ድምፅ አልባዉ የኪነ-ጥበብ ጥሪ
ዓርብ፣ ሰኔ 9 2015ኪነ-ጥበብ የህዝብ፤ ሀዘን፤ ደስታ ማህረበራዊ፤ ህይወት ከሚገለፁበት መንገዶች አንዱ ነው። ሕልም እንደ ፈችው ነው። ጥበብ በሜክአፕ ተገልጿል። የዛሬ ስንት ዓመት አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ ብራዚል በሪዮ ዴጄኔሮ አደባባይ እጆቹን ከፍ አድርጎ እና አጣምሮ የወያኔን አምባገነናዊ አገዛዝ ለዓለም እንዳገለጠው ሁሉ ያቺም ጉማ ላይ የታየችዉ ወጣት ሴት የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ አጋልጣለች። ወፍ እንደ አገሩ ይጮኋል አይደለም የሚባለዉ? ጉማ አዋርድ ወጣትዋ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶት ጎን በመቆሟ እንድናውቃት አድርጎናል። መድረኩንም በአግባቡ ተጠቅማበታለች፤ በሀገር ጉዳይ አቋምን መግለጽ እንጅ መሽኮርመም አያስፈልግም።» ይላል ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያገኘነዉ አስተያየት። ባለፈዉ ሳምንት የተካሄደዉ 9ኛው የጉማ አዋርድ አነጋጋሪ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ። የቀድሞዋ የአድማስ ዩኒቨርሲቲ መምህርትና የቢን ኢንተርናሽናል ሆቴል የፋይንስ ኃላፊ፤ ፍላጎት አብርሃም፤ በጉማ ድግስ ላይ ስትገኝ ግንባሯ ላይ የሚንጠባጠብ የሚመስል ደም መሳይ ቀለም ተቀብታለች። አፏም ተለጉሟል። ይሁንና ፍላጎትን አይቶ ሕልም እንደ ፈችው እንደሚባለው ግን አይደለም ያሉ ብዙዎች ናቸዉ። የዚህን ጥበብ ትርጉሙ ያልተረዳ የኢትዮጵያ ሁኔታ ግልፅ ያልሆነለት ብቻ ፤ ወይሞ ደግሞ ሞልቶ እየፈሰሰ ያለው ግፍ የማይሰማው መሆን አለበት ተብሏል። የጥበብን የግል ቋንቋ ተጠቅማ ተማሪዋን ተመስላ መታፈንን፣ መድማትን ለጉማ ታዳሚ በጥበብ ቋንቋ አናግራዋለች። በአዳራሹም ሆነ ከአዳራሽ ዉጭ፤ የሁሉንም ቀልብ ስባለች። የሁሉም ዓይኖች አርፈውባታል። የሶሻል ሚዲያውን ገጾች ሁሉ መሙላትዋ ታይቷል።
ጥበበኛዉም ሆነ የመድረኩ እድምተኛ ጋዜጠኛ ባለፎቶግራፉ ጥበበኛዋን ማለፍ አልቻለም። ምክንያቱም በዝምታ ጩኸት ጆሮዋቸዉ ላይ ትጮህባቸዉ ነበር፤ ሲሉ ብዙዎች ገልፀዋታል። ከግንባሯና ከከንፈሯ (አፏ) ወደ ደረቷ ወረድ ስንልም ሌላ ተጨማሪ ሀገራዊ ትርጉም ያላቸውን ምልክቶች ይነበቡ ነበር። በሀገር ተመስላ በሙሉ የሙሽራ ልብስ ተዉባ ባለ-አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የሕብረ ቀለም ውበት ያለው ሰንደቅ ዓለማችንን ደረቷ ላይ አገልድማ፤ የልብ ቅርፅ ያለው ምልክትም በኢትዮጵያ የሀገሯ ፍቅር እየነደደች መሆኗን በመግለፅ ፎቶው ይናገራል ሲሉም ብዙዎች የልጅትዋን ኪነ-ጥበባዊ አቀራረብ ተርጉመዉታል። አነጣጥረው ካሜራ የደቀኑባትና የፎቶው ትንግርታዊ መልዕክቱን ከሀገር እስከ አድማስ-ባሻገር ለሁሉም እንዲዳረስ ያደረጉ ሁሉ የጥበበኛዋ ማዕድ ተቋዳሾች ሌሎች የኪነ-ጥበብ አድናቂዎች በመሆናቸዉ ተመስግነዋል። በአገራችን ኪነጥበብ እና ጠበብተኞቹ እንዴት ናቸዉ ይሆን?
ኦስካር የተባለዉ በዓለም ትልቁ የፊልም ሽልማት መድረክ ሌላው መታወቂያው ፓለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች መተንፈሻ መድረክ በመሆኑ ነዉ። በዚህ መድረክ ጦርነትን የሚቃወሙ ንግግሮች ተስተጋብተዋል። የቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተብጠልጥለዋል። በቅርቡ የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ 'ጎሎደን ግሎብ' የፊልም የሽልማት መድረክ ላይ ተገኝተዉ ለሃገራቸዉ ጥሪ አድርገዋል። ታዋቂዎቹ የፊልም ተዋናዮች ፖለቲከኞች ነዉርም በገሃድ ሲልም በስምና ወርቅ ይነገርበታል። በጉማ 9ኛ አዋርድ ላይ በሜካፕ ራስዋንበኪነጥበብ ክህሎትዋ አበጃጅታ ያለድምጽ ከፍተኛ ጩኸት ማሰማትዋ ከተነገረላት ወጣት ኢትዮጵያዊት ሌላ ሌሎች ሦስት አራት ሴቶች እንዲሁም በመድረኩ መልክቶችን አስተላልፈዋል። ከነዚህ መካከል የመስጂድ መፍረስን በመቃወም ስሞታን በኪነ-ጥበብ የገለፀችዉ ኢክራም እድሪስ ናት።
በጥበብ ሃሳብን በመግለፃቸዉ ፤ በብዕር ጥበብን በመግለጻቸዉ ብዙ መስዋዕትነትን ከከፈሉት የሃገራችን ብርቅዬ ሰዎች መካከል ደራሲና ጋዜጠኛ በአሉ ግርማ አንዱ ነዉ ሲል በምሳሌነት የሚገልፀዉ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ነዉ። አርቲስት ደሳለኝ አሁንም በመነጋገር ሳይሆን በጉልበት በማመናችን በሃገራችን እና ህዝቧ አደጋ ላይ ወድቀናል ሲል ስጋቱን ይናገራል። የጉማ የሽልማት መድረክ እንዲመሰረት ድጋፍ ከሰጡ አንዱ የሆነዉ ልበ ቀናዉ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ፤ ቤተልሄም ዘ-ኢትዮጵያ የሰዉነት እና የበጎነት ስራዎች የሚል ድርጅት አቋቁሞ ወገኑን እያገዘ ይገኛል።
በጉማ የኪነ-ጥበባት ሽልማት ላይ ያለ ድምፅ በጥበብ ድምፅ ለሆኑን ሦስት አራት ሴቶች ፤ ምስጋናችን ይድረሳችሁ ያሉ በርካቶች ናቸዉ። በጥበብ መልክታችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ አፈና፣ መፈናቀል፣ ግድያ፣ ሰቆቃ፤ የሴቶች መደፈር ይቁም፤ የፍትህ ሥርዓት ይስፈን ብላችሁ መጮሃችሁን ሰምተናል እናመሰግናለን ያሉም ጥቂቶች አይደሉም።
ቃለ ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ