ዲፕሎማቶችና የዉጭ ሃገር ዜጎች ሱዳንን እየለቀቁ መሆኑ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2015
አስረኛ ቀኑን የየያዘው በሱዳን ጦር ሰራዊትና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የሚካሄደው ጦርነት፤ ሱዳንን ወደለየለት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ከቷታል። በሁለቱ ኃይሎች መክከል ሲደረጉ ከቆዩት የሰባዊ የተኩስ ማቆም ስምምነቶች አንዱም የተክበረ ባለመሆኑ በተለይ ካለፈው ዓርብ ወዲህ የምዕራባውያን፣አረብ መንግስታትና ለሎችም አገሮች ዜጎቻቸውን ከሱዳን ባስቸኳይ ለማስወጣት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሜሪካ፤ ጀርመን፤ ፈርንሳይ፤ እስፔንና ሌሎችም መንግስታት በየግላቸውና በጋራ ባደርጓቸው ስምሪቶች በርካታ ዜጎቻቸውን በተለይም ዲፕሎማቶቻቸውን ከካርቱም ለማስወጣት ችለዋል።
የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀልፊ ሚስተር ጆሴፍ ቦርየል ዛሬ እረፋድ ላይ በሉክዘምበርግ በሰጡት አስተያየት 21 የህብረቱን ድፕሎማቶችንና ሰራተኖችን ጨምሮ በርክታ የህብረቱ ዜጎች ከሱዳን ሊወጡ መቻላቸውን አረጋግጠዋል። “ የሳምንቱ መጨረሻ ዜጎቻችንን ከሱዳን ለማስወጣት ጥረት ስናደርግ የቆየንባቸው ረጅም ቀናት ነበሩ። 21 የህብረቱ ሰራተኖች አውርፓ ደርሰዋል፤ ከአንድ ሺ በላይ የህብረቱን ዜጎች ደግሞ ከሱዳን ማስወጣት ተችሏል በማለት ዜጎችን ለማስወጣት በተደረገው ጥረት የተካፈሉትን ሁሉና በተለይም የፈረንሳይን መንግስት አምስግንዋል። ሚስተር ቦይርየል የህብረቱ አምባሳደር ግን በዚያው በሱዳን ከካርቱም ውጭ ሁኔትዎችን እየተከታተሉ እንደሚቆዩም አስታውቀዋል።
አሜሪካም ኤም ኤች-47 የተሰኙ ሂሊኮብተቿን ወደ ሱዳን አስገብታ አንድ መቶ የሚሆኑ ዲፕሎማቶቿንና ቤተስቦቻቸውን ከካርቱም ማስወጥቷ ተገልጿል። ጀርመንና ፈረንሳይም በርካታ የየራሳቸውንና የሌሎች አገሮችን ዲፕሎማቶች በተደጋጋሚ በረራዎች ማሰወጣታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የብርታኒያ የመከላከያ ሚኒስተር ቤን ዋላስ በበኩላቸው፤ “ ባለፈው ምሺት የብርታኒያ ሰራዊት ወደ ካርቱም ስምሪት በማድረግ ዲፕሎማቶቹን በተሳከ ሁኔታ ከካርቱም አስወጥቷል በማለት ስምሪቱም የአየርና ባህር ሀይሎችን ያሳተፈ እንድነበር አስታውቀዋል።
ሳኡዲ አረቢያም በፖርት ሱዳን በኩል በመርከብ የበርካታ አገሮች ዲፖሎማቶንችና ዜጎችን ማስወጣቷ ታውቋል። ግብጽ በበኩሏ ከአስር ሺበላይ ዚጎቿ በሱዳን እንደሚኖሩ ገልጻ የቻሉት ፖርት ሱዳን ወደ ሚገኘው የግብጽ ቆንስላ እንዲሄዱ አሳስባለች። ሌሎች አገሮች፤ ቻይናና ሩሲያን ጨምሮ ሁሉም፤ ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማሰውጣት የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሆነም ታውቃኡል።
ይህች ዛሬ ሁሉም ሊለቃት የሚጣደፍባት አገር ሱዳን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከጎረቤት አገሮች የመጡ ስደተኖች የሚኖሩባት ወይም ወደ ሊላ ሶስተኛ አገር የሚተላለፉባት እንደሆነች የሚታወቅ ሲሆን፤ ዛሬ፤ ሁሉም አገሮች ዋና ትኩረታቸውና ጥድፊያቸው ዜጎቻቸውን እንደምንም ብለው ከሱዳን ማውጣት እንጂ ለሱዳን ችግር አለመሆኑ አስዛኝ መሆኑን ብዙዎች ይጠቅሳሉ።
ሱዳን ወደዚህ ችግር ወስጥ የገባችው በዋናነነት በአገሪቱ ውስጥ ሁለት ተገዳዳሪና የኢኮኖሚ አቅም ጭምር ያላቸው የሰራዊት ክፍሎች በመኖራችውና አዛዦቻቸውም የፖለትካ ስልጣን ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ነው የሚሉት ታዛቢዎች፤ ሁለቱም የጦር አዛዦች የሚደግፏቸው የውጭ ሀይሎች ያሏቸው መሆኑ ደግሞ፤ የሱዳንን ፖለቲካ የበለጠ ውስብስብ እንደሚያደርገውና ጦርነቱንና ፖቲካዊ ቀውሱንም ሊያራዝመው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።
ገበያው ንጉሴ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ