1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሶማሊያ

ዳግም ዕውቅና ፍለጋ፦ የሶማሌላንድ መንገድ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016

ሶማሌላንድ ከ64 ዓመታት በፊት ከቅኝ ገዢዎች ነጻ ስትወጣ ያገኘችውን ዕውቅና ዳግም እጇ ለማስገባት ጥረት ላይ ነች። ይኸ ጥረት ከሶማሊያ ብርቱ ተቃውሞ ቢገጥመውም የሶማሌላንድ ልሒቃን በቅርቡ ይሳካል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። ኢትዮጵያ ዕውቅና ብትሰጥ ሶማሌላንድ የአፍሪካ ኅብረት 55ኛ አባል ሀገር እንደምትሆን ልሒቃኑ ያምናሉ።

ሶማሌላንድ ዕውቅና እንድታገኝ ግፊት ከሚያደርጉ ልሒቃን አንዱ ዶክተር ጃማ ሙሴ ጃማ
ዶክተር ጃማ ሙሴ ጃማን የመሰሉ ልሒቃን ለዓመታት ሶማሌላንድ ዕውቅና እንድታገኝ ያደረጉት ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት ሊሳካ እንደተቃረበ ያምናሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

ዳግም ዕውቅና ፍለጋ፦ የሶማሌላንድ መንገድ

This browser does not support the audio element.

ዶክተር ጃማ ሙሴ ጃማ የሒሳብ ሊቅ ናቸው። ከሶማሌ ተረቶች ሥሌት የሚቀምሩት ጃማ በአፍሪካ ጥናት የፒኤችዲ ባለቤት ናቸው። በሶማሌ ማኅበረሰባዊ ጨዋታዎች ላይ የሚያተኩሩትን ጨምሮ የተለያዩ መጻሕፍት ደርሰዋል።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሀገራቸው ውጪ ቢኖሩም “ዲያስፖራ” መባልን ፈጽሞ አይሹም። የሐርጌይሳ ባሕል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ጃማ ሶማሌላንድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንድታገኝ ግፊት ከሚያደርጉ ልሒቃን አንዱ ናቸው። 

“ቅኝ ገዢዎች ወደ አፍሪካ ቀንድ በአጠቃላይም ወደ አፍሪካ ከመምጣታቸው በፊት የሶማሌ ሕዝቦች የአስተዳደር አንድነት አልነበራቸውም” የሚሉት ዶክተር ጃማ “እንደ ሶማሊኛ ተናጋሪ ወይም እንደ ሶማሌ ብሔር የሚኖሩበት መሬት ሁሉ ባለቤት እንደሆኑ የሚያምኑ ናቸው” ሲሉ ይናገራሉ።

ሶማሌዎች የሚኖሩበት ምድር ከአምስት መከፋፈል የጀመረው “ቅኝ ገዢዎች በ1884 መጥተው አፍሪካን ሲቀራመቱ ነበር።” “የፈረንሳይ ሶማሌላንድ” ትባል የነበረችው ጅቡቲ፣ ሶማሌዎች የሚኖሩባቸው እና ወደ ኢትዮጵያ እና ኬንያ የተካለሉት አካባቢዎች፣ “የጣልያን ሶማሌላንድ” እና “የብሪታኒያ ሶማሌላንድ” የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ቅርምት የፈጠራቸው ናቸው።

ሶማሌዎች ከቅኝ ግዢዎቻቸው ነጻ ሲወጡ የዛሬዋ ሶማሌላንድ ቀዳሚ ነበረች። “ነጻ የወጣንው ሰኔ 26 ቀን 1960 ነው። ከሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች ነጻ በመውጣት 12ኛ ነን” የሚሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ባልደረባ መሐመድ ዋርሳሜ ዱዓሌ “ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ እና ከሌሎች አብዛኞቹ ሀገሮች ቀድመን ነው ነጻ የወጣንው” ሲሉ በኩራት ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ባልደረባ መሐመድ ዋርሳሜ ዱዓሌ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዕውቅና ከሰጠች የአፍሪካ ኅብረት 55ኛ አባል እንደምትሆን እርግጠኛ ናቸው። ምስል Eshete Bekele/DW

በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 1 ቀን 1960 “የጣልያን ሶማሌላንድ” ከቅኝ ተገዢነት ነጻ ወጣች። “ብሪቲሽ ሶማሌላንድ” እና “የጣልያን ሶማሌላንድ” በጎርጎሮሳዊው 1960 ተዋሕደው ሶማሊያ ሪፐብሊክን አዋለዱ። አደን አዴ በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት አደን አብዱሌ ኦስማን ዳር የመጀመሪያው የሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ሆነው መንግሥት ተመሠረተ።

የሁለቱ ውኅደት በቅኝ ግዛት ሳቢያ አምስት ቦታ የተከፋፈሉትን የሶማሊያ ግዛቶች በማሰባሰብ “ታላቋ ሶማሊያ” እንድትመሠረት ጭምር የተወጠነበት ነበር። “የሶማሊያ እና ሶማሌላንድ ፕሮጀክት አልነበረም። የሶማሌ ሕዝቦችን መሬት ለመመለስ የተጀመረ ፕሮጀክት ነው” የሚሉት ዶክተር ጃማ ጅቡቲ እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ እና ኬንያ የተጠቃለሉ ሶማሌዎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ገልጸዋል።

“የሶማሌላንድ ፍላጎት ሁሉንም የሶማሌ ሕዝቦች ለማሰባሰብ ነበር። ይኸ ግን በአጭር ጊዜ ብን ብሎ የጠፋ ስሜት ነው” የሚሉት ዶክተር ጃማ የዘመኑ የሶማሌላንድ ልሒቃን “ያ ዕቅድ የሚሠራ እንዳልሆነ በራሳቸው” ሲገነዘቡ ዓመት እንኳ ሳይሞላ በ1961 መውጣት መፈለጋቸውን አስረድተዋል።   

“የፈረንሳይ ሶማሌላንድ” ትባል የነበረችው እና ከባብ ኤል መንደብ ሠርጥ የምትገኘው የዛሬዋ ጅቡቲ ከአውሮፓ ቅኝ ገዢዋ ለመላቀቅ እስከ ሰኔ 27 ቀን 1977 መጠበቅ ነበረባት። ነገር ግን የሶማሊያ ሪፐብሊክን ለመቀላቀል ፈቃደኛ አልሆነችም።

የሶማሊያ ሪፐብሊክ ሁለተኛ ፕሬዝደንት አብዲራሺድ አሊ ሸርማርኬ ተገድለው ጄኔራል ዚያድ ባሬ በመፈንቅለ-መንግሥት በ1969 ሥልጣን ጨበጡ። ዚያድ ባሬን የሚቃወም የሶማሊ ብሔራዊ ንቅናቄ የተባለ አማጺ በሶማሊላንድ ብቅ ያለው በ1980ዎቹ ነበር።

በጎርጎሮሳዊው 1991 የሶማሊ ብሔራዊ ንቅናቄ እና ሌሎች አማጺ ቡድኖች ባሬን ከሥልጣን አባረሩ። በዚያው ዓመት ግንቦት ወር ዋና ከተማዋን በሐርጌይሳ ያደረገችው የሶማሌላንድ ሪፐብሊክ ነጻነቷን አወጀች።

ሶማሌላንድ የራሷ ሰንደቅ ዓላማ፣ መገበያያ ገንዘብ፣ መከላከያ ሠራዊት ቢኖራትም እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና አላገኘችም። ምስል Eshete Bekele/DW

“ሶማሌላንድ በ1991 ያገኘችው ነጻነት የለም። ሶማሌላንድ ነጻ የወጣችው ሰኔ 26 ቀን 1960 ነው” ሲሉ ዶክተር ጃማ በአጽንዖት ይናገራሉ። ሶማሌላንድ እንደ ሀገር ያገኘችውን ዕውቅና ለመመለስ ግን ቀላል አልሆነም። “የተፈጠረውን ስህተት ለማረቅ እና የሶማሌላንድን ዕውቅና መልሶ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉ ጃማ አስረድተዋል።

ሶማሌላንድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባታገኝም በሕዝበ-ውሳኔ የጸደቀ ሕገ-መንግሥት አላት። ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የሚመሩት መንግሥት በሚኒስቴር ደረጃ የተዋቀሩ 26 መሥሪያ ቤቶች ያሉት ነው። የራሷን ፓስፖርት ለዜጎቿ ትሰጣለች፤ ምርጫ ታካሒዳለች፣ የመገበያያ ገንዘብም አላት።

የፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የቀድሞ አማካሪ የነበሩት እና አሁን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት መሐመድ ዋርሳሜ “የሀገራት ማኅበር አባል ለመሆን የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ አሟልተናል” ሲሉ ይሞግታሉ። ሶማሌላንድ “ባልጸና እና ብጥብጥ በበረታበት ቀጠና የመረጋጋት ምድር” ተብላ ለመጠራት መብቃቷ ችግር ከያማጣው ቀጠና የተሻለ እንደሚያደርጋት ያምናሉ። 

መሐመድ ዋርሳሜ “የተባበሩት መንግሥታት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ነጻ እና ፍትኃዊ” ብለው በመሰከሩለት ምርጫ ፕሬዝደንት የምትመርጥ መሆኗን ሶማሌላንድ ለምትሻው ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንደ ደጋፊ ማስረጃ የሚያቀርቡት ነው።

ሶማሌላንድ ከ64 ዓመታት በፊት ያገኘችውን ዕውቅና ለመመለስ የጀመረችው ጥረት በተለይ ባለፉት አራት ገደማ ወራት መነቃቃት አሳይቷል። መነቃቃቱ የተፈጠረው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት ነው።

መቀመጫውን በሐርጌይሳ ያደረገው የሰላም እና ልማት አካዳሚ ዳይሬክተር ዶክተር አሕመድ ፋራሕ ሶማሌላንድ ዕውቅና የማግኘት ኢትዮጵያም የመስጠት ሉዓላዊ መብት አላቸው ሲሉ ይሞግታሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

ዐቢይ እና ሙሴ ቢሒ አብዲ የመረጡት መንገድ ግን ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተመኙትን እንዲህ በቀላሉ የሚያሳካ አይደለም። ግብጽ እና ቱርክ የመግባቢያ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ከሶማሊያ ጎን ቆመዋል። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአረብ ሊግ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሰማው ሥጋት ግን መቀመጫውን በሐርጌይሳ ያደረገው የሰላም እና ልማት አካዳሚ ዳይሬክተር ለሆኑት ዶክተር አሕመድ ፋራሕ “ምክንያታዊ” አይደለም። “ሶማሌላንድ በዓለም አቀፍ ሕግ ዕውቅና የማግኘት መብት አላት። ኢትዮጵያም በተናጠል ለሶማሌላንድ ዕውቅና የመስጠት መብት አላት” ሲሉ ዶክተር አሕመድ ተናግረዋል።  

ሶማሊያ የሶማሌላንድን ሉዓላዊነት አትቀበልም። በተናጠል የምታደርጋቸውን ዓለም አቀፍ ሥምምነቶችም ስታወግዝ ቆይታለች። የፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ መንግሥት የመግባቢያ ሥምምነቱ “በሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ ነፃነት እና አንድነት ላይ የተፈጸመ ጥሰት እና ወረራ ነው” በማለት ተቃውሟል።

ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ “አንዲት ስንዝር የሶማሊያን ግዛት ማንም አሳልፎ አይሰጥም” ሲሉ ተናግረዋል። ይኸ “በቀጠናው ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችል ይሆን ወይ?” የሚል ሥጋት የሚያጭር ነው።

“ሶማሊያ ከአልሸባብ ጋር ጦርነት ውስጥ ነች” የሚሉት ዶክተር አሕመድ “ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ልትገባ አትችልም” የሚል አቋም አላቸው። ለዚህም የኢትዮጵያ ወታደሮች “በአሁኑ ወቅት የሶማሊያን ሕዝብ ከአልሸባብ፤ የሶማሊያን መንግሥት ከውድቀት እና ከቀውስ እየጠበቁ በሶማሊያ ይገኛሉ” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። 

“የእጅ አዙር አይነት ጦርነት” ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ሥጋትም ቢሆን ለዶክተር አሕመድ የሚዋጥ አይደለም። ዶክተር አሕመድ እንደሚሉት “የሶማሊያን ሉዓላዊነት ከኢትዮጵያ ሊከላከል የሚችል አስተማማኝ የጸጥታ አጋር የለም።”

በሶማሌላንድ የባርዋቆ የፖለቲካ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር ሙባሪክ አልብዱላሒምስል Eshete Bekele/DW

ተቃውሞ ቢበረታም ሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ የመጨረሻውን ሥምምነት በሁለት ወራት ገደማ ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የመግባቢያ ሥምምነቱ ሙሉ ሠነድ በሶማሌላንድ ለሕዝብ ይፋ አልሆነም። የተቃዋሚው ባርዋቆ የፖለቲካ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር ሙባሪክ አልብዱላሒ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የሚፈራረሙት ሥምምነት በሕጉ መሠረት በፓርላማ መጽደቅ እንደሚኖርበት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሶማሌላንድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል እንድትሆን ማድረግ የመጨረሻው ግብ መሆን አለበት የሚል አቋም ያላቸው ሙባሪክ የመግባቢያ ሥምምነቱ የመጀመሪያ እርምጃ እንደሚሆን ያምናሉ። ለዚህም የፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ መንግሥት ፓርላማውን ማሳመን ይጠበቅበታል።

“የሶማሌላንድ መንግሥት ይኸ የመግባባቢያ ሥምምነት እና ተከትሎ የሚመጣው ሥምምነት የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር እንደሆነ ተቃዋሚዎችን፣ ሕዝቡን እና ፓርላማውን ማሳመን ከቻለ መንገዱን የሚዘጋ ትልቅ ዕክል አይታየኝም” የሚሉት ሙባሪክ “ሁሉም ነገር ሁለቱ መንግሥታት የሚስማሙበት የመጨረሻ ውል ላይ የሚመሠረት ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

“እንደግፈዋለን፤ እንቃወመዋለን ማለት አልችልም” የሚሉት ሙባሪክ አልብዱላሒ አቋም ለመያዝ የመጨረሻውን ሥምምነት ይዘት ማወቅ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።  

የሶማሌላንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደረገው ድርድር ባዘጋጃቸው ሠነዶች ላይ ከባለድርሻዎች ጋር ውይይት ማድረግ መጀመሩን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ከኢትዮጵያ ወገን ሒደቱ ከምን እንደደረሰ እስካሁን በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም። መሐመድ ዋርሳሜ ግን “ኢትዮጵያ መንገዱን ከመራች የአፍሪካ ኅብረት 55ኛ አባል ሀገር እንሆናለን” ሲሉ ተስፋቸውን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW