1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድምጽ አልባው ገዳይ የደም ግፊት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6 2016

በመላው ዓለም 1,28 ቢሊየን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 79 ዓመት የሆነ ሰዎች ለከፍተኛ የደም ግፊት የጤና ችግር መጋለጣቸውን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። እንደመረጃው ከተጠቀሰው ቁጥር 46 በመቶ የሚሆኑት ችግሩ እንዳ4ለባቸው እንኳን አያውቁም።

ፎቶ ከማኅደር፤ ዲጂታል የደም ግፊት መለኪያ መሣሪያ
በደም ግፊት ምክንያት ለተለያዩ የጤና እክሎች አልፎም እስከ ህልፈተ ሕይወት የሚደርሱት በርካቶች ናቸው። ለዚህም ነው የህክምና ባለሙያዎች የደም ግፊትን ድምጽ አልባ ገዳይ የሚሉት። ፎቶ ከማኅደር፤ ዲጂታል የደም ግፊት መለኪያ መሣሪያ ምስል David Herrarez/Zoonar/picture alliance

ድምጽ አልባው ገዳይ የደም ግፊት፤ አስቀድሞ መደረግ የሚገባው ጥንቃቄ የህክምና የባለሙያ ምክር

This browser does not support the audio element.

 

አማካኝ የደም ግፊት 120 በ80 መሆኑን የህክምና ባለሙያዎችም ሆኖ የህክምና መረጃዎች ያመለክታሉ። ሰዎች አዘውትረው የደም ግፊታቸውን መጠን በመለካት እንዲከታተሉ ይመከራል።ፎቶ ከማኅደር፤ የደም ግፊት ሲለካ ምስል Getty Images/AFP/R. Gacad

ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም በህክምናው ሃይፐርቴንሽን በደም ቧንቧ ውስጥ የሚኖረው የደም ግፊት 140 በ90 ወይም ከዚያ በላይ ሲደርስ እንደሆነ የህክምና መረጃዎች ያመለክታሉ። እንዲህ ያለው የደም ግፊት መጠን የተለመደ ሲሆን ተገቢው የህክምና ክትትልና ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን አደገኛ መሆኑንም ያሳስባሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰዎች ድንገት ከከፍተኛ የደምግፊት ጋር በተያያዘ በልብ ህመም ወይም ለደም ዝውውር መታወክ ወይም ስትሮክ መጋለጣቸው እየተደጋገመ ነው። እንደ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ በመላው ዓለም 1,28 ቢሊየን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 79 ዓመት የሆነ ሰዎች ለደም ግፊት የተጋለጡ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 46 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳላቸው አያውቁም።  ሳይታወቅ ለተለያየ የጤና ችግር ከመዳረጉም በላይ እስከ ሕልፈተ ሕይወት ያደርሳልና የህክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ የደም ግፊትን ድምጽ አልባው ገዳይ ይሉታል። የደም ግፊትን በየጊዜው መከታተል በመዘናጋት ሊያስከትለው ከሚችለው ውስብስብ የጤና ችግር አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚረዳም ይመክራሉ። በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በግል ክኒሊካቸው የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የአጠቃላይ እና የውስጥ ደዌ ሀኪም ዶክተር ሊበን በሽር ስለደም ግፊትን የደም ማነስና ደም መብዛት በሚል ያልተገባ ስያሜ መስጠት እንዳለ ያመልክታሉ።

የደም ግፊት እና የደም ማነስ

የደም ማነስ ወይም በእንግሊዝኛው የኒሚያ የሚባለው የቀይ የደም ሴሎች በቁጥርም ሆነ በአይነት ሲያንሱ እና ብረት ወይም አይረን የሚባለው ንጥረነገር (የቀይ የደም ሴልን ኦክስጅን የሚያመላልሰው) በደም ውስጥ የእሱ ማነስ ሲከሰት የሚታይ የጤና ችግር ነው። የደም ግፊት በምሳሌ ሲያስረዱ ዶክተር ሊበን በቧምቧ ከሚወርድ የውኃ ኃይል ጋር ያነጻጽሩታል፤ ግፊት የሚባለው ልብ በሚመታበት ጊዜ በደም ቧምቧ ውስጥ የደም አወራረድ ያለውን ኃይል ያመላክታል ነው ያሉት። ይኽ ደግሞ ክንድ ላይ ተደርጎ በመለኪያ አማካኝነት ሊለካ እና ሊታወቅ እንደሚችልም አመልክተዋል።

የደም ግፊት አመጣጥ

ከፍተኛ የደም ግፊት መንስኤው የማይታወቅ እና የሚታወቅ ተብሎ ይለያል። ከቤተሰብ የሚወረስ እንዳለ ሁሉ በአኗኗር ዘይቤ ማለትም አመጋገብ እና እንቅስቃሴ ካለማድረግ፤ እንዲሁም ውፍረት፣ አልክሆል መጠጥ፤ ማጨስ እና ተያያዥ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ልማዶችን ማዘውተር በመንስኤነት ይጠቀሳሉ። ከፍተኛ የደም ግፊት ከሌላ ህመም ጋር በምክንያትም በውጤትም እንደሚያያዝ የሚናገሩት ዶክተር ሊበን፤ የስኳር ህመም፤ የደም ውስጥ ቅባት ወይም ስብ መጨመር ኮሌስትሮል የሚባለው ማለት ነው፤ የደም ስርን በማጥበብ ለደም ግፊት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።

ሊደረግ የሚገባ ጥንቃቄ

የተለያዩ የደም ግፊት መለኪያዎች እየመጡ ነው። አጋጣሚውም ሆነ ዕድሉ ካለ በቀላሉ በእጅ ላይ እንደ ሰዓት በማሰር የራስን የደም ግፊት መለካት ይቻላል። ፎቶ ከማኅደር፤ የደም ግፊት መለኪያ ምስል Robert Guenther/dpa/picture-alliance

የደም ግፊትን በተለይ ደጋግሞ መለካት እንደሚኖርበት፤ ከምንም በላይ ደግሞ የጤና እክሉ እንዳለበት የተነገረው ሰው በተረጋጋ ሁኔታ እቤቱ ሆኖ የደም ግፊቱ መለካት እንዳለበትም ዶክተር ሊበን ያመለከቱት። እርግጥ ነው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሰዎች በቤታቸው የግላቸው የደም ግፊት መለኪያ ላይኖራቸው እንደሚችል ይታወቃል እና ሀኪም ጋር ተመላልሶ በመሄድ ማረጋገጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። እንዲህ ያለው የጤና እክል ከመከሰቱ አስቀድሞ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ በተመለከተም ለህመም ከመጋለጥ በፊት ሰዎች አቅም በፈቀደ ሳያሰልሱ የጤናቸውን ይዞታ ወደ ሀኪም እየሄዱ መታየት፤ ቢያንስ በእግር በመጓዝ በቂ እንቅስቃሴ በየቀኑ ማድረግ፤ አመጋገብን በተመለከተም ጨው እና ቅባት አለማብዛትን መክረዋል።  

ምንም እንኳን ከፍተኛ የደም ግፍት በአብዛኛው የሚያሳየው የተለመደ የህመም ምልክት ባይኖርም የራስ ምታት፤ በእይታ ላይ የሚከሰት ብዥታ፤ የደረት ላይ ህመም እና የመሳሰሉን ሊያስከትል እንደሚችል ነው የሚገለጸው። ያልታከመ ከፍተኛ የደም ግፊት የኩላሊትን ጤናማ ተግባር የማሰናከል፤ የልብ ህመም እና የደም ዝውውር በማዛባት የተለያዩ የጤና እክሎችን እንደሚያስከትልም የህክምና ባለሙያው አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW