1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዳግም መፈናቀል ያሰጋቸው የአዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ ወረዳዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ተፈናቃዮች

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ጥር 21 2017

«ከአፋር ዞን 03 አዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ ወረዳ የተፈናቀሉ ዜጎች ከመንግስት እርዳታ እየቀረበላቸው ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ እርዳታን ይሻሉ፡፡ አሁን አሚባራ ወረዳ አዋሽ አርባ አከባቢ ፣መገንጠያ በሚባል ስፍራ የተሰባሰቡትና ከአዋሽ ፈንታሌ 5 ወረዳ እና ከዱለቻ ወረዳ 3 ቀበሌ የተፈናቀሉት ቁጥር 13 ሺህ ግድም ይሆናል» ተፈናቃዮች

Earthquake in Ethiopia, Afar region _ 01.01.2025
ምስል፦ private

ዳግም መፈናቀል ያሰጋቸው የአዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ ወረዳዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ተፈናቃዮች

This browser does not support the audio element.

ሀሰን ካሚል በአፋር ዞን 03 የዱለቻ ወረዳ ሳገንቶ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በቅርቡ አፋር ክልል ዞን ሶስት ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወረዳዎችን ባሰጋው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት  ወደ አሚባራ ወረዳ ሸሽተው ከተጠለሉ ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ለወራት  ያለማቋረጥ እየከፋ የመጣውን መሬት መንቀጥቀጥ ሸሽተው የተፈናቀሉት አስተያየት ሰጪው አሁንም ድረስ ስጋቱ እንዳላቆመ አስረድተዋል፡፡ “ስጋቱ በማየሉ፣ ሰው እንዳለ አከባቢውን ለቆ ወጥተዋል” ያሉን አስተያየት ሰጪው፤ የመሬት መሰነጣጠቆች በመክፋታቸው ስጋቱ መጠናከሩንም አስረድተዋል፡፡
ሌላም ስመኝ የተባሉ የዱለቻ ወረዳ ቀበና ቀበሌ ተፈናቃይ መዞሪያ በሚባል አከባቢ በተፈናቃዮች ጣቢያ ውስጥ መሆናቸውን አስረድተው አሁንም ያሰጋው የመሬት መንቀጥቀጥ በመቀጠሉ ለዳግም መፈናቀል እየተሰናዱ መሆኑን አስረድተውናል፡፡ “መጠለያ ካምፕ ገብተናል” ያሉን አስተያየት ሰጪዋ አሁን መገንጤ የሚባል የሰፈራ ጣቢያ ውስጥ ቢሆኑም አሁንም በቀጠለው የመሬት ርዕደት ስጋት ለዳግም መፈናቀል እየተሰናዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 የመሬት መንቀጥቀጡ እና ሊወሰድ ይገባል የተባለው ቀጣይ ጥንቃቄ


 “ትናንትም ነበር አደገኛ ርዕደትና ስጋቱ አልቀነሰም” ያሉን ሙሴ የተባሉ ሌላውም ተፈናቃይ « አሁን አዋሽ አርባ አከባቢ በሚገኝ መጠለያ» መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ከአፋር ዞን 03 አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳ የተፈናቀሉ ዜጎች ከመንግስት እርዳታ እየቀረበላቸው ቢሆንም እየቀረበላቸው በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ እርዳታን ይሻሉ፡፡ “አሁን ተፈናቃዮች አሚባራ ወረዳ አዋሽ አርባ አከባቢ መገንጠያ በሚባል ስፍራ የተሰባሰቡት ከአዋሽ ፈንታሌ 5 ወረዳ እና ከዱለቻ ወረዳ 3 ቀበሌ የተፈናቀሉ” ናቸው ያሉን አስተያየት ሰጪዎቹ “የተፈናቃዮች ቁጥር 13 ሺህ ግድም ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋልም፡፡ አስተያየት ሰጪ ተፈናቃዮቹ እስካሁን መንግስት ለተፈናቃዮቹ የእለት ምግብ እና የተለያዩ የፍጆታ እቃዎችን ቢያቀርብም እርዳታዎቹ በቂ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ምልክት በአፋር ክልል

በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ ሰዎች እቃዎች ሲያጓጉዙ ምስል፦ private


ዶይቼ ቬለ የተፈናቃዮቹ እርዳታ አቅርቦት ሁኔታ እና ቀጣይ ስጋቶቹን በተመለከተ ከአከባቢው ባለስልጣናት እና ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስብሰባ ላይ ነን በሚል አስተያየት እና ማብራሪያ ባለመስጠታቸው  አልተሳካም፡፡ የአፋር ክልልን ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጋር የሚያዋስነውን አካባቢ የመታው ተደጋጋሚ ርዕደ መሬትና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ስጋት አሁንም እንደቀጠለ ነዉ። ካለፈዉ መስከረም አጋማሽ ጀምሮ በተለይ የአዋሽ-ፈንታሌንና የዱለቻ ወረዳዎችን በተደጋጋሚ የሚመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ የመኖሪያ ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የመስሪያ ቤቶችን ሕንፃዎች እና ፋብሪካን አፈራርሷል። በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸዉ አፈናቅሏል።በኢትዮጵያ የተደጋገመው ርዕደ መሬት እና ስጋቱ

የመሬት መንቀጥቀጡ ዶፈን በተባለዉ አካባቢ የእሳተ ጎሞራ ትፍ የሚመስል አዋራ፣ ጢስና ፍል ዉኃ ሲያፈልቅ፣ የፈንታሌ ተራራ ደግሞ ጢስ አዉጥቶ በከፊል መደርመሱን የአከባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ካለፈዉ መስከረም ጀምሮ ተደጋግሞ በደረሰው ቀላልና ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ እስካሁን ድረስ በሰዉ ሕይወትና አካል ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ባይኖርም በተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥና ንዝረት በአካባቢው የሚኖረዉ ሕዝብ በሥጋትና ጭንቀት መዋጡ ተነግሯል፡፡

ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW