ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሄደችው ዛምቢያ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 15 2013
አፍሪቃ ያማረ የምርጫ ታሪክ እጅግም የላትም። በምርጫ ሰሞን ውዝግብ ግርግር፤ ከምርጫ በኋላ መካሰስ መጋደል ለአፍሪቃ ሃገራት ምርጫ መገለጫነቱ ብዙዎችን ያስማማል። ሰላማዊ የምርጫ ሂደትና የሥልጣን ሽግግር ታሳይ የነበረችው ጋና እንኳ ባለፈው ባካሄደችው ምርጫ ማግስት የሕዝብ ቅሬታ ንሮ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ክስና አቤቱታ ይስተጋባባት ይዟል። ሥልጣን ላይ የሚገኙ አብዛኛው የአፍሪቃ መሪዎች ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ ሲቃረብ በየሀገራቸው ሕገ መንግሥት የተደነገገውን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዳቸው የተለመደ ከሆነ ውሎ አድሯል። በዚህ የጨፈገገ የአፍሪቃ የምርጫ ታሪክ ውስጥ ዛምቢያ አዲስ ገድል በዚህ ሳምንት አስመዝግባለች። ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችም የዘንድሮው የዛምቢያ ምርጫ ግልጽ እና በሰላማዊ ሁኔታ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አወድሰውታል። ከፍተኛ የመራጭ ተሳትፎም የታየበት መሆኑም ተገልጿል።
ዋና ከተማ ሉሳካ በኗሪዎቿ ደስታና ጭፈራ የተሞላችው የተቃዋሚ ፓርቲ ተፎካካሪው ሃካኢንዴ ሂቺሌማ ሥልጣን ላይ የቆዩትን ፕሬዝደንት ኤዳር ሉንጉን የማሸነፋቸው ዜና ይፋ ሲሆን ነው። ሂቺሌማ ፤ ሌንጉን በሚሊየን የመራጮች ድምጽ በሰፊ ልዩነት ነው ያሸነፉት። ባለማመን እና ስጋት ሲጠባበቁ የነበሩት ደጋፊዎቻቸው ሉንጉ ወጥተው መፈነፋቸውን በይፋ እስኪያረጋግጡ ተጨንቀው ነበር። በደጋፊዎቻቸው በስሞቻቸው መነሻ ፊደላት HH በመባል የሚታወቁት የ59 ዓመቱ ሃካኢንዴ ሂቺሌማ ከጎርጎሪዮሳዊው 2006 ዓ,ም ጀምሮ ዛምቢያ ባካሄደችው ምርጫ በተፎካካሪነት ቢቀርቡም አልተሳካላቸውም ነበር። የዘንድሮው ድል ያላሰለሰ ጥረታቸው ውጤት ተደርጎ ነው የተወሰደው።
ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ ደቡብ ዛምቢያ ውስጥ የተወለዱት ሂቺሌማ በዛምቢያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ከመንግሥት የነጻ ትምህርት ዕድል ለማግኘት ብዙ ደክመዋል። በኤኮኖሚ እና የንግድ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ከብሪታንያው በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሁለተኛውን ወስደዋል። በግል ጥረታቸው ወደ ንግዱ ዓለም የገቡት ሂቺሌማ ከውጭ ሀገር ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ዛምቢያ በመመለስ በታወቁ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶችን በኃላፊነት መምራት ጀመሩ። በዚህም በንግዱ ዘርፍ ያላቸው የሥራ ልምድ የሰፋ መሆኑ ይነገርላቸዋል። በዚያም ላይ ከዛምቢያ ትላልቅ የከብት ርባታዎች የአንዱ ባለቤት ናቸው። ባለፈው ግንቦት ወር ሂቺሌማ ራሳቸውን በገለጹበት ደብዳቤ፤ «እኔ እረኛ ነኝ፤ ይኽ የልጅነት ፍቅሬ ነው። ይኽ ማለትም ተራ ዜጋ፤ ተራ አፍሪቃዊ።» ብለዋል።
ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዐም ዛምቢያ ፕሬዝደንታዊ እና የምክር ቤት አጠቃላይ ምርጫ አካሂዳ ሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ,ም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የተፈጸመበትን ውጤት ይፋ አድርጋለች። ስድስት ፕሬዝደንታዊ እጩዎች በተሳተፉበት በዚህ ምርጫ ጠንካራው ፉክክር ይደረጋል ተብሎ የተገመተው በአንድነት ለብሔራዊ ልማት ፓርቲ በእንግሊዝኛው ምህጻር UPND እጬ ሂቺሌማ እና በአርበኞች ግንባር እጩ በሆኑት ሉንጉ መካከል ነበር። ሂቺሌማ 59,3 በመቶ ድምፅ በማግኘት፤ 38,3 በመቶ የመራጩን ድምጽ ያገኙትን ሉንጉን በሰፊ ልዩነት ማሸነፋቸውን የዛምቢያ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።
ዛምቢያ ካሏት ባለሃብቶች አንዱ የሆኑት ሂቺሌማ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ለደጋፊዎቻቸው ይኽች በመዳብ ማዕድን የበለጸገች ሀገራቸው በኤኮኖሚ እንዴት ማደግ እንደምትችል መሥራት የሚችለው እንደእሳቸው ያለ የተሳካለት የንግድ ሰው መሆኑን አበክረው ሲገልጹ ነበር። ዛምቢያ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ካሉባቸው የአፍሪቃ ሃገራት አንዷ ናትና በወጣቶች ልብ ተስፋ ጫሩ። ከከተማ ውጪ የሚኖረውን አርሶ አደር ሲቀሰቅሱ ደግሞ የገጠር ልጅነታቸውን፤ ልጅነታቸውን በእረኝነት እንዳሳለፉ እና አሁንም በከብት ርባታው የተሰማሩ የአርሶ አደሩን ችግር ጠንቅቀው የሚያውቅ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ዛምቢያን የዳቦ ቅርጫት ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ እንደሚያውቁ በመንገር ብዙውን መራጭ አማልለው ድምጽ ማስገበሩ ተሳክቶላቸዋል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት የወጣቱን መራጭ ትኩረት መሳቡ ይበልጥ የተሳላካላቸው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ ሳይሆን አይቀርም። በምርጫው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ሰባት ሚሊየን ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች ነው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከአምስቱ አንዱ ሥራ አጥ ነው። የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ኤዳር ሉንጉ ፓርቲ የአርበኞች ግንባር በጎርጎሪዮሳዊው 2011 ዓ,ም ሥልጣን ለመያዝ የበቃው ግብር ለመቀነስ እና ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ቃል ገብቶ ነበር። ሆኖም ለበርካታ ወጣቶች ይኽ እውን ባለመሆኑ ፊታቸውን አዲስ ተስፋ ሰጥቶ አዲስ ቃል ወደ ገባላቸው አንድነት ለብሔራዊ ልማት ፓርቲ አዞሩ።
የፓርቲው መሪ እና ፕሬዝደንታዊው እጩ ሂቺሌማ በገዢው ፓርቲ ተስፋ የቆረጠውን ወጣት የሚያገኙበትን መድረክ ጠንቅቀው አውቀውታል። ማኅበራዊ መገናኛው አውታር። በፌስቡክ እና ትዊተር መራጮችን በየዕለቱ መቀስቀሱን ሥራዬ ብለው ያዙት። በፖለቲካው፣ በስፖርቱ፤ በፋሽንም ሆነ ባህላዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን በፌስቡክና ትዊተር ያጋራሉ። አልፈው ተርፈውም የማንቸስተር ዩናይትድ እና የአርሰናል ደጋፊዎችን ቡድኖቻቸው ሲሸነፉ ወይም ሲያሸንፉ በቀልድ ይወርፏቸዋል። አዘውትረውም በዛምቢያ የአራዳ ልጆች የሚጠቀሙባቸውን ቃላት እንደየአገባቡ ይጠቀማሉ። ይኽ ደግሞ ወደ ወጣቶቹ ልብ አቀረባቸው።
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ለደጋፊዎቻቸው በፖለቲካ ሕይወት ጉዟቸው ተስፋ እንደማይቆርጡ፤ አምስት ጊዜ በምርጫ ተወዳድረው መሸነፋቸውን፤ ወደ ፖለቲካው ዓለም ከገቡ ጀምሮም 15 ጊዜ መታሰራቸውን ደጋግመው ተናግረዋል። የዛሬ አምስት ዓመት ለፕሬዝደንቱ የሞተር ሳይክል አጀብ መንገድ አልሰጡም በሚል በሀገር ክህደት ወንጀል ተከሰዋል። ክሱ ውድቅ እስኪሆንም በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት እስር ቤት ለአራት ወራት ቆይተዋል። አሁን ለዓመታት የተመኙትን ከፍተኛውን የሀገሪቱን ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ተረክበዋል። የዛምቢያ ፕሬዝደንትነታቸውን ባረጋገጡበት ንግግራቸውም ለተቃዋሚዎች፤ «ከእንግዲህ ወከባ ወይም አስለቃሽ ጭስ አይደርስባችሁም እና አትስጉ።» የሚል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ሂቺሌማ ለ15 ዓመታት ዘልቀው የፖለቲካ ሕይወት ጉዟቸው በስድስተኛው የምርጫ ፉክክራቸው ዓላማቸው ሊሳካላ የቻለው ራሳቸውን ለዛምቢያ ፕሬዝደንትነት በማዘጋጀታቸው ነው ብለው ያምናሉ ዛምብያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ኒዮ ሲሙታኒ።
«ላለፉት 15 ዓመታት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ናቸው። በተቃዋሚ ፖለቲከኛነት ሚና እያደገ እና በርካታ የፖለቲካ ተሞክሮ እያካበተ ወደ ዋናው የፖለቲካ ቢሮ የመጣ ሰው ነው የምናየው።»
በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የዴሞክራሲ ፕሬፌሰር የሆኑት ኒስ ቺስማን በበኩላቸው የህዝቡ ተስፋና ፍላጎት ሂቺሌማን ለሥልጣን አብቅቷል ነው የሚሉት።
«ድማጻቸውን ለእሳቸው የሰጡ ሰዎች የመጀመሪያ ትኩረት የሀገሪቱ ኤኮኖሚው ሊያንሰራራ ይችላል የሚል ነው።»
በእሳቸው እምነትም የፕሬዝደንት ሉንጉ መንግሥት ከሥልጣን ለመወገዱ ቀዳሚው ምክንኢት የሀገሪቱ ኤኮኖሚ መላሸቅና ዛምቢያ የተሸከመቺው አሳሳቢ የውጭ ዕዳ ነው።
«በርካታ ዛምቢያውያን ለገጠማቸው የኤኮኖሚ ችግር የአርበኞች ግንባር ይመራው የነበረውን መንግሥት ተጠያቂ ያደርጋሉ። ከሙስና ጋር ያገናኙታል። እየጨመረ ከመጣው የሀገሪቱ ዕዳም ጋር ያያይዙታል።»
ኒዮ ሲሙታኒ ከዚህ ባለፈም የዘንድሮው የዛምቢያን ምርጫ በፕሬዝደንት ሉንጉ አመራር ላይ የተሰጠ «የተቃውሞ ድምጽ» እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
«ይኽን ምርጫ ለመረዳት ዋናው መንገድ በአርበኞች ግንባር ላይ የተሰጠ የተቃውሞ ድምጽ መሆኑን መረዳት ነው። በእርግጥም ሕዝበ ውሳኔ ነው። ለሂቺሌማ ድምፅ የሰጡ የምርጫ ጣቢያዎች ከዚህ ቀደም መርጠዋቸው አያውቁም። ምርጫው ከምንም በላይ የአርበኞች ግንባርን ውድቅ ያደረገ ነው።»
ሃካኢንዴ ሂቺሌማ ከጎርጎሪዮሳዊው 2006 ዓ,ም ጀምሮ በዛምቢያ በተካሄዱ ምርጫዎች ተፎካክረዋል። ዘንድሮ ግን ተፎካካሪያቸውን በሚያስገርም ልዩነት አሸንፈዋል። የድላቸው ምሥጢር የሀገሪቱ ወጣቶችን ቀልብ መሳባቸው መሆኑ ቢታመንም አሁን ቃለ የገቡትን የሥራ ዕድልም ሆነ ሀገሪቱን የዳቦ ቅርጫት የማድረጉን ተስፋ ዕውን ማድረጉ ይቻላቸው ይሆን? ነው ዋናው ጥያቄ።
በዚህ ምርጫ በተለይ የወጣቱ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ነው የሚነገረው። የሂቺሌማ ፓርቲ አባል የሆኑት ጆሴፍ ካሊምብዌ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት በዛምቢያ የምርጫ ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ ከ18 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በብዛት ተሳትፈዋል። ወጣቶቹ ድምጻቸውን ለሂቺሌማ ፓርቲ የሰጡበት ዋና ምክንያት ደግሞ የፓርቲው መሪ ሃካኢንዴ ሂቺሌማ በንግዱ ዘርፍ የደረሱበት ስኬት አነቃቅቷቸው ነው።
«አሁን ሂቺሌማ እስካሁን ስንሟገትለት የነበረውን ቃል ሁሉ ተግባራዊ ለመሆኑ ርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ አስፈላጊው ግብዓት እንዲቀርብላቸው እንፈልጋለን፤ ይኽ ባለፈው አስተዳደር አልተደረገም።»
ሂቺሌማ አሁን ለዓመታት የተመኙትን ከፍተኛውን የዛምቢያን ሥልጣን ተረክበዋል። በዛምቢያ ከሥራ አጥነት ጎን ለጎን የኑሮ ውድነት እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው። ከጎርጎሪዮሳዊው 1998 ዓ,ም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መላ ሀገሪቱን ሲያዳርስ ዛምቢያ የኤኮኖሚ ክስረት ውስጥ ገብታለች። ከውጭ የተበደረችው ከ12 ቢሊየን ዶላር በልጧል። ይኽ ማለት ደግሞ መንግሥት ከሚያገኘው ገቢ 30 በመቶውን ለዕዳ ክፍያ ማዋል ይኖርበታል። ሂቺሌማ ያገኙት ተቀባይነት ሳይደበዝዝ ይኽን ዕዳ እየከፈሉ የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ለመጠገን ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ለሕዝብ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ፤ ገንዘባቸውን ዛምቢያ ውስጥ ሥራ ላይ ለማዋል ለሚፈልጉ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ፤ የሉንጉ አስተዳደር በስፋት የሚታማበትን ሙስናን እንደማይታገሱ ተናግረዋል። 18 ሚሊየን ህዝብ ያላት ዛምቢያ ከምርጫው ግርግር ማግስት አሁን ወደ አንድነት እንድትመጣ የተማጸኑት ሂቺሌማ፤ ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ ማናቸውም ጥቃት እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል። «ዛሬ አዲስ ቀን ነው፤ ለውጥ አለ።» ያሉት አዲሱ የዛምቢያ ፕሬዝደንት፤ «ያለፈውን ከኋላችን እናስቀምጠው፤ ወደ ቤተ መንግሥት የምንገባው ቀድሞ ያሰሩንን በተራችን ለማሰር እና ሕዝባችን ላይ ጥቃት ሲደርሱ የነበሩትንም ለመተካት አይደለም» በማለት ሁሉም ተረጋግቶ የተገኘውን ለውጥ እንዲያጣጥም ጠይቀዋል። ለሰላማዊው የሥልጣን ሽግግር ማሳያም ከሉንጉ ጋር ማሸነፋቸው የተነገረለት ምሽት ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
ሂቺሌማ ሀገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከመሠረተች ወዲህ የተመረጡ ሰባተኛው የዛምቢያ ፕሬዝደንት ናቸው። ዛምቢያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በጎርጎሪዮሳዊው 1964 ነጻ በወጣች ማግሥት የመጀመሪያው መሪ የነበሩት ኬኔት ካውንዳ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መርተዋታል።
ዛምቢያ በአፍሪቃ ውስጥ በመዳብ ማዕድን ሀብቷ በሁለተኛ ደረጃ ያለች ሀገር ብትሆንም በዓለም ገበያ ከጎርጎሪዮሳዊው 2011 ዓ,ም ጀምሮ የመዳብ ዋጋ በመውደቁ ኤኮኖሚዋ ላይ ጫና አሳድሯል። አሁን ለሂቺሌማ ሜዳውም ፈረሱም ይኸው፤ ቃል ወደተግባር የሚለወጥበትን ቀን ዜጎችም ታዛቢዎችም ይጠብቃሉ።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ