1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዳግም የቪዛ ክልከላ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ላይ

ረቡዕ፣ መጋቢት 2 2018

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የፊታችን ዐርብ ፖላንድ ውስጥ በሚጀምረው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችለውን ቪዛ እስካሁን አላገኘም ። ፖላንድ ለመግባት የሚያስፈልገውን የሸንገን ቪዛ ለማመልከት 45 ቀናት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙ አሰልጣኝ ይህንኑ ከሦስት ወራት በፊት ብናገርም ሰሚ አጥቻለሁ ብለዋል ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓርማ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓርማምስል፦

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የፖላንድ ጉዞ የቪዛ ክልከላ ተደቅኖበታል

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የፊታችን ዓርብ ፖላንድ ውስጥ በሚጀምረው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችለውን ቪዛ እስካሁን አላገኘም ፖላንድ ለመግባት የሚያስፈልገውን የሸንገን ቪዛ ለማመልከት 45 ቀናት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙ አሰልጣኝ ይህንኑ ከሦስት ወራት በፊት ብናገርም ሰሚ አጥቻለሁ ብለዋል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሥልጣናትን በስልክ አግኝተናቸው በኋላ ደውሉ ቢሉንም መልሰን በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸውን አላነሱም ። 

ዳግም የቪዛ ችግር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ሰቅዞ ይዟል ።  በቀጣዩ ሳምንት ፖላንድ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ፉክክር ምናልባትም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የመሳተፋቸው ሁኔታ አጠራጥሯል ። የዓለም አትሌቲክስ ፉክክሩ ኩጃዊ ፖላንድ ውስጥ ከዓርብ መጋቢት 12 ቀን፣ እስከ ሰኞ መጋቢት 13 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ድረስ ነው የሚከናወነው ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቪዛ ማመልከቻ ጥያቄው ሒደትን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ተነስቶበታል ። ፖላንድ ለመጓዝ የሸንገን ቪዛ ማመልከቻ ሒደት እስከ ከ45 ቀናት ድረስ ሊረዝም ይችላል ። ፖላንድ ይጓዛሉ ተብለው ከነበሩት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አባላት መካከል አንዱ አሰልጣኝ ኅሉፍ ይህደጎ  ናቸው ። ለኤምባሲው የቪዛ ማመልከቻ ዘግይቶ በመግባቱ ችግሩ መከሰቱን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

«የአውሮጳ ሕግ 45 ቀን በፊት ነው የሚለው ከሁለት ወራት በፊት ቀጠሮ መያዝ ነበረበት፤ ግን አልተያዘም እነዚህ ይሄዳሉ ለተባሉት ልጆች ቀጠሮ አልተያዘም፤ [ኤምባሲ] አልገቡም ፖላንድ ጠይቀናል ይላሉ፤ ግን ቦታ ቀጠሮ የለም ነው የሚሉት የሚነግሩን ዛሬም ጠይቀን ነበር እስካሁን የቀጠሮ ቦታ የለም አልተያዘም ነው አሁን መሄጃው እኮ ሰኞ ነው »

በፖላንዱ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ለመሳተፍ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ በሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ ቪዛ ያመለከቱ አትሌቶች እና የቡድን አባላት ዛሬም በድጋሚ ጥያቄያቸው ውድቅ መሆኑ ተገልጧል ። በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰ ከቡድኑ ጋር ይሄዳሉ ተብለው ከነበሩ ሦስት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው ። እስካሁን ባሰባሰበው መረጃ ከሆነ የአትሌቲክስ ቡድኑ ወደ ፖላንድ ለማቅናት ቪዛ የማግኘት እድሉ የጠበበ መሆኑን ገልጧል ።

«በአጠቃላይ እንግዲህ ሦስት አሰልጣኞች፦ ኅሉፍ ይህደጎ፣ ሽባባው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ እንደዚሁም ደግሞ ሐብታሙ ተስፋዬ ወይንም ሑሴን ሽቦ ከሁለት አንዳቸው ከሸገር ሊሄዱ ታስቦ ነበር፤ ተከልክለዋል አንድ የሕክምና ዶክተር እንዲሁም አንዲትፊዚዮ ቴራፒስት ተከልክለዋል በአጠቃላይ የቡድኑ አባላት ቪዛ የማግኘት እድላቸው በእጅጉ የጠበበ መሆኑን ነው ያሰባሰብኩት መረጃ የሚጠቁሙው ።»

ፎቶ ከማኅደር፦ በፖላንድ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ምስል፦ Aleksandra Szmigiel/REUTERS

አሰልጣኝ ኅሉፍ ይህደጎ  ከዚህ ቀደም በርካታ አትሌቶችን የሸንገን ቪዛ በሚጠይቁ እንደ ጀርመን ባሉ አገራት ልከው ለውጤት ያበቁ ናቸው ። አሰልጣኙ በፖላንዱ ውድድር ለመሳተፍ አቅም ይኖራቸዋል ተብለው ለሚገመቱ አትሌቶች ከሦስት ወራት ቀደም ብሎ ቪዛ እንዲጠየቅ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ገልጠዋል ።

«ትልቁ ችግር የፌዴሬሽን ነው ዋና ችግሩ የፌዴሬሽን ነው ተሰብስበን ነበር እኔ በቅድሚያ ተጠይቄ ነበር በስልክም ተጠይቄ ነበር በኋላ ወደ አምሳ አምስት ቀናት ሲቀር ተሰብስበን ነበር በኋላ እኔ ይኼን ሐሳብ አነሳሁ በኋላ በጣም እንቸገራለን ልጆቹ ቀድመን ቀጠሮ ይዘን እናስገባቸው እና እነዚህ የገቡ ወደ  ውድድሩ የሚሄዱ ልጆች [በውድድሩ ለመሳተፍ ውጤት]ካመጡ በኋላ እንዲሄዱ ቀድመው ግን ልጆች መግባት አለባቸው ያመጣሉ የሚባሉ ልጆች፤ ይኼ ችግር ስላለ፣ የአገሪቱ ችግር ስላለ ብዬ ነበር ግን ፌዴሬሽን ዘገየ 20 ምናምን ቀን ሲቀር ፌዴሬሽኑ ጠይቆ ነበር 20 ምናምን ቀን ሲቀር ለልጆቹ [ኤምባሲ] ቀጠሮ ተገኝቷል 20 ምናምን ቀን ሲቀር ቀጠሮ ቢገኝም ባይገኝም ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም ።»

ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሥልጣናት ማብራሪያ ለማግኘት ስልክ ደውለን አግኝተናቸው ነበር ። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንትእና ተቀዳሚ ፕሬዚደንት በኋላ እንድንደውል የነገሩን ቢሆንም መልሰን በተደጋጋሚ ብንደውልም ግን ስልካቸውን አላነሱም ። አትሌቶቹ በሚቀጥለው ሳምንት ውድድር በሚደረግበት ፖላንድ ውስጥ ነበር በቅርቡ ሌላ ውድድርቻቸውን ያጠናቀቁት ። ውድድራቸውን አጠናቅቀው ሚኒማ የሚያሟሉ በሚለዩበት ወቅት ግን አስፈላጊው የ45 ቀን የቪዛ ማመልከቻ አልፎ እንደነበር ጋዜጠኛ ምስጋናውም አሰልጣኝ ኅሉፍም ተናግረዋል።

በፖላንዱ ውድድር ለመሳተፍ ሚኒማ አሟልተዋል በሚል የተመረጡ አትሌቶች  10 መሆናቸው ተገልጧል ።  ከነዚያ አትሌቶች መካከል፦ አትሌት ብርቄ ኃየሎም እና ንግሥት ጌታቸው ቀደም ሲል የፖላንድ ቪዛ ያላቸው መሆኑ ታውቋል ። አትሌት ሣሮን በርኄ፣ ሐረገወይን ካልዓይ ፣ ሞሲሳ ሥዩም፣ ፍሬወይኑ ኃይሉ፣ አዲሱ ይሁኔ፣ ጌትነት ዋለ  እንዲሁም በ800 ሜትር ከቅርብ ጊዜ አንስቶ በዓለም መድረክ ብርቱ ተፎካካሪ የሆነችው አትሌት ጽጌ ዱጉማም ቪዛ ካላገኙት መካከል መሆናቸው ተገልጧል ። 

ፎቶ ከማኅደር፦ በ800 ሜትር ከቅርብ ጊዜ አንስቶ በዓለም መድረክ ብርቱ ተፎካካሪ የሆነችው አትሌት ጽጌ ዱጉማ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ባስገኘችበት ወቅት የተነሳምስል፦ Dylan Martinez/REUTERS

የአትሌቶቹ የቪዛ ጥያቄ ምናልባትም ነገ እና ከነገ በስተያ ቁርጡ እንደሚታወቅ ተገልጧል ። ጋዜጠኛ ምሥጋውም ያነጋገራቸው አትሌቶች ውጤት ለማምጣት በትጋት ልምምድ በሚያደርጉበት ወቅት የቪዛ  ጥያቄ አነጋጋሪ መሆኑ እንዳስጨነቃቸው ተናግረዋል ። እንደ አትሌቶቹ እና የአትሌቲክስ ቡድኑ አባላት ሁሉ ቪዛ ከተከለከሉት መካከል ጋዜጠኛ ምስጋናው ይገኝበታል ። 

«እንግዲህ የዓለም አትሌቲክስ ለሦስት ጋዜጠኞች እድሉን ሰጥቶን ነበር በቦታው ተገኝተን እንድንዘግብ ከኢትዮ ኤፍ ኤም እኔ ምስጋናው ታደሰ እንደዚሁም ደግሞ ሦስት ጋዜጠኞች ጠይቀን ነበር መጥቶልን የቪዛ ማመልከቻ አስገብተናል አሁንም ድረስ ኤምባሲው ቪዛ አልሰጠንም እስካሁን ድረስ ባለው ሒደት ጉዳዩን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ይዞታል በነሱ በኩል ጥረት እየተደረገ  ነው የሚገኘው ቪዛ እንድናገኝ »

ሆኖም የውድድር ጊዜው እጅግ ከመቃረቡ የተነሳ ግን ቪዛው ይሳካል ብሎ ለማሰብ እንደሚከብደው ምስጋናው አክሎ ተናግሯል ። በፖላንዱ ውድድር ለመሳተፍ ዘጠኝ አለያም 10 አትሌቶች፤ አንድ የቡድን መሪ፣ ሁለት አሰልጣኞች አንድ የፌዴሬሽኑ የሚዲያ እና ተግባቦት ባለሞያ፣ ሦስት የስፖርት ጋዜጠኞች እና ሁለት የህክማና ባለሞያዎች ብሎም ሁለት ወጌሻዎች ይሄዳሉ ተብሎ ነበር ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW