ድህረ ምርጫ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ቃለ መጠይቅ
ረቡዕ፣ ግንቦት 26 2018
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል እንደ ክልል ከተዋቀረ ወዲህ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እንደ ክልል ምርጫ ሲከናወንበት ። አራት ብዝኃ ከተሞችን አካትቶ በተዋቀረው በዚህ ክልል ታምራት ዲንሳ የፕሬዚደንቱ እና የፖለቲካ መቀመጫ በኾነው የከፋ ቦንጋ ከተማ ዛሬ ይገኛል ። 22 የምርጫ ክልሎች ያሉት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ 171 የክልል ወንበሮች አሉት ። ከ1780 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች አማካኝነት ነው በክልሉ የዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫ የተከናወነው ። ትናንት በጅማ እና አጋሮ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን የተመለከተው ባልደረባችን ታምራት ዛሬ ደግሞ እስከ ቦንጋ ከተማ ድረስ ያየውን፣ ያስተዋለውን ያካፍለናል ።
ሲመሠረት አራት ብዝኃ ከተሞችን በማካተት የተዋቀረው የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል የቦንጋ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ 105 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል ።
አንጻራዊ ሰላም ያለባቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ክልሎች መካከል አንዱ እና ተጠቃሽ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ነው ያለው ታምራት የከፋው ቦንጋ ከተማ እስኪደርሱ ድረስ «ምንም አይነት ችግር» እንዳልገጠማቸው ገልጧል ።
ጥቅጥቅ ደኖች በብዛት በሚገኙበት አረንጓዴያማው መስመር ላይ እነ ታምራት ያነጋገሯቸው ሰዎች «አካባቢው ፀጥታው የተጠበቀ» መኾኑን እንደነገሯቸው ገልጧል ። የአካባቢው ሰው እንደማንኛውም ሰው ለውጥ እንደሚሻ፣ «የኑሮ ውድነቱ እንዲቀረፍ፣ የዋጋ ግሽበት ወደ ቦታው እንዲመለስለት» ምኞታቸው መኾኑን መግለጣቸውንም አክሎ ዘግቧል ።
ከታምራት ዲንሳ ጋር የተደረገውን ቃለ-መጠይቅ በድምፅ ማገናኛው በኩል ማድመጥ ይቻላል
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026