1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የምርጫው ውጤት ሰላምን እንዲያመጣ መራጮች ይሻሉ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ግንቦት 24 2018

«ምርጫውን የሚያሸንፈው ፓርቲ፤ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የሚያሰፍንልን እንዲሆን እንሻለን» ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአዳማ ከተማ መራጮች ገልጹ። አስተያየት ሰጪ መራጮቹ እንዳሉት በየአካባቢዮቻቸው ለመምረጥ ረጃጅም ሰልፎችን ለሰዓታት መጠበቅ አዳጋች ቢሆንባቸውም ደኅንነቱ፣ ነጻነቱና ምስጢራዊነቱ ተጠብቆ መምረጣቸውን ገልጸዋል።

ድምፅ ለመስጠት የተሰለፉ የአዳማ ነዋሪዎች
ድምፅ ለመስጠት የተሰለፉ የአዳማ ነዋሪዎች ምስል፦ Seyoum G/DW

ድምፅ ለመስጠት የተሰለፉ የአዳማ ነዋሪዎች

This browser does not support the audio element.

 

ከምርጫው የሚጠበቅ ተስፋ

ለውጥ እድገት መተሳሰብ ፍቅር የሚያመጣ መንግሥት ምርጫውን አሸንፎ አገሪቱን ሲመራት ማየት ምኞታቸው መሆኑን ገልፀው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በለጠ ወልዴ የተባሉ የአዳማ ምርጫ ክልል አንድ መራጭ ናቸው። ግዛው ገመቹ የተባሉትም መራጭ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። «ሰላም አንድነት የሚያመጣልኝን መንግሥት ነው የምፈልገው።»

በኢትዮጵያ ከ80ዎቹ ወዲህ በተካሄዱ ሁሉም ምርጫዎች ላይ በመራጭነት ተሳትፈው ዛሬም ለሰባተኛው ምርጫ መራጭነት ተሳትፎ መብቃታቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡ ገረሱ ኦዳ የተባሉ መራጭ በፊናቸው፤ «አገሪቱ ቆራጥ መሪ ያስፈልጋታል ለሕዝቡ መፍትሄ የሚሰጥ መሪ እንዲመረጥ ፍላጎት አለኝ» ነው ያሉት።

የመራጮች በነቂስ መውጣት

ዶይቼ ቬለ ተዘዋውሮ በጎበኛቸው የአዳማ ከተማ ውስን የ ምርጫጣቢያዎች ላይ እጅግ የበዛ የመራጮችን ተሳትፎ ተመልክቷል። በተለይም አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ከማለዳው እስከ እኩለ ቀን ሰልፉ እጅጉን ከባድ ሆኖም ተመልክተናል። በዚሁ የረጃጅም ሰልፍ ከባድ ተጽእኖ እና የምርጫው ተስፋ ላይ መራጮች አስተያየታቸውን አጋርተውናል።

«እንግዲህ እኔ አሁን ከመጣሁ ከ2፡00 ሰዓት በላይ ሆኖኛል። ለሦስት ሩብ ጉዳይ ነው የመጣሁት እስካሁን ሰልፉ በጣም በዝቶ መቆም አቅቶናል። ሰው መምረጥ ስለፈለገ በጠዋት መጥቷል» ይላሉ አንደኛው መራጭ። ሌላም በምርጫው ላይ ስላላቸው ተስፋ ሲገልጹ፤ «ጥሩ ነገር ነው የምጠብቀው። የሚሆነኝን ለመምረጥም ነው በጠዋት የወጣሁት» ብለዋል። ልጃቸውን አዝለው ለመመምረት የቀረቡ መሳይ ሹሚ የተባሉ እናት ደግሞ «ለሀገሬም ለሚመጣውም ትውልድ ይጠቅማል ብዬ ስላሰብኩኝ የሚጠቅመኝን ፓርቲ መርጫለሁ» ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ያጋሩት።

የተፎካካሪ ፓርቲዎች እጩዎች አስተያየት

በአዳማ በሦስት የ ምርጫክልሎች ተከፍሎ በተካሄደው በዛሬው ምርጫ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች መሳተፋቸው ታውቋል። ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶቹ እጩ አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይ ኢብራሂም አለነ እንዳሉት፤ «የዘንድሮ ሰባተኛው ምርጫ የተረጋጋ ሆኖ እስካሁን ድረስ የታዘብኩት ይሄንን ነው። ኢትዮጵያ መርጣለች የሚለው ነው ውስጤ ያለው።»

አዳማ ላይ ከማለዳ ጀምረው ድምፃቸውን ለመስጠት በርካቶች ተራ ሲጠብቁ ታይተዋልምስል፦ Seyoum G/DW

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ን ወክለው በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) ላይ የሚፎካከሩት እጩ ሀብታሙ ተሰማ በፊናቸው፤ «ሕዝባችን የፈለገውን ፓርቲ ለአምስት ዓመት ይመራኛል ላለው ፓርቲ ካርዱን እየሰጠ ይገኛል፤ ከአስተባባሪ እስከ የጸጥታው አጠባበቅ ሁኔታ ምንም በሕዝባችን ላይ ብዥታ የሚፈጥር ነገር አይደለም» ብለዋል።

አቶ ሀብታሙ አብን በኦሮሚያ ክልል ብቻ በ16 የምርጫክልሎች ውስጥ ተፎካካሪ እጩዎችን እንዳስመዘገበም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት ተወካዩ ተድላ በቀለ እንደተናገሩትም፤ «መስተንግዶ ጥሩ ነው ለኔ፤ እስካሁት ሰውም ተሰልፎ እየመረጠ ነው» በማለት እስካሁን የመጨረሻውን አላውቅም፤ ለአሁኑ ግን ጥሩ ሆኖ ነው ያገኘሁት ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት የአዳማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ በምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ በሰጡበት ወቅት ለዶይቼ ቬለ፤ ከዚህ ምርጫ ዶሞክራሲያዊ ምርጫን ለማካሄድ የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ስፍራ ላይ መድረሱን የተመለከቱበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ወደ 313 ሺህ መራጮች በተመዘገቡበት የአዳማ ሦስት የምርጫ ክልሎች ከሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች 46 እጩ ተፎካካሪዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ እንደሚፎካከሩ ታውቋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW