን ይወስዳል። `` የዳዋሮ ትልቁ በዓል የዘመን መለወጫ ነው። ይህም በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ላይ ነው። በዚህ ጊዜ ሁሉም ህጻን ሽማግሌው በደንብ እደጠግብ ሆኖ ነው የሚመገበው። ይህም ጠግቦ አዲስ ዘመን ካልተሻገረ አዲሱ ዓመት ረሃብ ይሆናል ተብሎ ነው የሚገመተው። ስለሆነም ማሰሮ እንኳን ባዶ አይሆንም በውሃ እንዲሞላ ይደረጋል። በዚህ ለዘመን መለወጫ በዓል በማድመቅ ዲንካ ከፍተኛ ሚና አለው።``

ዲንካ ደስታን ብቻ ሳይሆን የሃዘን ማጀቢያም እንደሚሆን አቶ እድገቱ አጫውተውናል። አሁን አሁን እየቀነሰ ቢሆንም በተለይ በብሔረሰቡ ታላቅ ከበሬታ ያላቸው ሰዎች ሲሞቱ ዲንካ የቀብር ስነስርዓት  ማጀቢያ ሆኖ ያገለግላል።

ምስል፦ Edgetu Beyabih/Privat

ዲንካ እንደየ አካባቢው እንደየሁኔታው ከ3 እስከ እስከ 5 ሜትር የሚረዝም ልዩ ባሕላዊ የትንፋሽ መሳሪያ ቢሆንም ይህ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ የሚደረጉ ጥረቶጥ ግን እምብዛም እንደሆኑ አቶ እድገቱ በዛብህ ነግረውናል። በቁመተ ረዥሙ የዳዋሮ ብሄረሰብ ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ላይ ያዘጋጀነው በዚሁ ፈጸምን።

 ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር 

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW