1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ድምጻዊ እና የመብት ተሟጋቹ ኑሆ ጎበና ሲዘከር

እሑድ፣ ጥር 15 2014

ለዛ ባላቸው እና ወኔ ቀስቃሽ ሙዚቃዎቹ ተወዳጅነትን ያተረፈው ገና በለጋ የወጣትነት ዕድሜው ነበር ። ለዚያውም አማራጭ የመገናኛ ብዙኃን ባልነበረበት እና የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ገና ባልተስፋፋበት የንጉሱ ዘመን። ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር «ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የሙዚቃ ተሰጥዖውን ተጠቅሞ መታገሉን » የሙያ አጋሮቹ ይመሰክሩለታል።

Äthiopien Beisetzung  Oromigna Sänger Nuho Gobena
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ድምጻዊ እና የመብት ተሟጋቹ ኑሆ ጎበና ሲዘከር

This browser does not support the audio element.


ለዛ ባላቸው እና ወኔ ቀስቃሽ ሙዚቃዎቹ ተወዳጅነትን ያተረፈው ገና በለጋ የወጣትነት ዕድሜው ነበር ። ለዚያውም አማራጭ የመገናኛ ብዙኃን ባልነበረበት እና የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ገና ባልተስፋፋበት የንጉሱ ዘመን። ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር «ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ እስከ በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት ድረስ የሙዚቃ ተሰጥዖውን ተጠቅሞ መታገሉን » የሙያ አጋሮቹን ጨምሮ ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ » ድምጻዊ እና የመብት ታጋይ ኑሆ ጎበና ፤ ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን በዛሬው የመዝናኛ ዝግጅታችን ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አንጋፋው የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊ ኑሆ ጎበና የሙዚቃ ስራዎች እና ህይወት ላይ ያተኩራል ፤ አብራችሁን ቆዩ ።

ኑሆ ጎበና በምስራቋ ፈርጥ ድሬዳዋ ከተማ በ1948 ነው የተለደው ፤ በአያቱ መጠራትን የመረጠው ኑሆ መሀመድ ጎበና በቤተሰቡ ውስጥ ከነበ,ሩት አንድ ወንድም እና ሶስት እህቶቹ ይልቅ እርሱ ወደ ሙዚቃው መሳቡ ይነገራል። ገና በለጋ የልጅነት ዕድሜው የሚያከናውናቸውን ነገሮች ሁሉ ከሙዚቃ ጋር ማያያዝ እንደሚወድም ነው አብሮ አደጎቹ የሚናገሩት ። ታላቅ ወንድሙን ጨምሮ ሌሎች አብዛኞቹ አብሮ አደጎቹ ወደ ኃይማኖታዊ ትምህርት ሲወሰዱ እርሱ ግን ሙዚቃን የሙጢኝ ብሎ እስከ ህልፈተ ህይወቱ ዘልቋል ።
በህንድ የሙዚቃ ስራዎች ይመሰጥ እንደነበር የሚነገርለት ኑሆ ዜማውን በመውሰድ በአፋን ኦሮሞ በማንጎራጎር በአቅራቢያው ባሉ ሰዎች እየታወቀ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ ሀሚድ ከተባለ የልጅነት ጓደኛው ጋር በመሆን በዚያ ዘመን ቤት ለብቻ ተከራይተው እስከመውጣት እና የሙዚቃ ስራቸውን ዘጠናክረው መቀጠላቸው ነው የሚነገረው ።

ድምጻዊ እና የመብት ተሟጋቹ ኑሆ ጎበና በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ በተለይ ስለ ኦሮሞ ህዝብ  መብት ዘፍኗል፤ አንድነትን ሰብኳል፤ መለያየትን ነቅፏል፤ ብቻ ብዙ ብሏል። ለዚህ አንዱ ማሳያ ቶኩማ ቶኩማ እያለ ያቀነቀነው ሶስት ትውልድ የተቀባበለው ተወዳጁ ዜማው ነው። 

አንድ እንሁን ፤ አንድ እንሁን ፣የኦሮሞ ልጆች አንድ እንሁን
እስላም ክርስትና እኛን ላይለያዩን 
እምነት የግል ነው ሁላችሁም ተረዱ
የፈጣሪን ስራ ለእርሱ እንተወው 
በጎሳ እና በወንዝ መከፋፈልን እንተው
እያለ ይቀጥላል ኑሆ 
ኑሆ ጎበና በተለይ የመብት ጉዳዮችን በተመለከተ በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ጥርስ የተነከሰበት የንጉሱ ስረዓት ተገርስሶ ደ,ርግ ስልጣኑን እንደተቆጣጠረ ነበር። በዚህም በኑሆ እና ጓደኛው ስራ ያልተደሰቱት የደርግ ባለስልጣናት በ1968 ዓ/ም ለጥቂት ቀናት አስረዋቸው እንደነበረ ታሪኩን በቅርበት የሚያውቁ ይናገራሉ። የባለስልጣናቱ ማሳደድ የሚወደውን የሙዚቃ ስራ እንዳያከናውን እንቅፋት የፈጠረበት ኑሆ በ,ወቅቱ የነበረው አማራጭ እንደማንኛውም በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ ለስደት እንደተዳረገው የወቅቱ ኢትዮጵያዊ ወጣት ሀገር አቋርጦ ወደጎረቤት ሀገር ጂቡቲ መሰደድ ነበር። ኑሆ  ዘመኑን ሙሉ ማለት ይቻላል ህይወቱ በስደ,ት የተሞላ ነበር ። በአፍሪቃ ከጂቡቲ በተጨማሪ ኬንያ  ፤ ከኢስያ በየመን እና ሳኡዲ አረቢያ ከአውሮጳ ጣልያን፤  በሰሜን አሜሪካ ካናዳ እና በሌሎችም በርካታ ሀገራት በስደት አሳልፏል። 
ይህንኑ በተመለከተ ኑሆ በስደት ባሳለፈባቸው ዓመታት በጥቂቶቹ የስደት ጊዜ አብሮት እንዳሳለፈ የሚናገረው ሌላው የኦሮሞ አንጋፋ የሙዚቃ ሰው መሐዲ ሼካ ስለኑሆ ሲናገር ፤ ኑሆ ዕድሜውን በሙሉ ለትግል የኖረ ሲል ይገልጸዋል። ለዚህም የተሻለ ህይወት ሊመራ ከሚችልበት የምዕራቡ አለም ወደ አፍሪቃ የተመለሰበትን አጋጣሚ እንዲህ ያስረዳል።  
ኑሆ ጎበና ከአርባ አመታት በተሻገረ የሙዚቃ ስራው በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሆነ ሌሎች የእርሱ ሙዚቃ አድናቂዎች  የማይሰለቹ ጣዕመ ዜማዎችን አበርክቷል። ምንም እንኳ የነበረበት የስደት ህይወት እና እርሱ ከነበረው ትልቅ አቅም አንጻር ኑሆ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን ሊያበረክት ይችል እንደነበር በርካቶች በጸጸት ሲገልጹ ይሰማል ። ነገር ግን እርሱ በ,አቅሙ የቻለውን አበርክቷል እና አዲሱ ትውልድ ከእርሱ ሊማር የሚገባቸው በርካታ ነገሮች እንዳለም ይታመናል። መሐዲ ሼካ ይህንኑ ያስረዳል።

ድምጻዊ እና የመብት ተሟጋቹ ኑሆ ጎበና በአፋን ኦሮሞ ካበረከታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ውስጥ ቶኩማ ቶኩማ አንድነት አንድነት ፣ ኢሲን ዋምቲ ሀርሜን እናታችሁ ትጣራላች፤ ዱፋን ጂራ ፣ እየመጣሁ ነው ፤ 911 ፤911 እና ነዲፍቴ ፣ ተውሽኝሳ የተሰኙ ስራዎቹ ዘመን አይሽሬ እና ተ,ወዳጆች እንደሆኑ ዘልቀዋል። 
ኑሆ ጎበና በዚህ ሁሉ ዕድሜው በህመም ተይዜ አልጋ ላይ እስኪወድቅ ድረስ ማረፊያ ጎጆ አልነበረውም ፤ ይህኑ የተረዱ አንዳንድ ወጣቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቅመው ኑሆን የማሳከም እና መኖርያ ቤት የመግዛት መርሃ ግብር አከናውነው በቅርቡ በአዳማ ከተማ የመኖሪያ ቤት ገዝተውለት ነበር። ነገርግን ብዙዎች እንደፈለጉት እና እንደተመኙት ከህመሙ አገግሞ በተገዛለትቤት ውስጥ አ,ርፎ መኖር አልቻለም ተሸነፈ ፤ አይቀሬው ሞት ቀደመው ፤ባለፈው ማክሰኞ አመሻሽ በአዳማ ከተማ በሚገኘው መኖርያ ቤቱ በተወለደ በ66 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ። ኑሆ ጎበና ባለትዳር እና የሰባት ልጆች አባት ነበር። ዶይቼ ቬለም በአርቲስቱ ህልፈት የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል። 
ታምራት ዲንሳ 
ሸዋዬ ለገሰ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW